ሳይንስና ቴክኖሎጂ
በክልሉ ወጣቶች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት እንዲያበለጽጉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
Apr 27, 2025 51
ደሴ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ወጣቶች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት እንዲያበለጽጉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ። 9ኛው የክልሉ የቴክኖሎጂ፣ የክህሎት፣ የተግባራዊ ጥናትና ምርምር እና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የንግድ ትርዒት እና የደረጃ ሽግግር ሳምንት በኮምቦልቻ ከተማ ተከፍቷል። ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት ለወጣቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት በቴክኖሎጂ፣ በስልጠናና በክህሎት ዳብረው ሥራ ፈጣሪ መሆን እንዲችሉ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን በማበረታታት የክልሉን ኢኮኖሚ የበለጠ ለማነቃቃት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ወደ ባለሃብትነት ሲሸጋገሩም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል። በተለይም ወጣቶች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት እንዲያበለጽጉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።   በመርሃ ግብሩ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፋሪሃት ካሚል በበኩላቸው በቴክኖሎጂ የበለጸገ ትውልድ በመፍጠር ለዜጎች የተሻለ የሥራ እድል ለማመቻቸት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። በተለይም የወጣቶችን የፈጠራ ሥራ በማበረታታትና በማጎልበት በኢኮኖሚ እራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ለሀገርና ለዓለም መትረፍ እንዲችሉ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ወጣቶች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው በመስራት ከአነስተኛ ወደ ባለሃብትነት እንዲሸጋገሩ ለማድረግም የማሰልጠን፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ የማመቻቸት ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል። ዛሬ በአማራ ክልል የተመለከትነው የፈጠራ ሥራ፣ የቴክኖሎጂ ውጤትና የወጣቶች ተነሳሽነት የሚበረታታና የሚደነቅ በመሆኑ የበለጠ ማደግ እንዲችል ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት። የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ስቡህ ገበያው(ዶ/ር) በበኩላቸው ወጣቶችን በቴክኖሎጂ በማገዝ ክህሎታቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሚቆየው የንግድ ትርኢትና የደረጃ ሽግግር ሳምንት በቴክኖሎጂው ዘርፍ 345 አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ታዳጊና መካከለኛ ባለሀብትነት የሽግግር መርሃግብር መኖሩን ተናግረዋል። በፕሮግራሙ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) እና በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን መሀመድ(ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።
የአማራ ክልል የቴክኖሎጂ፣ የክህሎት እና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር የንግድ ትርኢት ሳምንት በኮምቦልቻ ከተማ ተከፈተ
Apr 27, 2025 52
ደሴ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል 9ኛው የቴክኖሎጂ፣ የክህሎት፣ የተግባራዊ ጥናትና ምርምር እና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የንግድ ትርዒት እና የደረጃ ሽግግር ሳምንት በኮምቦልቻ ከተማ ተከፈተ። የንግድ ትርኢትና የደረጃ ሽግግር ሳምንቱን የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፋሪሃት ካሚል ናቸው። በሥነ-ስርአቱ የአማራ ክልል ሥራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አማረ አለሙ እንደገለፁት ፕሮግራሙ በዘርፉ የተሰማሩ ሙያተኞች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን ማዳበር የሚያስችል ነው።   ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሚቆየው የንግድ ትርኢትና የደረጃ ሽግግር ሳምንት 110 በክህሎት፣ 75 የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን 57 የፈጠራ ሥራዎችም ለእይታ ይቀርባሉ ብለዋል። ባለፉት ዓመታት በየተሰማሩበት የሥራ ዘርፎች ለውጥ ያመጡ 345 አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችም ወደ ታዳጊና መካከለኛ ባለሀብትነት ይሸጋገራሉ ብለዋል። በፕሮግራሙ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር)፣ አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል።    
በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዜጎቻችን ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሰራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
Apr 26, 2025 128
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 14/2017(ኢዜአ)፦ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዜጎቻችን ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሰራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ለዚህ ቁርጠኝነታቸን አንዱ ማሳያ የሆነውን የመሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከልን ዛሬ መርቀናል ብለዋል።   ይኽን አዲስ ማዕከል የሚገልጡ ሶስት ቁልፍ አላባውያን አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቆየ እና የተጎዳ ህንፃን ወደ ዘመናዊ እና ሥነውበታዊ ደረጃው ለሥራ ከባቢ አስደሳች ወደ ሆነ ህንፃ መለወጡ አንዱ ነው ሲሉ ገልጸዋል። አገልግሎቶችን ለመሰተር እና ለማቀናጀት በሀገር ውስጥ የለማ ሶፍትዌር በሥራ ላይ መዋሉ ብሎም በታደሰ አመለካከት ብቁ እና ክብር የሞላበት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች መዘጋጀታቸው ሌሎቹ አላባውያን ናቸው ብለዋል። 12 ተቋማት በአንድ ጣሪያ ሥር 40 የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የጀመሩ ሲሆን ይኽም ዜጎች ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ እና አገልግሎቶችን በተሻለ ውጤታማ መንገድ ለማግኘት ያግዛል ነው ያሉት።   እንደዚህ ያሉ ሥርዓቶችን ማበልፀግ ለዜጎች የተለያዩ የአገልግሎት ርካታ መታጣቶች ምላሽ በመስጠት በሂደት ለሰፊው ማኅበረሰብ ርካታ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ሲሉም አክለዋል። የዛሬው ምረቃ ትልቅ ርምጃ መራመዳችንን ያሳያል፤ ኢትዮጵያ በዚህ ማዕከል ላይ ጨምራ እና አስፋፍታ ለዜጎች ሁሉ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥን ታረጋግጣለች ብለዋል።
መሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት በአንድ ጣራ ስር የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን መስጠት ጀመረ
Apr 26, 2025 85
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2017(ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት በአንድ ጣራ ስር የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን መስጠት ጀምሯል። መሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት በአንድ ጣራ ስር የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን በማጣመር ምርጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚሰጥ አገልግሎት ነው። የአሰራር ስረዓቱ ዜጎች የተሟላ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም በቀላሉ የተለያዩ የፌደራል ተቋማትን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ይህም ባለጉዳዮች ወደ ተለያዩ ቢሮዎች የሚያደርጉትን ምልልስ፣ረጅም የወረፋ ጥበቃ እና ከወረቀት ጋር ተዛማጅ የሆኑ ስራዎችን የሚያሰቀር ነውም ብሏል፡፡   አሁን ሥራ ለጀመረው የሙከራ ፕሮጀክት አስራ ሁለት የፌደራል መንግስት ተቋማት የተቀላቀሉ ሲሆን አርባ አንድ የሚሆኑ የህዝብ አገልግሎቶችንም ማቅረባቸውንም ገልጿል፡፡ አገልግሎቶቹም ከፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ ፋይዳ ድጅታል የመታወቂያ ምዝገባ እና ሌሎችንም ያካተተ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።   በአጠቃላይ በፓይለት ፕሮግራም በአንድ ስፍራ የ12 ተቋማት 41 አገልግሎቶች በመሰጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን ተቋማቱም፦ 1. የብሄራዊ መታወቂያ አገልግሎት 2. የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት 3. የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት 4. የገቢዎች ሚኒስቴር 5. የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር 6. የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር 7. የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን 8. የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር 9. የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት 10. የኢትዮ ፖስታ 11. የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 12. ኢትዮ ቴሌኮም ሀሉም ተቋማት በቴክኖሎጂ አማካኝነት በትስስር አገልግሎት እየሰጡም ይገኛሉ።
ኮሌጆች ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት ተወዳዳሪነትን ማሳደግ አለባቸው
Apr 26, 2025 62
አሶሳ፤ሚያዝያ 18/2017(ኢዜአ):-በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ችግር ፈቺ እና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንዳለባቸው የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ገለጸ። ቢሮው ከአሶሳ ዩኒቨርስቲ እና ከአሶሳ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር "ክልላዊ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ እና ጥናትና ምርምር ውድድር" በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱሰላም ሸንገል በወቅቱ እንደገለፁት፥ ኮሌጆች ችግር ፈቺ እና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሰው ሀይል ለማፍራት የተያዘውን ግብ ለማሳካት ተወዳዳሪዎች ባገኙት ዕድል መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል። ውድድሩ የቴክኖሎጂ ትውውቅን በማጎልበት ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶች እንዲወጡ ያግዛል ያሉት አቶ አብዱሰላም ተወዳዳሪዎች ያካበቱትን ዕውቀት የሚያዳብሩበት ነው ብለዋል። የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች የሚሰጡት ተግባር ተኮር ስልጠና ውጤት የሚታይበት እንዲሁም ክፍተቶችን ለመለየት የሚያስችል ውድድር መሆኑን አንስተዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ የክህሎት እና ተቋማት ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አህመድ ሙሳ በበኩላቸው የዚህ ውድድር አሸናፊዎች በቀጥታ በሀገር አቀፍ ውድድር ይሳተፋሉ ብለዋል። የቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ እና የቴክኖሎጂ ትስስር ለመፍጠር አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል። ውድድሩ "ብሩህ አዕምሮዎች፤ በቴክኒክ የበቁ ዜጎች" በሚል መሪ ሃሳብ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ይካሄዳል። በአውቶ መካኒክ፣ ኤሌክትሪክ ስራ፣ ኮንስትራክሽን፣ በእንጨት ስራ እና በአጠቃላይ በስምንት ሙያዎች ውድድሩ ይደረጋል።
ስኬታማ የፈጠራ ውጤት ባለቤቶችን ለመደገፍና ለማብቃት ትኩረት ተሰጥቷል
Apr 26, 2025 56
ዱራሜ፤ሚያዝያ 18/2017(ኢዜአ) :-ስኬታማ የፈጠራ ውጤቶች ባለቤቶችን ለመደገፍና ለማብቃት ትኩረት መስጠቱን የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስትቲዩት አስታወቀ፡፡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዱራሜ ከተማ "ብሩህ አዕምሮዎች በክህሎት የበለፀጉ እጆች" በሚል መሪ ሀሳብ ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ጥናትና ምርምር ውድድር ሲምፖዝየምና ኤግዚቢሽን ተጠናቋል፡፡ በማጠናቀቂያው ላይ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት የጥናት፣ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ሙልጌታ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ውጤታማ የፈጠራ ባለቤቶችን የመደገፍና የማብቃት ስራ ትኩረት አግኝቷል፡፡ በተቋማቱና በፈጠራ ባለቤቶች የሚሰሩ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለውድድር የማቅረብና ተሞክሮና ልምድ እንዲወሰዱ እንዲሁም የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውም ይደረጋል ብለዋል። በቴክኒክና ሙያ የሚሰጠው የስልጠናና የውድድር ስርዓቱ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ደረጃን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ይደረጋልም ብለዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ደቼ በበኩላቸው፥በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በዜጎች ህይወት ላይ ለውጥ የሚያመጡና ችግር ፈቺ ቴክሎጂዎች ማፍለቅ ላይ እንዲያተኩሩ መደረጉን ተናግረዋል። በተቋማቱ እየተሰሩ የሚገኙ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች የግብርናውን ዘርፍ ጨምሮ ሌሎች መርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች የምርምር ስራዎችን እያወጡ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ወደ ማህበረሰቡ በማውረድ በኩል የሚታየውን ውስንነት ለመቅረፍ በቀጣይ በስፋት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ ከወራቤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የክህሎት ተወዳዳሪና የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ሰምረዲን ተማም፥ በክህሎት ዘርፍ በሰራው የፈጠራ ስራ ተሸላሚ መሆን መቻሉን ገልጿል። መንግሥት በዚህን ወቅት የፈጠራ ስራን ለማበረታታትና ለማገዝ እያደረገ ያለው ጥረት እና የውድድሩ መዘጋጀት የክህሎትና የቴክኖሎጂን ዘርፍ ውጤታማነት በማረጋገጥና ተተኪዎች ለማፍራት ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ተናግሯል። በውድድሩም የወራቤ ክላስተር፣የወልቂጤና የቡታጅራ ክላስተሮች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ በመውጣት የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል እንዲሁም የዞንና የልዩ ወረዳዎች ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል፡፡
ተቋሙ አሰራሩን ዲጅታላይዝ በማድረግ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ነው
Apr 26, 2025 52
ሀዋሳ፤ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ) ፦የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አሰራሩን ዲጅታላይዝ በማድረግ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገለጸ፡፡ አገልግሎቱ ዩኒቨርሲቲው ላበለጸጋቸው አዳዲስ ሶፍትዌሮች እውቅና የመስጠትና በቀጣይ ስራዎችን በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፥ ተቋሙ አሰራሩን ዲጅታላይዝ በማድረግ ለደንበኞቹ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግም ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አዳዲስ መተግበሪያዎችን በማበልጸግ ወደ ስራ ማግባቱን ተናግረዋል። ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅንጅት የበለጸጉት አዳዲስ መተግበሪያዎችም አገልግሎቱን ለማዘመን ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል። የበለጸጉት መተግበሪያዎችም የትምህርት ማስረጃን የማጣራት፣ወደ ሌላ ተቋም የመላክና ሌሎች አገልግሎቶችን በፍጥነት ለደንበኞች ለማቅረብ ያስችላሉ ብለዋል፡፡ በቀጣይም ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የፈተና አስተዳደርና የምዝገባ ስርዓቱን ማዘመን የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን ለማበልጸግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ከ34 ሚሊየን በላይ ዜጎችን መረጃ መያዙን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህን መረጃዎች በተፈለጉበት ፍጥነት ለደንበኞች ለማድረስ አዲስ የበለጸጉት መተግበሪያዎች ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑ አስረድተዋል። በተለይም መረጃዎችን በዘመናዊ መልኩ በመሰነድ ለተለያየ አገልግሎት እንዲውሉ እንደሚያግዙ ተናግረዋል፡፡ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን የሚያስችሉ ሶፍትዌር በማበልጸግ ማስረከቡን ጠቁመዋል፡፡ መተግበሪያው የአገልገሎቱን አሰራር በማዘመን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታና የተደራጀ መረጃን ለመያዝ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህም የኒቨርሲቲው ከመደበኛ ማስተማር ስራው በተጓዳኝ የማህበረሰብን ችግሮች የሚፈቱ የምርምር ስራዎችን ከሚያፈልቅበት ስራዎች አንዱ መሆኑን አንስተዋል ብለዋል፡፡ የበለጸገው መተግበሪያ በከፍተኛ ወጪ የቀነሰና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የቀረፈ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ጉመራ ናቸው፡፡ ዪኒቨርሲቲው ያበለጸገው መተግበሪያም ለህዝብ የሚጠቅሙ አዳዲስ አሰራሮችን ለመዘርጋት የሚያደርግው ጥረት አካል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የቴክኖሎጂ ዘርፉን ለስራ እድል ፈጠራ በማዋል የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ ጥረት እየተደረገ ነው
Apr 25, 2025 83
ሀዋሳ ፤ሚያዚያ 17/2017(ኢዜአ):- በሲዳማ ክልል የቴክኖሎጂ ዘርፉን ለስራ እድል ፈጠራ በማዋል የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ። በሲዳማ ክልል የቴክኖሎጂ፣ ክህሎትና የጥናትና ምርምር አውደ ርዕይ በሀዋሳ ሚሊኒየም አደባባይ ተከፍቷል። የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ፤ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ዘርፉን በማጠናከር ልማትን ለማፋጠን ግብ ተቀምጦ እየተተገበረ ነው ብለዋል።   በእስካሁኑ ሂደትም በክልሉ በመፍጠርና በማሻሻል እንዲሁም መቅዳትና ማሸጋገር የቻሉ በርካታ ተወዳዳሪ ዜጎች መፈጠራቸውን ጠቁመዋል። ውጤቱንም ይበልጥ ለማሳደግ በዘርፉ ተሰማርተው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውም አቶ በየነ ተናግረዋል። የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ተወካይና የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት ለቴክኒክና ሙያ ዘርፎች በሰጠው ትኩረት ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ይህንንም ለማጠናከር ሙያንና ክህሎት ለማሳደግና ልምድ ለመለዋወጥ የሚያግዙ ውድድሮችና አውደ ራዕዮች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል። የሲዳማ ክልል ስራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሀገረጽዮን አበበ በበኩላቸው በክልሉ በፈጠራና ቴክኖሎጂ ዘርፉ ያለውን ዕምቅ አቅም ለስራ ፈጠራና የዜጎች ህይወት የሚለውጥ እንዲሆን ታቅዶ በመሰራቱ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል። በተለይም ወደ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች ለመቀላቀል የነበረው አመለካከት በመቀየሩ በርካቶች በዚህ ሂደት እያለፉ ህይወታቸውን እየቀየሩ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም በክልሉ ከራሳቸው አልፈው ሀገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ መወከል የቻሉ ሰልጣኞች መፈጠራቸውን አንስተው ''ይህን አጠናክረን መቀጠል ይገባናል'' ብለዋል። ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ውድድር በክልሉ ከሚገኙ ከመንግስት፣ከግል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የተውጣጡ አሰልጣኞችና ሰልጣኞች እንዲሁም በኢንተርፕራይዞች የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች መቅረባቸውን ገልጸዋል።  
የሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያ በድሮን ቴክኖሎጂ የገነባችውን አቅም አደነቀ
Apr 25, 2025 84
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ የሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያ በድሮን ቴክኖሎጂ የገነባችውን አቅም አድንቋል። በሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ በሪድ የተመራ የልዑካን ቡድን የስካይ ዊን ኤሮናቲክስ ኢንደስትሪንና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን መጎብኘቱን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡ የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በመርሐ-ግብሩ መሳተፋቸውንም ጠቁሟል፡፡ በጉብኝቱ የተሳተፉት የሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል የአቅም ግንባታ ዘርፍ ተወካይ ኮለኔል ሜጀር ሳልህ ኢዲን ሪዞኒ የስካይ ዊን ኤሮናቲክስ ኢንደስትሪን በመጎበኘታቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በዘርፉ የደረሰችበት ደረጃ የሚደነቅ መሆኑንም ጨምረው መናገራቸው በመረጃው ተመላክቷል፡፡ ኢትዮጵያ በድሮን ቴክኖሎጂ የምታከናውናቸው ተግባራትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ብሔራዊ ደኅንነትንና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ በተለያየ መልክ የሚገለጹ ፋይዳዎች እንዳሉትም ኮለኔል ሜጀር ሳልህ ኢዲን ሪዞኒ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያና የሞሮኮ የመረጃና የደኅንነት ተቋማት በተለያዩ መስኮች በትብብር ሢሰሩ መቆየታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ ጠቁሟል፡፡
የኢትዮ-ቻይና የባህል እና የቋንቋ ልውውጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው
Apr 25, 2025 76
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና የቻይና የባህል እና የቋንቋ ልውውጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) ገለጹ። የቻይና ቋንቋ ቀን በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የቻይና ቋንቋ ቀን በተቋሙ መከበር የሀገራቱን ባህሎች ለመተዋወቅ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ የሚበረታታ ተግባር ነው ብለዋል።   የኢትዮጵያ እና የቻይና የባህል እና የቋንቋ ልውውጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። ቋንቋ ሰዎችን፣ ባህልንና ጥበብን የሚያገናኝ ድልድይ መሆኑንም ጨምረው አመላክተዋል። እንደ ኮንፊሺየስ የሙያ ትምህርት ተቋም ያሉ የቻይና ቋንቋ ማዕከላት መቋቋማቸው በሁለቱ ሀገራት በባህል፣ ሳይንስና ስነ ጥበብ መካከል ያለውን የጋራ ግንዛቤ ማሳደግ የሚያስችል ተጨማሪ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። በአሁኑ ጊዜ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በሌሎች ዘርፎች ካለው ጠቀሜታ የተነሳ የቻይና ቋንቋን የመማር ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። በየዓመቱ ተመራቂዎች የቻይና ቋንቋን እንደ ተጨማሪ ትምህርት በተቋሙ እንዲማሩ እንደሚደረግም አመላከተዋል። በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የባህል አማካሪ ዣንግ ያዌ በበኩላቸው የቻይና ቋንቋ ቀን መከበሩ በቻይና ቋንቋ የተካተተውን ታሪክና ባህል ብቻ ሳይሆን መግባባትና አብሮ መኖርን የሚያበረታታ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያና ቻይና በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን የረጅም ጊዜ የሁለትዮሽ ትብብር ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል። የቋንቋ ልውውጥ በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል ባህሎች እንዲራመዱ እና ጥልቀት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። በተጨማሪም በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ቻይና ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
በክልሉ በዲጂታል ዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን በቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ብቁ ዜጋን ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል
Apr 25, 2025 72
አርባ ምንጭ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዲጂታል ዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን በቴክኖሎጂ፣ በእውቀትና በክህሎት የበቃ ዜጋን ለማፍራት በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ። በክልሉ የመጀመሪያ ዙር ክልላዊ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድርና አውደ ርዕይ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።   የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደገለጹት፣ በዲጂታል ዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን በክልሉ በቴክኖሎጂ፣ በዕውቀትና በክህሎት የበቁ ዜጎችን ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። በክልል ደረጃ እየተካሄደ ያለው ውድድርና ዐውደ ርዕይም የተሻለ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸውን ዜጎች ከመለየት ባለፈ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎችን ለመቅዳት እና ለማሸጋገር ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ረገድ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ በስሩ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን እንዲያፈሩ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል። የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዮት ደምሰ በበኩላቸው ውድድሩ በቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፣ ሙያና ሙያተኞችን የማበረታታት ዓላማም እንዳለው ጠቁመዋል። በተጨማሪም ዜጎች የሙያ ክቡርነትን ተረድተው እንደዝንባሌያቸው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን እንዲቀላቀሉ ለማስቻል ነው ብለዋል። በክልሉ በ35 የስልጠና ኮሌጆች ዜጎች በቴክኖሎጂ፣ በክህሎትና በተግባራዊ ጥናትና ምርምር ሥራዎች እንዲበቁ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ በዛብህ ገበየሁ ናቸው። ሰልጣኞቹ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሻራቸውን ሊያኖሩ ይገባል ብለዋል። ክህሎት መር የሥራ ዕድል በመፍጠርና ለአምራች ኢንዱስትሪው የሰው ሃይል በማቅረብ በኩል አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል። በመድረኩ የክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የዘርፉ አሠልጣኞችና ሠልጣኞች እንዲሁም ኢንተርፕራይዞች ተገኝተዋል።
የአሜሪካው ኩባንያ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሃዋላ አገልግሎትን የማስፋት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ
Apr 25, 2025 56
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፡-የአሜሪካው ቪዛ ባንክ ኩባንያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጣናው ዓለም አቀፍ የሃዋላ አገልግሎትን የማስፋት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአሜሪካው ቪዛ ኢንክ ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርድ አገልግሎት ኩባንያ ጋር በሃዋላ፣ በዲጂታል ፋይናንስና በአዳዲስ የትብብር ዕድሎች ላይ በጋራ ለመስራት መክረዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንግስት በእኩልነትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የዲጂታላይዜሽን ትብብር እንዲጎለብት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል። የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስኬት ለማረጋገጥ በህግ ማዕቀፍ፣ በመሠረተ ልማቶችና በሰው ኃይል ግንባታ ላይ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። ሀገራዊ ስራዎችን ዲጂታላይዝ ለማድረግና የፋይናንስ ምርቶችንና አዳዲስ አገልግሎቶችን በኢትዮጵያ ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። የቪዛ ኢንክ የደቡብና ምስራቅ አፍሪካ ሪጅን ምክትል ፕሬዝዳንት ሚካኤል በርነር ዓለም አቀፍ የቪዛ አገልግሎትን በኢትዮጵያ እና በቀጣናው ሀገራት ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል። የቪዛ ክፍያ የዲጂታል ስነ-ምህዳርን በኢትዮጵያ ለማጎልበት እንደሚያስችል ጠቁመው፥ ዓለም አቀፍ እና ክልላዊ ምርጥ ተሞክሮዎችን ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል። የኢትዮጵያን አጠቃላይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ እንዲሁም የዲጂታል ስትራቴጂ ፕሮጀክቶች እና የትግበራ እቅዶችን አስመልክቶ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮ ቴሌኮም እና ቪዛ ኢንክ ኩባንያ በዲጂታል ፋይናንስ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ
Apr 24, 2025 163
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 16/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮ ቴሌኮም እና የአሜሪካው የክፍያ ካርድ አገልግሎት ኩባንያ ቪዛ ኢንክ በዲጂታል ፋይናንስ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ከአሜሪካው ቪዛ ኢንክ ኩባንያ የደቡብ እና ምስራቅ አፍሪካ ሪጅን ምክትል ፕሬዝዳንትና ኃላፊ ሚካኤል በርነር ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል።   ውይይቱ በዓለም አቀፍ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ አዳዲስ የትብብር ዕድሎችን መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው። በውይይቱ ላይ ተቋማቱ ነሐሴ 2016 ዓ.ም በጋራ ይፋ ያደረጉት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የዋሌት ቨርቹዋል ቪዛ ካርድ እና በቪዛ ዳይሬክት እንዲሁም በቴሌብር ረሚት በኩል የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ሐዋላ አገልግሎቶች የሚገኙበት የአፈጻጸም ደረጃ ቀርቧል። በሐዋላ አገልግሎቶቹ የተመዘገበው አበረታች አፈጻጸም እና በተለይም ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የገበያ እድል ማደጉ ተመላክቷል። እንዲሁም የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በዓለም አቀፍ ሐዋላ አገልግሎቶች ላይ ቀጣይነት ያለው ማሻሻያ እየተከናወነ መሆኑም ተነስቷል። ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ፍሬሕይወት ቴሌብር ለአካታች እና ተደራሽ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ ነው ብለዋል። ቴሌብር ከቪዛ ዓለም አቀፍ ኔትወርክ ጋር በመጣመር አዳዲስ ፈጠራ የታከለባቸው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ማቅረብ የሚቻልባቸው ዕድሎች መኖራቸውን ገልጸዋል። የቪዛ ኢንክ የልዑካን ቡድን በጋራ ተግባራዊ የተደረጉት ዓለም አቀፍ አገልግሎቶች ስኬት በማድነቅ የገበያውን ከፍተኛ አቅም መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል። ተጨማሪ የትብብር ዕድሎችን በመፈተሽ የፋይናንስ ተደራሽነትን የሚያሰፋና በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ባህል ግንባታ ትብብር ላይ የሚሰራ የጋራ ቡድን ለማቋቋም መስማማታቸውን የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ ያመለክታል።
ከምርምር ማዕከሉ ያገኙት "ቴላ" የተሰኘ የበቆሎ ዝርያ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አርሶ አደሮች ገለጹ
Apr 24, 2025 104
ሀዋሳ፤ ሚያዚያ 16/2017 (ኢዜአ)፡-ከሀዋሳ መለስተኛ የበቆሎ ምርምር ማዕከል ያገኙት "ቴላ" የተሰኘ የበቆሎ ዝርያ ድርቅን መቋቋምና ምርታማ መሆኑ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በሲዳማ ክልል የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ። በወረዳው የጋሎ ኡርጌሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት ቴላ የተሰኘው የበቆሎ ዝርያ ተባይና ድርቅን የሚቋቋም ሲሆን ዝርያውን መጠቀም ከጀመሩም አራት አመት ሆኗቸዋል። በእነዚህ ጊዜያት የተሻለ ምርት በማግኘትና ገቢያቸውን በማሳደግ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውንም አርሶ አደሮቹ ገልፀዋል። ከቀበሌው ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ስምኦን መንገሻ እንዳሉት ቀደም ሲል ሲጠቀሙበት ከነበረው የበቆሎ ዘር በሄክታር ከ50 ኩንታል በላይ ምርት አግኝተው አያውቁም። ከዚህ በተጨማሪ ዝርያው የዝናብ እጥረት ሲገጥም ድርቅን መቋቋም ስለማይችልና በቀላሉ በትል ስለሚጠቃ ትሉን ለማጥፋት ኬሚካል ይረጩ እንደነበር አስታውሰው ይህም ለወጪ ሲዳርጋቸው መቆየቱን ተናግረዋል። ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ በወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል ሥር ካለው ሀዋሳ መለስተኛ የበቆሎ ምርምር ማዕከል ያገኙት "ቴላ" የተሰኘ የበቆሎ ዝርያ ድርቅን ስለሚቋቋም ችግራቸው መፈታቱን ነው የገለጹት። "ከማዕከሉ ያገኘነው የበቆሎ ዝርያ የዝናብ እጥረት ሲገጥም ሳይደርቅ እድገቱን ይቀጥላል፤ በሄክታርም እስከ 100 ኩንታል ምርት እያገኘንበት ነው ሲሉም" ጠቅስዋል።   ሌላው ሞዴል አርሶ አደር ካሳ ካያሞ በበኩላቸው እንዳሉት ከማዕከሉ ያገኙት የበቆሎ ዝርያ ከምርታማነቱና ድርቅን ከመቋቋም አቅሙ ባለፈ የተለየ የምግብነት ጣዕም እንዳለው ተናግረዋል። ዘንድሮም ከምርምር ማዕከሉ ዘር ወስደው በመዝራት በአሁኑ ወቅት ቡቃያውን እየተንከባከቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። አምና ካለሙት ማሳ በሄክታር እስከ 100 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ያስታወሱት አርሶ አደር ካሳ፣ አንዱን ኩንታል በ4 ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል። ቀደም ሲል ይጠቀሙት የነበረው የበቆሎ ዝርያ በሄክታር ከ20 እስከ 40 ኩንታል ቢገኝበትም በቀላሉ በትል ስለሚጠቃ ለኬሚካል የሚወጣው ወጪና የሚገኘው ገቢ አይመጣጠንም ነበር ብለዋል።   በወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል የሀዋሳ መለስተኛ የበቆሎ ምርምር ማዕከል ተመራማሪና የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ይድነቃቸው መርዕድ እንዳሉት "ቴላ" የበቆሎ ዝርያ ባለፉት አራት ዓመታት ምርምር ከተደረገባቸው የበቆሎ ዝርያዎች አንዱ ነው። ይህ የበቆሎ ዝርያ ቀደሞ አርሶ አደሩ ሲጠቀምበት ከነበረው በቆሎ ጋር ሲነጻጸር ተባይ፣ በሽታንና ድርቅን የመቋቋም አቅሙና ምርታማነቱ ከፍተኛ እንደሆነ በምርምር መረጋገጡን ተናግረዋል። በአርሶ አደሩ ዘንድ ያለው ተፈላጊነት ከፍተኛ በመሆኑ ይህን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ለማቅረብ ዘር ከሚያባዙ ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።  
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጀማሪ ስራ ፈጠራ(ስታርታፕ) ሥነ-ምህዳር ማጠናከር የሚያስችል ውይይት ተደረገ
Apr 24, 2025 89
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 16/2017(ኢዜአ)፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ ባዳዳ(ዶ/ር) ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሉዊስ አንቶኒ ጋር በኢትዮጵያ ያለውን የጀማሪ ስራ ፈጠራ(ስታርታፕ) ሥነ-ምህዳር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል። የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ ከአውሮፓ ህብረት እና ኤክስፐርቲስ ፍራንስ ጋር በመተባበር የስታርታፕ ሥነ-ምህዳሩን ለማጠናከር 10 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ እንደተዘጋጀም ተገልጿል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ ባዳዳ(ዶ/ር) ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሉዊስ አንቶኒ ጋር ተወያይተዋል። ውይይቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጀማሪ ስራ ፈጠራ (ስታርታፕ) ሥነ-ምህዳር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ከአውሮፓ ህብረት እና ኤክስፐርቲስ ፍራንስ ጋር በመተባበር የስታርታፕ ሥነ-ምህዳሩን ለማጠናከር 10 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል። ይህም ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውንና በቅርቡ ወደ ስራ የሚገባውን የስታርታፕ አዋጅ ወደ ተግባር ለማሸጋገር እንደሚረዳ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል። በተጨማሪም የስታርታፕ ኢንኩቤሽን ሞዴሎችን ማሻሻል እና የስታርታፖች አቅም ማጠንከርና የፈንድ ምንጮችን ለመጨመር መግባባት ላይ ተደርሷል። ሚኒስትር ዴኤታው እና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ ያሉ ስታርታፖች በአውሮፓና ፈረንሳይ የስታርታፕ ስነምህዳር እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉብት ዕድል በሚፈጠርበት ሁኔታ ላይ በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ 4ኛው ክልላዊ የስራ ፈጠራ ውድድር መርሃ ግብርን አስጀመሩ
Apr 23, 2025 122
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2017(ኢዜአ)፦ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ 4ኛው ክልላዊ የስራ ፈጠራ ውድድር መርሃ ግብርን አስጀምረዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ ውድድሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት በክልሉ በቴክኒክ ሙያ ኮሌጆች መምህራን እና ተማሪዎች የሚዘጋጁ የፈጠራ ስራዎች የማህበረሰቡን የእለት ተእለት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያቃልሉ ሊሆኑ ይገባል። በውድድሩ 12 የቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች 34 መምህራን፣ 59 ተማሪዎች እና 2 የግል ድርጅቶች መቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።   በተወዳዳሪዎቹ ተዘጋጅተው ከቀረቡ የፈጠራ ውጤቶች መካከል የእርሻ ምርት መሰብሰቢያ ማሽኖች፣ የዶሮ መፈልፈያ፣ የእንስሳት መኖ ማዘጋጃና ለቤት ግንባታ የሚውሉ ግብዓቶች እንደሚገኙበትም ተጠቁሟል። ለውድድሩ የሚቀርቡ የፈጠራ ስራዎች የማህበረሰቡን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ መሆን እንደሚገባቸው ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል። በውድድሩ ላይ ለእይታ የቀረቡ ምርቶች የክልሉን ህዝብ የእለት ተእለት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያቃልሉና የወጣቶችን የስራ ፈጠራ ባህል የሚያበረታቱ እንዲሆኑም አስገንዝበዋል። በፈጠራ ላይ የሚሰማሩ ሰዎች የሚሰሯቸውን ሥራዎች ለመደገፍ የክልሉ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።   የሶማሌ ክልል የክህሎትና ሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ጌይድ፤ 4ኛ ዙር ዓመታዊ የቴክኒክ ኮሌጆች ያቀረቡት ምርቶች ለግብርና፣ ለእንስሳት እርባታና ለስራ ፈጠራ የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱና አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች የቀረበበት ነው ብለዋል። ለሶስት ቀናት የሚቆየው ይህ ውድድር "ጤናና አምራች ዜጋ ለሁለንተናዊ እድገት መሰረት ነው" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ የሚቆይ ሲሆን በውድድሩ ለሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች እውቅና እና ሽልማት እንደሚበረክት ገልጸዋል። በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ፣ የክልሉ የክህሎትና ስራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ጌይድ፤ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ አደንና ሌሎች አመራሮች መገኘታቸው ተጠቅሷል።
የቴክኖሎጂና የክህሎት ውድድሩ የንድፈ ሀሳብ እውቀቶችን ወደ ተግባር ለመለወጥ ያግዛል - የውድድሩ ተሳታፊዎች
Apr 23, 2025 81
ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዚያ 15/2017(ኢዜአ)፦ ክልል አቀፍ የቴክኖሎጂ፣ የክህሎት እና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር ለመቀየር እንደሚያግዛቸው የውድድሩ ተሳታፊዎች ገለጹ። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ "ብሩህ አዕምሮዎች በክህሎት የበቁ ዜጎች" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው ክልል አቀፍ የቴክኖሎጂ፣ የክህሎትና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር በወላይታ ሶዶ እና በአርባ ምንጭ ከተሞች እየተካሄደ ነው። በወላይታ ሶዶ ከተማ በተጀመረው ውድድር ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የውድድሩ ተሳታፊዎች እንደገለጹት የውድድሩ መዘጋጀት በኮሌጆች ያገኙትን የንድፈ ሀሳብ ዕውቀት ወደ ተግባር ለመቀየርና ልምድ በማዳበር የበለጠ ለመስራት የሚያግዛቸው ነው።   በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚሰጡ ስልጠናዎች ከቴክኖሎጂ ጋር በመላመድና ምርታማ በመሆን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮቻችን በራስ አቅም መፍታት የሚያስችሉ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።   ከሳውላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤትን ይዞ የቀረበው ተወዳዳሪ ተመስገን አዝማች ክልላዊ ውድድር መዘጋጀቱ በኮሌጅ ያገኘነውን የንድፈ ሀሳብ ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ይበልጥ ተጠቃሚ እንድንሆን ያስችለናል ብሏል። በቴክኖሎጂ በመታገዝ ተኪ ምርቶችን በስፋት በማምረት የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑንም ነው የተናገረው። ውድድሩ ከጠባቂነት አስተሳሰብ ወጥቶ በራስ ጥረት ሠርቶ ለመለወጥ የሚያነሳሳ ነው ያለችው ደግሞ ከዲላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በምግብ አዘገጃጀት ክህሎት የተወዳደረችው ፍጹም ዮሐንስ ናት። ውድድሩ ልምድ በመለዋወጥና ክፍተቶቻችንን በማረም በቀጣይ ምርታማ ለመሆን ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብላለች።   የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትልና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ዘርፍ ሃላፊ አቶ በዛብህ ገበየሁ በበኩላቸው እንዳሉት የውድድሩ መዘጋጀት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ ነው። በቢሮው ስር ባሉ ኮሌጆች የሚሰጠው ተግባር ተኮር ትምህርትና ስልጠና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሚተኩ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። ከቴክኖሎጂ ማዕከላት የፈጠራ ሀሳቦችንና ቴክኖሎጂዎችን በመሰብሰብ ሰልጣኞች ስልጠናቸውን ሲጨርሱ በተናጠልም ሆነ በጋራ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ቴክኖሎጂዎችና የፈጠራ ሀሳቦች የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በመሰረታዊነት እንዲፈቱ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱንም ነው የገለጹት። ለአራት ቀናት በሚካሄደው ክልል አቀፍ ውድድር በክህሎት ዘርፍ በ20 ሙያዎች፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ደግሞ በ14 ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም በ6 ተግባራዊ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ውድድሩ እንደሚካሄድ ታውቋል። በውድድሩ የተለያዩ አሰልጣኝ መምህራን፣ ሰልጣኞችና ኢንተርፕራይዞች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በክልሉ ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል
Apr 23, 2025 110
ሶዶ፤ሚያዚያ14/2017(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ገለጸ። በቢሮው አዘጋጅነት ክልል አቀፍ የቴክኖሎጂ፣የክህሎት እና ተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር ከነገ ጀምሮ ለአራት ቀናት በሶዶ እና አርባ ምንጭ ከተሞች እንደሚካሄድ ተመላክቷል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ በዛብህ ገበየሁ ክልል አቀፍ ውድድሩን በማስመልከት በሶዶ ከተማ መግለጫ ሰጥተዋል። አቶ በዛብህ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ በክልሉ ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። ለዚህም በተለይ በመካከለኛ ደረጃ ብቁ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ይህም የኢ-ፍትሃዊነት ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎችን ለማሳለጥ ያግዛል ብለዋል። በሶዶ እና አርባ ምንጭ ከተሞች የሚካሄደው የቴክኖሎጂ፣የክህሎት እና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር ዓላማ ሠልጣኞች ያገኙትን ዕውቀት ወደ ኢንተርፕራይዝ ለማሽጋገር ታስቦ መሆኑንም ጠቁመዋል። በቴክኖሎጂም የማህበረሰቡን ችግር ከመፍታት ባለፈ ተቋማት ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳትና በማባዛት ሀብት እንዲያመነጩ ታስቦ መዘጋጀቱን አስረድተዋል። የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድርም ጥናታዊ ሥራዎች በመደርደሪያ የሚቀመጡ ሳይሆን ቴክኖሎጂ፣ ምርት እና አገልግሎት ሆነው እንዲወጡ ነው ብለዋል። ለአራት ቀናት በሚቆየው ክልል አቀፍ ውድድር በክህሎት ዘርፍ በ20 ሙያዎች፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ደግሞ በ14 ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም በስድስት የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ውድድር ይካሄዳል ብለዋል። በውድድሩም የተለያዩ አሠልጣኝ መምህራን፣ ሠልጣኞችና ኢንተርፕራይዞች እንደሚሳተፉም ነው አቶ በዛብህ ያስታወቁት። በክልል ደረጃ የተዘጋጀውን ውድድር የሚያሸንፉት ተወዳዳሪዎችም በቀጣይ ክልሉን በመወከል በፌዴራል ደረጃ በሚካሄድ ውደድርም እንደሚሳተፉ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም