ኢኮኖሚ - ኢዜአ አማርኛ
ኢኮኖሚ
በአማራ ክልል ከ269 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ የልማት ዘርፎች ተሰማርተዋል
Apr 27, 2025 29
ወልዲያ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት 269 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ የልማት ዘርፎች መሰማራታቸውን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ። "ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሀሳብ የወልዲያ ከተማ ባለሃብቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና አጋር አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በወልዲያ ከተማ ተካሂዷል። በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንዳሉት፣ የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማሳደግ በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 269 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 1ሺህ 899 አዳዲስ ባለሀብቶች በተለያዩ የልማት ዘርፎች መሰማራታቸውን ገልጸዋል። ከነዚህ መካከል 43ቱ በአምራች ኢንዱስትሪ፤ ዘጠኙ ደግሞ በአበባ ልማት የተሰማሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። እንደ አቶ እንድሪስ ገለጻ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 96ሺህ 81 ቶን የአበባ ምርት ወደ ውጪ ገበያ በመላክ 139 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማግኘት ተችሏል። በሌላ በኩል 585 አምራች ኢንዱስትሪዎች 324ሺህ 409 ቶን ተኪ ምርቶችን በማምረት 40 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማዳን መቻላቸውን ነው ያስረዱት። ዘርፉን ወደ ተሻለ እመርታ ለማሳደግና ለማጠናከር ሠላም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ የወልዲያ ከተማ ህዝብም ሰላሙን በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል። የሰላሙ ሁኔታ እንዲጠናከር መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ይበልጥ ለማስፋፋትም ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል። ሰርቶ ለማትረፍና ለመጠቀም ሰላም አስፈላጊ በመሆኑ መንግስት ለዘላቂ ሰላም ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ህብረተሰቡም ሳያውቁ ወደ ጥፋት የገቡ ልጆቹን መክሮ እንዲመልስ አስገንዝበዋል። የወልዲያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው በከተማው አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። አዳዲስ ባለሃብቶች እንዲመጡ፣ በብድር አገልግሎት ላይ ያለውን ችግር ለመፍታትና መሬትን ከሦስተኛ ወገን ነጻ በማድረግ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ቁርጠኛ ነው ሲሉም አረጋግጠዋል። ተሳታፊ ባለሀብቶች በበኩላቸው የተሟላ የውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፣ በብድር አገልግሎት ላይ የሚታየውን መጉላላት መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል። በወልዲያ ከተማ አስተዳደር በአራት ቢሊዮን ብር ካፒታል የግንባታ ፈቃድ ያወጡ ሰላሳ ሰባት ባለሃብቶች እንዳሉና አስራ አንዱ ወደ ምርት መግባታቸውን የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ኢትዮጵያ የያዘችውን የልማት ዕቅድ በውጤታማነት ለማሳካት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው
Apr 27, 2025 37
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የያዘችውን የልማት ዕቅድ በውጤታማነት ለመተግበር እና ዘላቂ ዕድገት ለማስመዝገብ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል። በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የሚመራውና የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችን ያካተተው የኢትዮጵያ ልዑክ በቅርቡ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር በመሆን ከተሾሙት ኒጌል ክላርክ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርጓል። ውይይቱ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው እኤአ የ2025 የዓለም ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የጸደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን ነው። በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ውጤታማነትና ድርጅቱ በቅርቡ በኢትዮጵያ በነበረው የፕሮግራም ግምገማ በቀረቡ ግኝቶች ላይ ያተኮረ ውይይት ማድረጋቸውም ተጠቁሟል። ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳን በመተግበር ኢኮኖሚውን ለማዘመን፣ ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ፣ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማበረታታትና የስራ ዕድል ለመፍጠር በምታደርገው ጥረት ለሚያደርገው የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ አመስግነዋል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኒጌል ክላርክ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በመተግበር ግሽበትን ለማውረድ፣ ወደ ውጭ የሚላክ ምርትን ለማሳደግ፣ ገቢ ለማሳደግ እና ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል። በዚህም ኢትዮጵያ የያዘችውን የልማት ዕቅድ በውጤታማነት ለመተግበርና ዕድገትን ለማሳካት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል። ሁለቱ ወገኖች ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
አቶ አህመድ ሽዴ ከአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዴቭ ጃጋዴሳን ጋር ተወያዩ
Apr 27, 2025 47
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዴቭ ጃጋዴሳን ጋር ተወያይቷል። በውይይታቸው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተጠቁሟል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዘርፎችን ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች መክፈቷን ጨምሮ፤ እየተገበረች ያለችውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እየተወሰዱ ስላሉ እርምጃዎች በተመለከተ ተወያይተዋል። የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን በአሁኑ ወቅት የኢንቨስትመንት የትኩረት አቅጣጫዎች በሆኑት አይሲቲ፣ ማዕድን፣ መሠረተ ልማት እና ግብርና የኢንቨስትመንት አማራጮች በኢትዮጵያ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ሥራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል። የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ቡድኑ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እንዲያደርግ አቶ አህመድ ጋብዘው በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል። በተለይም ተቋሙ ፋይናንስ ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን እንደ አዲሱ ዓለም አቀፍ የኤርፖርት ልማት ያሉ እና ሌሎች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን እንዲመለከቱ ዕድል ይፈጥራልም ነው ያሉት። ሁለቱ ወገኖች በሚቀጥሉት ወራት በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ብሎም በኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የስፖርት ትጥቅ አልባሳትን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እያስቻለ ነው - ሚኒስትር መላኩ አለበል
Apr 27, 2025 60
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የስፖርት ትጥቅ አልባሳትን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እያስቻለ እንደሚገኝ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትብብር የተዘጋጀው የ2017 ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በውድድሩ ማስጀመሪያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ታምርት የጎዳና ላይ ውድድር የኢትዮጵያን ምርት ለዓለም የማስተዋወቅ ዓላማ ያነገበ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ በሚደምቅበት የአትሌቲክስ የስፖርት ዘርፍ ውድድር መካሄዱም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማስተዋወቅ ገንቢ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ላደረገው የሩጫ ውድድር መካሄድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ተወዳዳሪዎች ምስጋና አቅርበዋል። የዘንድሮው የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫም አምባሳደሮች የተሳተፉበት እና ለአሸናፊዎች ላቅ ያለ ሽልማት መዘጋጀቱ ከወትሮው ለየት እንደሚያደርገው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ በስፋት እያቀረበች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡ አምራችና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ስፖርታዊ ውድድር ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም የስፖርት ትጥቅ አልባሳትን በሀገር ውስጥ መተካት እያስቻለ ነው ብለዋል። የስፖርት ትጥቅ አምራች ኢንዱስትሪ ትስስርን በማሳደግ የስፖርት ትጥቆች በስፋት እንዲመረቱና ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲቀርቡ የማድረግ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ምርት በመጠቀም ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ማዘውተር እንደሚኖርባቸውም አስታውቀዋል። የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው ባለፉት የለውጥ ዓመታት በስፖርት ልማት ላይ የተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት ልማትን በማስፋት ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ባህሉ ያደረገ ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የስፖርት ትጥቅን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል። በ2017 ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተሳታፊዎች መካከል ኃይለ-ሚካዔል ማስረሻ፣ መቅደስ ጸጋዬ እና አዲስ በቀለ ይገኙበታል። ወጣት ኃይለ-ሚካዔል ማስረሻ በሰጠው አስተያየት መርሐ ግብሩ ከስፖርታዊ ውድድርነት ባሻገር የሀገር ውስጥ ምርትን እንድንጠቀም ግንዛቤ የሚፈጥር ነው ብሏል፡፡ ሌላኛዋ ተሳታፊ መቅደስ ጸጋዬ በበኩሏ የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሚትር ሩጫ ኢትዮጵያውያን ይበልጥ እንዲተባበሩ እና ለጋራ ግብ እንድንተጋ የሚያበረታታ ነው ብላለች። በውድድሩ የሀገርን ምርት ለማስተዋወቅና ሁሉም እንዲጠቀመው ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ የሩጫው ተሳታፊ አዲስ በቀለ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በወንዶች ሞገስ ጥዑማይ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ፣ ጅራታ ሌሊሳ በግል እና ሲዳ አማና ከሸገር ከተማ በቅደም ተከትል የወርቅ፣ የብር እና የነሀሰ ሜዳሊያ በማግኘት የ300ሺህ፣ የ200ሺህ እና የ100ሺህ ብር ሽልማት ተረክበዋል። በተመሳሳይ በሴቶች የሩጫ ውድድር ገመኔ ማሚቴ ከኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ፣ አበዙ ከበደ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ማርታ አለማየሁ በግል በቅደም ተከትል የወርቅ፣ የብር እና የነሀሰ ሜዳሊያ በማግኘት የ300ሺህ፣ የ200ሺህ እና የ100ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በግብርና ኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መደገፍና ማበረታታት ይገባል - በመስኩ የተሰማሩ ሴት ባለሀብቶች
Apr 27, 2025 44
ሀዋሳ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ በግብርና ኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ማበረታታና መደገፍ እንደሚገባ በመስኩ የተሰማሩ ሴት ባለሀብቶች ገለጹ። ባለሃብቶቹ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎችን በትብብር መፍታት ከተቻለ የግብርና ኢንቨስትመንት አዋጭ ነው። በዘርፉ የተሰማሩት ወይዘሮ ብዙነሽ ቦርሳሞ እንደገለጹት፣ በሀዋሳ ከተማ በ300 ሺህ ብር ካፒታል የጀመሩት የግብርና ኢንቨስትመንት በአሁኑ ወቅት ወደ 30 ሚሊዮን ብር አድጓል። በወተት ከብቶች እርባታ ሥራ እንደተሰማሩ የገለጹት ባለሀብቷ፣ የሴቶች ወደ ግብርና ኢንቨስትመንት መሰማራት ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል። በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ሃላፊዎች ሥራቸውን ተመልክተው እንዳበረታቷቸው ገልጸዋል። ግብርና ለኑሮና ለኢኮኖሚ መሰረት በመሆኑ ሴቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ከማድረግ ጀምሮ በዘርፉ የተሰማሩትም ውጤታማ እንዲሆኑ ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል። ድርጅታቸው ለሀዋሳ ከተማና በዙሪያው ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ወተት ከማቅረብ በተጨማሪ ለበርካቶች የገበያ ትስስር መፍጠሩን ጠቅሰው፣ በድርጅቱ ለ30 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል። በቀጣይም ሥራቸውን የማስፋት ዕቅድ እንዳላቸውና ለከተማ አስተዳደሩ የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ሌላኛዋ በከብት እርባታ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት ወይዘሮ ፀሐይ ታደሰ በበኩላቸው ከ1998 ጀምሮ በዚሁ ሥራ ላይ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ የሴቶች በግብርና ኢንቨስትመንት ሥራ መሰማራት ጠቀሜታው ከራስ ባለፈ ለሀገር ነው ብለዋል። ካሏቸው 23 የወተት ላሞች የሚያገኙትን ወተት በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውንና ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል። ሴቶች በግብርና ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ መንግስት ልዩ ትኩረት መስጠቱን አስታውሰው በቀጣይም መጠናከር እንዳለበት ጠቅሰዋል። የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበራ ሌላሞ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በከተማው በግብርና ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ 53 ባለሃብቶች ውስጥ 25 ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ከፍተኛ ካፒታል ያስመዘገቡና በሀገር አቀፍ ደረጃም ተሞክሮ ያላቸው ሴቶች እንዳሉ ጠቁመው፣ ውጤታማ ተሞክሮዎችን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። መሬት ወስደው ያላለሙ ባለሃብቶችን በመለየት እርምጃ መወሰዱን የጠቀሱት አቶ አበራ፣ ከዚህ ውስጥ ወደ መሬት ባንክ የገባውን መሬት ለሌሎች ባለሃብቶች የመስጠት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በግብርና ኢንቨስተመንት መስክ የተሰማሩ ባለሃብቶች ያቀረቧቸውን የማስፋፊያ ቦታና መሰል ጥያቄዎች ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በግብርና ኢንቨስትመንት መስክ በተሰማሩ ሴቶች ላይ ያተኮረ ውይይት በሀዋሳ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።
የክልሉ መንግስት በገባው ቃል መሰረት ምትክ የቤት መስሪያ መሬት ተረክበናል - የልማት ተነሺዎች
Apr 27, 2025 58
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ በሐረር ከተማ መንግስት ለልማት ተነሺዎች ምትክ የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት በገባው ቃል መሰረት የተዘጋጀላቸውን የቤት መስሪያ መሬት መረከባቸውን የአሚር ኑር ወረዳ የልማት ተነሺዎች ገለፁ። በሐረር ከተማ አሚር ኑር ወረዳ በተለምዶ ገንደ ፌሮ በመባል በሚጠራው አካባቢ ለሚከናወነው የኮሪደር ልማት ከአካባቢው በልማት የተነሱ ነዋሪዎች በተገባላቸው ቃል መሰረት ምትክ የቤት መስሪያ ቦታ መረከባቸውን ተናግረዋል። በተለይ የከተማ የመሬት ደረጃን የጠበቀ ቦታ በፍጥነት በመረከባቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል። የኮሪደር ልማቱ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች እና ለመኖሪያ ምቹ የሆነች ከተማን ማስረከብ የሚያስችል ነው ያሉት የልማት ተነሺዎቹ መንግስት የጀመረውን የኮሪደር ልማት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል። በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዓረግ የሐረሪ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ በበኩላቸው ለ25 የልማት ተነሺዎች የከተማውን የመሬት ደረጃ የጠበቀ ቤት የመስሪያ ቦታን ጨምሮ የካሳ ክፍያ መፈፀሙን ገልፀዋል። በመሬት ዝግጅቱ በተለይ የልማት ተነሺዎችን ማህበራዊ መስተጋብር አስጠብቆ ለማስቀጠል ትኩረት መሰጠቱንም አክለዋል። በቀጣይም የዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ለተቀሩ የልማት ተነሺዎች የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ካሁን ቀደም በከተማው ለኮሪደር ልማት ተነሺዎች ምትክ የመስሪያ ቦታ እንደተሰጠም በመረጃው ተጠቁሟል።
በአማራ ክልል የትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመን የትራፊክ አደጋን ለመከላከል እየተሰራ ይገኛል - ባለስልጣኑ
Apr 27, 2025 57
ገንዳ ውሃ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመን የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ስራ እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ባለስልጣን አስታወቀ። በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውኃ ከተማ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ አገልግሎት መስጫ ተቋም ዛሬ በይፋ ስራ ጀምሯል። የባለስልጣኑ ኃላፊ አቶ ዘወዱ ማለደ በስነ-ስርአቱ ላይ እንደገለጹት በክልሉ የትራንስፖርት ዘርፉን መሰረተ ልማት በማሳደግ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ። ከዚህ በፊት በክልሉ በሰባት ዞኖች ብቻ ይሰጥ የነበረውን የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ አገልግሎት አሁን ላይ በሁሉም የክልሉ ዞኖች እንዲሰጥ መደረጉን ለአብነት አንስተዋል። የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት የጂፒኤስ፣ ሲምዪሌተርና የኢንተርኔት መሰረተ ልማትን በማሟላት ዘመኑን የዋጀና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስልጠና እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል። የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን በማልማትና በማዘመን በኩልም በክልሉ ከሚገኙ 251 መናኸሪያዎች መካከል ስምንቱ ደረጃ አንድ መሆናቸውንም አንስተዋል። በክልሉ በትራፊክ ኮምፕሌክስ መሰረተ ልማትን በማሟላት፣ የፓርኪንግ አገልግሎትና የጭነት መኪኖች ተርሚናል በማዘጋጀት በስርዓት እንዲመሩ እንደሚሰራም ተናግረዋል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉዓለም ታደሰ በበኩላቸው እንደተናገሩት ለአሽከርካሪና ተሽከርካሪ አገልግሎት መስጫ ልማቱ ከ10 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል ብለዋል። የክልሉ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ባለስልጣን ከ7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል። በቀጣይም የጥገናና የምርመራ ተቋማት እንዲሁም የደረቅ ጭነት ተርሚናል ለማስገንባት የከተማ አስተዳደሩ የቦታ ልየታ ስራ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል። የገንዳውኃ ከተማ ነዋሪና የተሽከርካሪ ባለቤት የሆኑት መቶ አለቃ በቀለ ተከተል እንዳሉት ከዚህ በፊት የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ አገልግሎት ለማግኘት ጎንደር ከተማ መሄድ ግዴታ ነበር። አሁን በከተማው ሁሉም አገልግሎቶች መጀመራቸው ያለአግባብ ያወጡት የነበረውን ወጭ እንዳስቀረላቸው አስገንዝበዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት የስራ ሀላፊዎች ጋር ተወያዩ
Apr 27, 2025 57
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት የስራ ሀላፊዎች ጋር ተወያይተዋል። ውይይቱ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው እኤአ የ2025 የዓለም ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የጸደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን ነው። አቶ አህመድ ሽዴ የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት ምክትል ጸሀፊ ኤሪክ ሜየር ጋር በሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸው ተገጿል። የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት ምክትል ጸሀፊ ኤሪክ ሜየር የኢትዮጵያ መንግስት እየተገበረ ባለው ሪፎርም ዓለም አቀፍ ችግሮችን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ እየገነባ በመሆኑ አድንቀዋል። ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የኢኮኖሚ ሪፎርም ኢኮኖሚውን ማዘመንና አብዛሃነት መደገፍ በሚያስችል መልኩ እንዲቀጥል የሚደረገውንም ጥረት እንዲሁ። አቶ አህመድ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና ቀጣናዊ መረጋጋት እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች የጋራ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላትን የላቀ አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ነች።
የኢትዮጵያ ታምርት የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ዓላማ የኢትዮጵያን ምርት ለዓለም ማስተዋወቅ ነው - ሚኒስትር መላኩ አለበል
Apr 27, 2025 55
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ዓላማ የኢትዮጵያን ምርት ለዓለም ማስተዋወቅ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ። የ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው። ውድድሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 4ኛ ዓመትን አስመልክቶ የተሰናዳ መሆኑ ተገልጿል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በውድድሩ ማስጀመሪያ ላይ እንደገለጹት፥ የጎዳና ላይ ውድድሩ ዓላማ የኢትዮጵያን ምርት ለዓለም ማስተዋወቅ ነው። አምራችና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ስፖርታዊ ውድድሩ ትልቅ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል። በውድድሩ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ክለቦችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ በሚደምቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድር መካሄዱ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማስተዋወቅ ገንቢ ሚና እንዳለውም አንስተዋል። መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ላደረገው የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር መካሄድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ተወዳዳሪዎች ምስጋና አቅርበዋል። የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፥ ያለፉት የለውጥ ዓመታት የስፖርት ልማት ስራዎች ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው እያስቻሉ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ ከውጪ ይገቡ የነበሩ የስፖርት ትጥቅ አልባሳትን በሀገር ውስጥ በጥራት በማምረት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በሩጫ ውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች በቅደም ተከተል ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች የ300ሺህ፣ የ200ሺህ እና የ100ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት የሚበረከትላቸው ይሆናል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በ2014 ዓ.ም ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ማነቆዎችን በዘላቂነት በመፍታት መዋቅራዊ ሽግግር፣ ተወዳዳሪ፣ ምቹ የቢዝነስ ከባቢያዊ ሁኔታን የመፍጠር እንዲሁም በሀገር ውስጥ ትላልቅ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የመገንባት ዓላማን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር እየተካሄደ ነው
Apr 27, 2025 62
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የ2017 ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ይገኛል። የሩጫ ውድድሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን ውድድሩም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 4ኛ ዓመት ዝግጅትን አስመልክቶ የተሰናዳ መሆኑ ተገልጿል። በዝግጅቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ታድመዋል። አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት፤ ውድድሩ የሀገራችንን ምርት ለአለም ለማስተዋወቅ ያለመ ነው ብለዋል። የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፤ ባለፉት የለውጥ አመታት በተሰሩ ስራዎች ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ተደርጓል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ ከውጪ ይገቡ የነበሩ የስፖርት ልብሶች ጥራታቸውን ጠብቀው በሀገር ውስጥ መመረት መጀመራቸውን በመግለጽ። ውድድሩ ባለሃብቶች በስፖርቱ ዘርፍ መዋለ ንዋያቸውን ፈሰስ በማድረግ አስፈላጊ ምርቶችን በማምረት ድጋፍ እንዲያደርጉ እና በሀገር ውስጥ አምራቾች የተመረቱ የስፖርት አልባሳትን ለማስተዋወቅ እንዲሁም አስፈላጊውን የገበያ ትስስር ለመፍጠር መዘጋጀቱ ተገልጿል። መነሻና መዳረሻውን መስቀል አደባባይ ባደረገው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በሁለቱም ፆታዎች በቅደም ተከተል ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች የ300ሺህ፣ የ200ሺህ እና የ100ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት የሚበረከትላቸው ይሆናል። በክለብ ደረጃ በሁለቱም ፆታዎች ተወዳዳሪዎቻቸውን ለሚያሳትፉ ክለቦች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ለሚወጡም እንዲሁ ሽልማት ተዘጋጅቷል። በውድድሩ የአምራች ኢንዱስትሪ ተዋናዮች፣ አጋር ድርጅቶች፣ ከ34 በላይ የአትሌቲክስ ክለቦችና መላው የአትሌቲክሱ ቤተሰቦች በአጠቃላይ ከ14 ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከብሪታንያ የዓለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
Apr 27, 2025 54
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከብሪታንያ የዓለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር ባሮንስ ቻፕማን ጋር ተወያይተዋል። ሁለቱ ወገኖች የተወያዩት በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ባለው እኤአ የ2025 የዓለም ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የጸደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን ነው። ውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል። በቀጣይም ሁለቱ ሀገራት በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸውን ዕድሎች ማስፋት ላይም ውይይት አድርገዋል። አቶ አህመድ ሽዴ ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለውን የኢኮኖሚ ሪፎርምና ያስገኘውን ውጤት፣ እየገጠሙ ያሉ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች፣ የኢትዮጵያ አዎንታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ሪፎርሙን የበለጠ ውጤታማ የሚያደርጉ እንዲሁም በሁለትዮሽ ትብብር ቀጣይነት ባለው መልኩ መደረግ ስለሚገባቸው ድጋፎች ለሚኒስትሩ ገለጻ ማድረጋቸውም ተመላክቷል። የብሪታንያ የዓለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር ባሮንስ ቻፕማን በበኩላቸው ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን አድንቀዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ የምታደርገውን ጥረትም እንዲሁ። ኢትዮጵያ የጀመረችው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ሀገራቸው በዓለም አቀፍ የልማት ትብብር በኩል ድጋፏን እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል። የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ትብብር በማስፋት ከልማት ትብብር ባለፈ በኢንቨስትመንት በንግድና በፋይናንስ ዘርፎች ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውም ተመላክቷል።
የሌማት ትሩፋት ተቋዳሹ ተምሳሌታዊ አርሶ አደር
Apr 26, 2025 78
የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ አርሶ አደሩን ሀብት እንዲያፈራ እና ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል። በዳውሮ ዞን ሎማ ወረዳ ኤላ ባቾ ቀበሌ የሚገኙ አርሶ አደር ደነቀ ሳንሞ በንብ ማነብ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። አርሶ አደሩ ከ600 በላይ በሚሆኑ የዘመናዊ እና ባህላዊ የንብ ቀፎዎች ላይ ነው የንብ ማነብ ሥራ በመስራት ላይ የሚገኙት። በ10 የተለያዩ መንደሮች ንብ በማነብ ላይ የሚገኙት እኚህ አርሶ አደር በአማካይ በዓመት እስከ 400 ኪሎ ግራም የተጣራ እንዲሁም 200 ኪሎ ግራም የማር ምርት እንደሚያገኙ ተናግረዋል። ከዚሁ የማር ምርት በየዓመቱ ወደ 400 መቶ ሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ እያገኙ እንደሆነ ገልጸዋል። ለሥራቸው ስኬታማነት ከባለሙያዎች የሚያገኙት ድጋፍ አቅም እንደሆናቸው ጠቅሰው በሚያገኙት ገቢ ሀብት መፍጠር መቻላቸውን አስታውቀዋል። የሞዴል አርሶ አደሩን ተሞክሮ የተከተሉ በወረዳው የሀሊአኒ አይሺ እና ኤላ ባቾ ቀበሌ አርሶ አደሮችም በንብ ማነብ ሥራ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል። የሎማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘለቀ ሲሳይ በወረዳው የሌማት ትሩፋት ሥራ በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ይላሉ። ተግባሩን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የክትትልና ድጋፍ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል። የሎማ ወረዳ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ እና የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መስፍን ገበየሁ የአርሶ አደሩን ተሞክሮ ለማስፋት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። በወረዳው ለሚገኙ 14 የማር መንደሮች 220 ዘመናዊ ቀፎ ፣ የማር ማጣሪያ እና የንብ መነቢያ ቁሳቁሶች መከፋፈላቸውንም ጠቁመዋል። የወረዳው ግብርና ፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ልማት ጽህፈት ቤት የንብና ሐር ልማት ባለሙያ ሙሉነሽ ከበደ አርሶ አደሩ የማር ምርታቸውንም እስከ አዲስ አበባ በመላክ እየሸጡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ምርቱ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ክትትል እየተደረገ መሆኑን ስለመግለጻቸውም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በጉባኤው ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ነጥቦች መካከል ፦
Apr 26, 2025 84
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ያካሔደውን ጉባኤ መጠናቀቅ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ነጥቦች መካከል ፦ በያዝነው አመት አጠቃላይ ኢኮኖሚው በታቀደው መሠረት በ8 ነጥብ 4 በመቶ የሚያድግ መሆኑን የሥራ አስፈጻሚው ገምግሟል፡፡ ግብርና በ6 ነጥብ 1 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ በ12ነጥብ 8 በመቶ፣ ማኑፋክቸሪንግ በ12 በመቶ፣ ኮንስትራክሽን በ12 ነጥብ 3 በመቶ፣ አገልግሎት ደግሞ በ7 ነጥብ 1 በመቶ የሚያድጉ መሆናቸው ተገምግሟል፡፡ ያለፉት 9 ወራት ጠቅላላ የመንግሥት ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ134 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ የውጭ ብድር ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ ወርዷል፡፡ ወደ ውጭ ገበያ የሚቀርቡት ስድስት ዋና ዋና ምርቶች፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸሩ ከ82 በመቶ እስከ 386 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ በስንዴ፣ በሩዝ፣ በቡና፣ በሻይ ቅጠል እና በፍራፍሬ ምርቶች በአፍሪካ ቀዳሚ ሆኖ ለመውጣት እየተደረገ ያለው ትግል ፍሬ እያፈራ መሆኑን አይተናል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዝቅተኛ ኑሮ በሚኖሩ ወገኖች ላይ ጫና እንዳያሳድር አስፈላጊ የሆኑና የታቀዱ የድጋፍ መርሐ ግብሮች መከናወናቸውንም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መርምሯል፡፡ ለማዳበሪያ 62 ቢሊዮን ብር፣ ለሴፍቲኔት 41 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር፣ ለነዳጅ 60 ቢሊዮን ብር፣ ለመድኃኒት 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር፣ ለምግብ ዘይት 6 ነጥብ1 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለደመወዝ 38 ነጥብ 4 ቢሊ ዮን ብር ድጎማ ተደርጓል፡፡ ባለፉት 9 ወራት ብቻ 344 ሺህ 790 የውጭ ሀገር ሕጋዊ የሥራ ዕድሎች እና ከ3 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ግሪክ በህጋዊ የስራ ስምሪት በትብብር መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት አካሄዱ
Apr 26, 2025 73
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፡- የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ከግሪክ ልዑካን ቡድን ጋር በጽህፈት ቤታቸው ጋር ተወያይተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ በኢትዮጵያ የግሪክ ኤምባሲ እና የግሪክ የፓርላማ ተወካዮች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል። ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት ህጋዊ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ስምሪት ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው። ግሪክ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሚሰማራ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ መግለጿን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ የአንድ ማዕከል የኢንቨስትመንት አገልግሎት ሊጀመር ነው
Apr 26, 2025 58
ጎንደር፤ሚያዚያ 18/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ኢንቨስትመንትን ይበልጥ ለመሳብ በተመረጡ ስድስት ዋና ዋና ከተሞች የአንድ ማዕከል የኢንቨስትመንት አገልግሎት እንደሚጀመር የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡ ቢሮው ያለፉትን ዘጠኝ ወራት የኢንቨስትመንት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ አካሂዷል፡፡ በመድረኩ የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዮሃንስ አማረ እንደተናገሩት፤ የአንድ ማእከል አገለግሎቱ በክልሉ በኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሀብቶች ከውጣ ውረድ ነጻ የሆነ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡ ማዕከሉ ባለሀብቶች ከዚህ ቀደም የሚያነሷቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታዎች በመሰረታዊነት ለመፍታት የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የክልሉን ኢንቨስትመንት ፍሰት በማሳለጥ ትልቅ ሚና ያለው ነው ብለዋል፡፡ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ የሚጀመርባቸውም ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሃን እና ወልዲያ ከተሞች እንደሆኑም አስታውቀዋል። በማዕከላቱ የኢንቨስትመንት ቢሮን ጨምሮ የመሬት አስተዳደር የከተማና መሰረተ ልማት ንግድና ገበያ ልማት እንዲሁም ገቢዎች ቢሮ በጋራ ሆነው በአንድ ቦታ ባለሀብቱ የሚፈልገውን አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በከተሞቹ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል የአሰራር ደንቦች ተዘጋጅተው መጽደቃቸውን ጠቁመው፤ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው አገልግሎቱን በከተሞቹ ለመጀመር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በከተሞቹ አገልግሎቱን የሚሰጡ የባለሙያዎች ምደባም በክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በኩል እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተው፥ በቀጣይም አሰራሩን ወደ ሌሎች ከተማ አስተዳደሮች ለማስፋት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ የአንድ ማዕከል የኢንቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጡ ወረቀት አልባ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሰራርን የሚከተል ሲሆን ባለሀብቶች በየትኛውም ቦታ ሆነው አገልግሎቱን በኦን ላይን እንዲያገኙ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡ የአንድ ማዕከል የኢንቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጥ የባለሀብቱን ጊዜና ወጪ የሚቀንስ ነው ያሉት በጎንደር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ አቶ ፋሲል ዘውዱ ናቸው፡፡ የከተማውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ከማሳደግና ቀልጣፋና ዘመናዊ የአገልግሎት የአሰጣጥ ስርአት ከማስፈን አኳያ ማዕከሉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አንስተው፤ መምሪያው አገልግሎቱን ለማስጀመር ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 269 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ለአንድ ሺህ 898 ፕሮጀክቶች ኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ወጪን ለመቀነስ አግዞናል- በምሥራቅ ጎጃም አርሶ አደሮች
Apr 26, 2025 61
ደብረ ማርቆስ፤ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ) ፡- ምርታማነትን ለማሳደግ በግብአትነት የሚያዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀማቸው ወጪን ለመቀነስ ያገዛቸው መሆኑን በምሥራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ። በዞኑ ለመጪው የመኸር ወቅት በግብአትነት የሚውል ከ35 ሚሊየን ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የግብርና መምሪያ አስታወቋል። አርሶ አደር አጅጉ ታደለ በዞኑ ጎዛምን ወረዳ የገራሞ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት በማሳቸው ለሚለሙት ሰብል ሲጠቀሙ እንደቆዩ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል። ይህም ለዘመናዊ ማዳበሪያ የሚያወጡትን ወጪ ከመቀነሱም ባሻገር በፊት ያገኙት ከነበረው ምርት በሄክታር ከስምንት ኩንታል በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሰዋል። ያስገኘላቸው ውጤት ከዘመናዊው ማዳበሪያ የልተናነሰ መሆኑን ጠቁመው፤ ተጠቃሚነታቸውን ለማስፋትም ዘንድሮ ከ50 ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። በዚሁ ወረዳ የጥጃን ቀበሌ አርሶ አደር መለሰ ታረቀኝ በበኩላቸው፤ ዘንድሮ ከ80 ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውም ለዘመናዊ ማዳበሪያ በየዓመቱ የሚያወጡት ወጪ በግማሽ ያህል መቀነስ እንዳስቻላቸው አብራርተዋል። አርሶ አደሩ ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራሱን ለማስቻል የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ እንዲጠቀም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ እምቢያለ አለኸኝ ገልጸዋል። ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በግብአትነት የሚውል እስካሁን ከ35 ሚሊየን ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሩ ተሳትፎ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያን ከ130 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለመበተን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። እስካሁንም ከ80 ሺህ በላይ አርሶአደሮችን በማሳተፍ በተካሄደው የመበተንና ከአፈሩ ጋር የማዋሃድ ስራ 6 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን አስረድተዋል። ቡድን መሪው እንዳሉት፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም የመሬቱ እርጥበትን የመያዝና ለረጅም ጊዜ ምርት የመስጠት አቅሙ እንዲያድግ የሚያስችል በመሆኑ በአርሶ አደሩ ዘንድ ተመራጭ እየሆነ መጥቷል። በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2017/ 2018 የምርት ዘመን የአፈር ለምነትን በማሳደግና ሌሎች ተክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከ25 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን መምሪያው አመላክቷል።
በደብረ ብርሃን ከተማ ኢንዱስትሪዎች የሚለቁትን ፍሳሽ አክሞ ለመስኖ ልማት የማዋል ተግባር መጠናከር አለበት
Apr 26, 2025 64
ደብረብርሃን፤ሚያዚያ 18/2017(ኢዜአ)፦በደብረ ብርሃን ከተማ ኢንዱስትሪዎች የሚለለቁትን ፍሳሽ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማከሞ ለመስኖ ልማት ለማዋል የተጀመረው ተግባር መጠናከር እንዳለበት የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት አሳሰቡ። ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ዘመናዊ የማጣሪያ ቴክኖሎጅን ተጠቅሞ አክሞ በሚለቀው ውኃ በ119 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የስንዴ ሰብል ዛሬ በከፍተኛ አመራሮች ተጎብኝቷል። የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በጉብኝት ላይ እንደገለጹት፥ በከተማ አስተዳደሩ በኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሃብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ከነዚህ ኢንዱስትሪዎች የሚወጣውን ፍሳሽ በአግባቡ በማከም ለመስኖ ልማት በማዋል የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም የዳሽን ቢራ ፋብሪካ የሚለቀውን ፍሳሽ በቴክኖሎጂ በማከም ለመስኖ ልማት በማዋል ለሌሎች ፋብሪካዎች ተሞክሮ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል። የዛሬው ጉብኝት ዋና አላማም የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ለአካባቢ ጥበቃና ልማት ያበረከተውን አስተዋጽኦ ለአርሶ አደሩ ለማሳወቅና ሌሎች ፋብሪካዎችም ተግባሩን እንዲከተሉ ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል። የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ መርሻ አይሳነው በበኩላቸው፥ በያዝነው በጋ ወራት 4 ሺህ 527 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 2 ሺህ 413 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ እየለማ ይገኛል። ከለማው ሰብልም ከ144 ሺህ 900 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ የታቀደውን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ፍሳሹን በማጣራት ለመስኖ ልማቱ እንዲውል ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚበረታታ ነው ብለዋል። በዳሽን ቢራ ፋብሪካ የማህበረስብ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታነህ ዝቄ እንዳሉት ፋብሪካው በሚሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው ብለዋል። ፋብሪካው በትምህርት፣በጤና፣በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና በመስኖ ልማት ላይ በማተኮር ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። አሁን ላይም ከፋብሪካው የሚወጣው ፍሳሽ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በማጣራት አካባቢውን ከብክለት ነጻ የማድረግና ተጣርቶ በሚለቀቀው ውሃ አርሶ አደሮች በመስኖ እንዲጠቀሙ እየተሰራ ነው ብለዋል። አርሶ አደር አሸናፊ በላይነህ እንደገለጹት፥ የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ከፋብሪካው የሚለቀውን ፍሳሽ በማከም ንጹህ ውሃ በመልቀቁ ታርሶ የማያውቅ መሬታቸውን በበጋ ስንዴ ማልማት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። በአንድ ሄክታር መሬታቸው ላይ በመስኖ ያለሙት የበጋ ስንዴ ሰብል የፍሬ አያያዙ ጥሩ በመሆኑ ከ45 ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል። በጉብኝቱ ላይም የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና የአካባቢው አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደትን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ ናት - ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
Apr 26, 2025 64
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደትን እስከ እ.አ.አ ማርች 2026 ባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ እንደሆነች የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ገለጹ። በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው የዓለም ባንክ ግሩፕ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ እና ኡዝቤኪስታን የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሂደትን የተመለከተ የከፍተኛ ደረጃ ውይይት ተካሄዷል። ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ዝግጅት እያደረገች ነው ውይይቱ የተዘጋጀው በዓለም ባንክ ግሩፕ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የጋራ ትብብር ነው። በመድረኩ ላይ የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዊላ፣ የዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ፕሬዝዳንት ንድያሜ ዲዮፕ እና የአይኤምኤፍ የስትራቴጂ ምክትል ዳይሬክተር ኬን ካንግ ተሳትፈዋል። የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) የኢትዮጵያን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬት እና ማዕቀፉ ለኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ጥያቄ ያለውን አንድምታ አንስተዋል። ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ እ.አ.አ ማርች 2026 በካሜሮን ያውንዴ በሚካሄደው 14ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብስባ ላይ አባል የመሆኗን ሂደት ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ገልጸዋል። የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዊላ የኢትዮጵያ እና ኡዝቤኪስታን የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደት እንዲፋጠን የባለብዝሃ ወገን ተቋማት እና የሁለትዮሽ አጋሮች አስፈላጊውን የቴክኒክ እና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ ህግን መሰረት ባደረገው የዓለም የንግድ ስርዓት አካል ለመሆን ያሳየችውን ቁርጠኝነት በማድነቅ ለኢትዮጵያ የአባልነት ሂደት ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በአዲስ አበባ ከተማ ለኢትዮጵያ ታምርት የሚዘጉ መንገዶችን ፖሊስ ይፋ አደረገ
Apr 26, 2025 74
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ ከተማ ነገ ለሚደረገው የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ለተሽከርካሪዎችና ለእግረኞች ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን የከተማዋ ፖሊስ ይፋ አድርጓል፡፡ የውድድሩ መነሻ ቦታ መስቀል አደባባይ ሲሆን ለገሃር መብራት፣ ቡናና ሻይ ሜክሲኮ አደባባይ፣ አፍሪካ ህብረት ሳር ቤት (ፑሽኪን አደባባይ)፣ ቄራ አዲሱ መሿለኪያ ድልድይ፣ ጎተራ ማሳለጫ፣ አጎና ሲኒማ፣ ግሎባል ሆቴል፣ መስከረም ማዞሪያ፣ ጥላሁን አደባባይ፣ ሳንጆሴፍ መብራት አድርጎ መስቀል አደባባይ ያበቃል። በዚህም መሠረት :- * ከቅዱስ ዑራኤል አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ (ባምቢስ መቅረዝ ሆስፒታል መስቀለኛ ላይ ) * ከኦሎምፒያ አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ (ኦሎምፒያ አደባባይ ላይ) * ከብሔራዊ ቤተመንግሥት ወደ መስቀል አደባባይ (ብሔራዊ ቤተመንግሥት ላይ) * ከሀራምቤ መብራት ወደ ሳንጆሴፍ መብራት * ከብሔራዊ ቲያትር ወደ ለገሀር መብራት * ከሠንጋ ተራ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ * ከአረቄ ፋብሪካ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ * ከልደታ ወደ ሜክሲኮ አደባባይ * ከልደታ ፀበል ወደ አፍሪካ ህብረት መብራት * ከካርል አደባባይ ወደ ሳር ቤት አደባባይ * ከቫቲካን ወደ ሳርቤት አደባባይ * ከቄራ አልማዝዬ ሜዳ ወደ ቄራ መብራት * ከጎፋ ገብርኤል አቅጣጫ ወደ ጎፋ መስቀለኛ በስር * ከዮሴፍ ወደ ጎተራ ማሳለጫ * ከመስቀል ፍላዎር ወደ አጎና መስቀለኛ * ከጋዜቦ አደባባይ ወደ በቅሎ ቤት ድልድይ ከንጋቱ 11:00 ሰዓት ጀምሮ ፕሮግራሙ እስከሚጠናቀቅ ድረስ መንገዶቹ ይዘጋሉ። በተጠቀሱት መስመሮችም ከዛሬ ምሽት 12 ሠዓት ጀምሮ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
የሸገር ከተማን 'ስማርቲ ሲቲ' እቅድ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
Apr 26, 2025 51
ሚያዚያ፤18/2017(ኢዜአ)፦የሸገር ከተማን 'ስማርቲ ሲቲ' እቅድ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና አገልግሎት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ጉግሳ ደጀኔ ገለጹ። በሸገር ከተማ አስተዳደር ለሚቀጥሉት ሰላሳ ዓመታት ስራ ላይ የሚውል 'ስማርት ስቲ' ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ላይ ያተኮረ ውይይት በቢሾፍቱ ከተማ ተካሄዷል። በውይይቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። በውይይቱ መክፈቻ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና አገልግሎት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ጉግሳ ደጀኔ፤ የከተማው 'ስማርት ሲቲ' ሀሳብ እና እቅድ እውን እንዲሆን የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። ከዚህ ውስጥ ለሚቀጥሉት ሰላሳ ዓመታት ስራ ላይ የሚውለው የሸገር ከተማ 'ስማርት ሲቲ' ረቂቅ ፍኖተ ካርታ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ሀሳብ እንዲሳካ ከተማ አስተዳደሩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ካለፈው ዓመት ጀምሮ የመነሻ ጥናት ማካሄዱን ገልጸዋል። መነሻ ጥናቱ ብዙ ጉዳዮችን ያጠቃልለለ መሆኑን አንስተው፥ ይህን መነሻ ሀሳብ መሰረት በማድረግ ለሰላሳ ዓመታት የሚተገበረው ረቂቅ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን አስረድተዋል። ረቂቅ ፍኖተ ካርታው በውስጡ ከተማው አሁን ያለበትን ሁኔታ መሰረት በማድረግ የህዝብ ብዛት፣ መሰረተ ልማቶች ያሉበት ደረጃ እና ወደፊት እንዴት መሆን እንዳለባቸው የሚያመለክቱ ሀሳቦችን መያዙን አንስተዋል። በተጨማሪም የመሬት አጠቃቀም፣የቱሪዝም ልማትና ከብክለት የጸዳ የትራንስፖርት ሁኔታ እንዲኖር አቅጣጫ ጠቋሚ ሀሳቦችን ያከተተ መሆኑን ተናግረዋል። በአጠቃላይ የሸገር ከተማ 'ስማርት ሲቲ' ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ከሰላሳ ዓመታት በኃላ የሚሰጡ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል። በብልጽግና ፓርቲ የሸገር ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየው ቱሉ በበኩላቸው፥ ሸገር ከተማ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ከተቋቋመ ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል ብለዋል። በመሆኑም ፍኖተ ካርታው በዘላቂነት ተወዳዳሪ እና ዘመኑን የሚመጥን ከተማ ለማፍጠር ትልቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። ፍኖተ ካርታው የከተማ አስተዳደሩን የ10 ዓመት እቅድ፣የከተማዋን የምሥረታ ግብ እና ሌሎችንም ሀሳቦች መሰረት ተደርጎ የተዘጋጀ እንደሆነ አስታውሰዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎችም ረቂቅ የፍኖተ ካርታው ከተማውን በትክክለኛ መንገድ ለመምራትና የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።