በክልሉ ወጣቶች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት እንዲያበለጽጉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ደሴ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ወጣቶች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት እንዲያበለጽጉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

9ኛው የክልሉ የቴክኖሎጂ፣ የክህሎት፣ የተግባራዊ ጥናትና ምርምር እና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የንግድ ትርዒት እና የደረጃ ሽግግር ሳምንት በኮምቦልቻ ከተማ ተከፍቷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት ለወጣቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት በቴክኖሎጂ፣ በስልጠናና በክህሎት ዳብረው ሥራ ፈጣሪ መሆን እንዲችሉ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን በማበረታታት የክልሉን ኢኮኖሚ የበለጠ ለማነቃቃት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ወደ ባለሃብትነት ሲሸጋገሩም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።

በተለይም ወጣቶች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት እንዲያበለጽጉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።


 

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፋሪሃት ካሚል በበኩላቸው በቴክኖሎጂ የበለጸገ ትውልድ በመፍጠር ለዜጎች የተሻለ የሥራ እድል ለማመቻቸት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም የወጣቶችን የፈጠራ ሥራ በማበረታታትና በማጎልበት በኢኮኖሚ እራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ለሀገርና ለዓለም መትረፍ እንዲችሉ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ወጣቶች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው በመስራት ከአነስተኛ ወደ ባለሃብትነት እንዲሸጋገሩ ለማድረግም የማሰልጠን፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ የማመቻቸት ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

ዛሬ በአማራ ክልል የተመለከትነው የፈጠራ ሥራ፣ የቴክኖሎጂ ውጤትና የወጣቶች ተነሳሽነት የሚበረታታና የሚደነቅ በመሆኑ የበለጠ ማደግ እንዲችል ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ስቡህ ገበያው(ዶ/ር) በበኩላቸው ወጣቶችን በቴክኖሎጂ በማገዝ ክህሎታቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሚቆየው የንግድ ትርኢትና የደረጃ ሽግግር ሳምንት በቴክኖሎጂው ዘርፍ 345 አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ታዳጊና መካከለኛ ባለሀብትነት የሽግግር መርሃግብር መኖሩን ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) እና በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን መሀመድ(ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም