አካባቢ ጥበቃ
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሀገር በቀል ችግኞች ትኩረት ተሰጥቷል
Apr 27, 2025 59
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ ዘንድሮ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሀገር በቀል ችግኞች ትኩረት ተሰጥቶ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል። በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዩኒት ክፍል አስተባባሪና የአረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ መርሃ-ግብር ቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በቂ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። በዚህም ዘንድሮ በሚካሄደው ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። አስተባባሪው እንዳሉት በበጋው ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተሰራባቸው፣ የተራቆቱና ሌሎች ለተከላ ዝግጁ በሆኑ ቦታዎች የችግኝ ተከላ እንደሚከናወን ተናግረዋል።   በተጨማሪም ከፌደራል አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ፈፃሚ አብይ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች ወደ ተለያዩ ክልሎች በመሄድ የመትከያ ቦታዎችንና የችግኝ ዝግጅቱን እየተመለከቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። በዘንድሮ ዓመት ለችግኝ ተከላ ከሚለየው መሬት 50 በመቶ ለሚሆነው ካርታ እንደሚዘጋጅለትም ገልጸዋል። በመርሃ-ግብሩ የፍራፍሬ እና የደን ችግኞችን ለተከላ በማዘጋጀት ቅድመ -ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ ሂደት በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል።   ለችግኝ ዝግጅት በርካታ የችግኝ ጣቢያዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ገልፀው፤ በዚህም ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ነው አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር) ያነሱት። ለመርሃ ግብሩ የተሻለ እና ውጤታማ የሆነ የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል። በዚህም በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ካለፉት አመታት በተለየ ሁኔታ ለሀገር በቀል ችግኞች ትኩረት ተደርጎ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ የበጋ ወራት የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከ136 ሺህ ሄከታር በላይ መሬት ላይ ተከናውኗል
Apr 25, 2025 119
ሀዋሳ ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል በበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ አፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከ136 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ መከናወኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ የበጋ ወቅት የተፋሰስ ስራ መዝጊያ መርሃ ግብር ተካሂዷል። በዚሁ ወቅት የቢሮው ሀላፊ አቶ መምሩ ሞኬ እንዳሉት በክልሉ በበጋ ወቅት የተፋሰስ ልማት ስራ በህዝብ ተሳትፎ ከ136 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ላይ ተከናውኗል። ለአንድ ወር የተከናወነው የተፋሰስ ልማት የመሬት ለምነትን በመመለስ ምርታመነትን ለመጨመር ማለሙን ተናግረዋል። በተለይም የመሬት መሸርሸርን ለመከላከል ለጠረጴዛ እርከን ስራ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል። በቀጣይ የተፋሰስ ልማት በተሰራባቸው አካባቢዎች በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የምግብና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ከ307 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ይተከላሉ ብለዋል። በደጋማ አካባቢዎች በለሙ ተፋሰሶች ከ85 ሺህ በላይ የአፕል ችግኝ እንደሚተከል ጠቅሰው ከዚህ ጎን ለጎን ባህር ዛፍን በማንሳት በሌላ የመተካት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በአጠቃላይ ቀደም ሲል የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የውሃ ምንጮች እንዲጎለብቱና የአፈር ለምነት እንዲመለስ እንዲሁም የደን ሽፋን እንዲጨምር በማድረግ ለምርትና ምርታማነት ማሳደግ ማገዙን ጠቁመዋል።   የቢሮው ምክትል ሃላፊና የተፈጥሮ ሀብትና መሬት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፍቅረኢየሱስ አሸናፊ በበኩላቸው በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ክልሉ ካለው ተዳፋታማ የመሬት አቀማመጥ አንጻር የሚስተዋለውን የአፈር መሸርሸር በዘላቂነት ለመከላከል ወሳኝ የሆነውን ጠረጴዛማ እርከን ትኩረት ተሰጥቶ መከናወኑን ጠቅሰዋል። በዚህም 8 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር በላይ መፈጸሙን ገልጸው በእነዚህ ቦታዎች በቀጣይ በስነህይወታዊ ስራዎች የመሸፈን ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል። በክልሉ ሀገረ ሰላም ወረዳ ሀለቃ ቀበሌ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ሁኔታ በጎርፍ የሚጠቃ መሆኑን የሚገልጹት አርሶ አደር ፋንታዬ ቡጡነ ጠረጴዛማ እርከን በመስራት ከዚህ ቀደም በዝናብ ወቅት ይደርስባቸው የነበረውን መሸርሸር አስቀርቷል ብለዋል።   የዳራ ኡቲልቾ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጸጋዬ ዳንሳሙ መሬታቸው ተዳፋታማና የዘሩት ሳይቀር በጎርፍ እየተጠረገ ለከፋ ችግር ሲዳረጉ እንደነበረ አስታውሰው በዘንድሮ የተፋሰስ ጠረጴዛማ እርከን በመስራት ችግሩን መከላከል መቻላቸውን ተናግረዋል ።  
ሁለተኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከሰኔ ወር ጀምሮ ይካሄዳል - ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ
Apr 25, 2025 144
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፡-ሁለተኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጽዳትና የአካባቢ ጥበቃ ስራን ባህል ማድረግ በሚያስችል መልኩ ከመጪው ሰኔ ወር ጀምሮ ለስድስት ወራት እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚያዚያ 18/2016 ዓ.ም ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ያለመ "የጽዱ ኢትዮጵያ" ንቅናቄን በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል። በንቅናቄው በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የከተማ ጽዳትና ውበት የገቢ ማሰባሰቢያ ጨምሮ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ተካሂደዋል። የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ÷ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተተገበሩ የአረንጓዴ አሻራና የኮሪደር ልማት መርሃ ግብሮች ለአካባቢ ጥበቃና ጽዱ ኢትዮጵያ ገንቢ ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል። የመጀመሪያው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄም የፕላስቲክ፣የአየር፣ የውሃ፣የአፈርና የድምጽ ብክለትን መከላከል እንዲሁም የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ ሰነዶች ግምገማ መድረክ መካሄዱን አስታውሰዋል። በዚህም ዜጎች ጽዳትና የአካባቢ ጥበቃ ስራን ባህል እንዲያደርጉ ግንዛቤ የተፈጠረበት ነው ብለዋል። በተጨማሪም በጽዳትና በአካባቢ ጥበቃ አሰራር ሥርዓት ላይ የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶችን በመፈተሽ የማሻሻልና ተፈፃሚ የማድረግ አቅምን ማጎልበቱን ተናግረዋል። በመጀመሪያው ዙር ጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የመንግስት፣ የኃይማኖትና የግል ተቋማትን ጨምሮ ከ7 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በዚህም ብክለትን የመከላከልና የአካባቢን ንጽህና የመጠበቅ ጉዳይ ቁልፍ አጀንዳ መሆኑን መግባባት በመፍጠር ወደ ትግበራ የተገባበት ነው ብለዋል። ሁለተኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ መርሃ ግብርን "ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን" ጋር በማስተሳሰር ከመጪው ሰኔ ወር ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ወራት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። በዚህም በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በግንዛቤ ፈጠራ፣ በሕግ ተከባሪነትና ለአካባቢ ደህንነት ጥሩ የሰሩ የሚመሰገኑበት መርሐግብር ይካሄዳል ብለዋል። መርሃ ግብሩን ስኬታማ ለማድረግ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን (ኢዜአ) ጨምሮ ከሌሎች መገናኛ ብዙኃንና ኢንዱስትሪዎች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ንቅናቄው የኤሌክትሮኒክስ፣የአደገኛ ኬሚካልና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ የውሃና የአፈር፣ የአየርና የድምጽ ብክለት መከላከል ሥራ የሚከወንበት እንዲሁም የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ የሚደረግበት መሆኑን አስረድተዋል። በገፅ ለገፅ መርሐ ግብሮች 15 ሚሊዮን ዜጎችን በማሳተፍ ጽዳትና የአካባቢ ጥበቃን ባህል ያደረገ ትውልድ ለመገንባት እንደሚሠራም ተናግረዋል። የችግኝ ተከላ እና መንከባከብ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሥራዎች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል።
በምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከል ችግኝ ዝግጅት እየተከናወነ ነው
Apr 25, 2025 85
ነቀምቴ/ ጭሮ፥ሚያዝያ 17/2017 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞን በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ የተለያየ ዝሪያ ያለው ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን የዞኖቹ ግብርና ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ። የምስራቅ ወለጋ ዞን የግብርና ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አስፋው ሀምቢሳ እንደገለጹት፥ በዞኑ በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 544 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው። ባለፉት ዓመታት በተተከሉ ችግኞች ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፥ በዚህ አመትም የበለጠ ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል። በፅህፈት ቤቱ የተፋሰስ እና የደን ልማት የስራ ሂደት ሀላፊ አቶ ደሳለኝ በልዓታ፤ በዞኑ በዘንድሮው የክረምት መርሃ ግብር የሚተከሉ የደን፣ የእንስሳት መኖ፣ የፍራፍሬና ሌሎች የችግኝ ዘሮች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። በተመሳሳይ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ዋሴ በቀለ በበኩላቸው፥ ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ካለፉት አመታት በተሻለ መልኩ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በዞኑ በዘንድሮው የሚተከሉ ከ413 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ችግኝ አይነቶች እየተዘጋጁ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ከ82 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት እንደ ጊሽጣ፤ አቮካዶ፤ ዘይቱን፤ ማንጎና የመሳሰሉ የፍራፍሬ ችግኞች እንደሆኑ ገልጸዋል። ዘንድሮ ለመትከል የታቀደው የፍራፍሬ ዛፍ አይነቶች ቁጥር ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ከ20 ሚሊዮን በላይ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል፡፡ በዞኑ በየአመቱ እየተተከሉ ያሉት የፍራፍሬ ችግኞች የአርሶ አደሮችን ገቢ በማሳደግና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ አስተዋጽዎ እያበረከቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በጋምቤላ ክልል የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች የክረምት ቅድመ ጥንቃቄና የዝግጅት ስራዎች ተጀምረዋል
Apr 24, 2025 117
ጋምቤላ ፤ ሚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች የክረምት ቅድመ ጥንቃቄና የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የክረምት ወራት የአደጋ ምላሽ እቅድ ማዘጋጀቱን ገልጿል። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጃክ ጆሴፍ ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ ዝቅተኛና ትላልቅ ወንዞች አቋርጠው የሚያልፉበት በመሆኑ በክረምት ወራት የጎርፍ ተጋላጭነቱ ከፍተኛ ነው። በተለይም ባሮን ጨምሮ ክልሉን አቋርጠው የሚያልፉ አራት ትላልቅ ወንዞች ከደጋና በአካባቢ በሚጥለው ዝናብ ሞልተው በመፍሰስ በወንዞች አካባቢ የሚኖሩ በርካታ ዜጎችን እንደሚያፈናቅል ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ይህን ታሳቢ በማድረግ ከክልሉ እስከ ወረዳ የጎርፍ መከላከል ግብረ ሃይል አደረጃጀቶችን በመፍጠር በተጋላጭ አካባቢዎች የቅደመ ጥንቃቄና የዝግጅት ስራዎች ከወዲሁ መጀመራቸውን ገልጸዋል። በገጠር ወረዳዎች አካባቢ ውሃ ሰብሮ በሚገባባቸው ቦታዎች በአፈር የመገደብ እንዲሁም ጋምቤላን ጨምሮ በከተሞች በቆሻሻ የተሞሉ የውሃ ማፋሰሻ ቦዮችን የማጽዳት ስራ የእተከወነ ነው ብለዋል። የጎርፍ አደጋ የሚከሰትበት ጊዜ ከመቃረቡ ጋር ተያይዞ የጤና፣ የውሃ፣ የትምህርትና ሌሎች የልማት ዘርፍ መስሪያ ቤቶች የተካተቱበት የጋራ አደጋ ምላሽ እቅድ መዘጋጀቱንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። የጋምቤላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ጀምስ ፖል በበኩላቸው የጋምቤላ ከተማ በክረምት ወራት በአካባቢው በሚጥላው ዝናብና የባሮ ወንዝ በሚሞላበት ወቅት ለጎርፍ አደጋ ይጋለጣል ብለዋል። ማዘጋጃ ቤቱ ይህን ታሳቢ በማድረግ የክረምቱ ወራት ከመግባቱ በፊት የውሃ ማፋሰሻ ቦዮች ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የማጽዳትና ተጨማሪ የውሃ ማፋሰሻ ቦዮችን የመገንባት ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። በክልሉ ጋምቤላ ከተማንና ኢታንግ ልዩ ወረዳን ጨምሮ በኑዌርና በአኝዋሃ ዞኖች የሚገኙ ወረዳዎች የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች እንደሆኑ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በአማራ ክልል 207 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው - የክልሉ ግብርና ቢሮ
Apr 24, 2025 87
ባህር ዳር፤ ሚያዚያ 16/2017(ኢዜአ):- በአማራ ክልል በመጪው ክረምት በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 207 ሺህ ሄክታር የተጎዳ መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። ባለፈው ዓመት ክረምት በክልሉ ከተተከለው ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ችግኝ በመጀመሪያው ዙር በተካሄደ ቆጠራ 85 በመቶ መፅደቁም ተመልክቷል።   በግብርና ቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የተጎዳ መሬትን በደን ለመሸፈን ጥረት እየተደረገ ነው። እስካሁን በተደረገ ጥረትም በመንግስት፣ በግል፣ በማህበራትና በተቋማት አማካኝነት የችግኝ ዝግጅቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል። በሚከናወነው የችግኝ ተከላ በክልሉ አሁን ያለውን 16 ነጥብ 3 በመቶ የደን ሽፋን ወደ 17 ነጥብ 3 በመቶ ለማሳደግ ታሳቢ መደረጉንም አብራርተዋል።              
በቀጣዮቹ ቀናት በኢትዮጵያ፣ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች ሞቃታማ የአየር ሁኔታ ይጠበቃል
Apr 22, 2025 141
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 14/2017(ኢዜአ):-በቀጣዮቹ ቀናት በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ ኬንያ ከመደበኛው በላይ የሙቀት መጠን የሚመዘገብ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት (ኢክፓክ) አስታውቋል። የኢክፓክ የአየር ትንበያ መረጃ እንደሚያመለክተው በሱዳን በርካታ አካባቢዎች በኢትዮጵያ በተለይም የአፋር ክልል በቀጣዮቹ ስምንት ቀናት ከፍተኛ የሙቀት መጠን ሊመዘገብ የሚችል መሆኑን ጠቁሟል። በደቡብ ሱዳንና ኤርትራ እንዲሁም በሰሜን፣ምእራብና ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ደግሞ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ሙቀት የሚኖር ይሆናል። በጅቡቲ፣ሶማሊያ፣ዩጋንዳ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ በተመሳሳይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ሙቀት ሊመዘገብ ይችላል የሚል የትንበያ መረጃ አስነብቧል። በአብዛኛው የኤርትራ ክፍል፣በጅቡቲ፣ታንዛኒያ፣ኢትዮጵያ፣ኡጋንዳ፣ ምእራባዊ የኬንያ ክፍል፣ በማእከላዊና ሰሜን የሶማሊያ ግዛቶች ከመደበኛው ባላይ ሙቀት እንደሚኖራቸው ተመላክቷል። በኢትዮጵያ ምእራባዊ የሀገሪቱ ክፍሎች፣በሩዋንዳ፣ብሩንዲ፣በሰሜንና ደቡባዊ ታንዛንያ፣በኡጋንዳ ምእራባዊ ክፍል እንዲሁም በኬንያ ጠረፋማ አካባቢዎች መጠነኛ ዝናብ እንደሚኖርም ይጠበቃል። የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት (ICPAC) የአየር ትንበያና ሌሎች ተያያዥ ወቅታዊ ክስተቶችን በመተንበይና በመተንተን የቅድመ ጥንቃቄ መልእክቶችን በማጋራት ይታወቃል።
በመጪዎቹ አሥር ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛዎቹ የበልግ ተጠቃሚ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀጣይነት ይኖራቸዋል -የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት
Apr 22, 2025 131
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 14/2017(ኢዜአ)፡-በመጪዎቹ አሥር ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛዎቹ የበልግ ተጠቃሚ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ቀጣይነት እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት አስታወቀ። ኢኒስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በደቡብ፣ደቡብ ምዕራብ፣ምዕራብ፣በምስራቅ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይኖራቸዋል። በዚህም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎችን የሚሸፍን ቀላል መጠን ያለው ዝናብ የሚያገኙ ሲሆን በውሃ አካላትና በከባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ኢኒስቲትዩቱ በትንበያው ይፋ አድርጓል። ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎችን ጨምሮ የደቡብ ምዕራብ እና የምዕራብ እንዲሁም የሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ቦታዎችን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም ኢኒስቲትዩቱ ገልጿል። አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በደቡብ፣ደቡብ ምስራቅ፣ እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚጠቁሙም አስታውቋል። በኤፕሪል የሶስተኛው አሥር ቀናት ከሚኖረው ከፍተኛ የጸሀይ ኃይል ጋር በተያያዘ በተለይም በጋምቤላ፣በአፋር፣በሶማሌ ፣ቤንሻንጉል -ጉሙዝና በምዕራብ አማራ አካባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ35 እንዲሁም በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ ከ40 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሚሆን የኢኒስቲትዩቱ ትንበያ መረጃ ያመለክታል።    
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጋራ አመራር እና አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
Apr 18, 2025 261
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጋራ አመራር እና አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) “ዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የ2025 ፒ4ጂ ቬይትናም ጉባኤ ተሳትፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል እና ይህን ጠቃሚ ጉባኤ ላዘጋጀው የቬይትናም መንግስት ምስጋና በማቅረብ በአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።   የ2025 ፒ4ጂ ጉባዔ የአረንጓዴ ልማት እድገትን ለማፋጠን፣ አዳዲስ አጋርነቶችን ለማጎልበት እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚደረገው የጋራ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። ባለፉት ጥቂት ቀናት የአንድነትና የብዝሃነት ሃይል ማሳካት የሚችለውን አቅም አይተናል ብለዋል። የተቀናጁ የፒ4ጂ ፕሮጀክቶች ትርጉም ያለው ውጤት የሚያስገኙና ይህን ለማሳደግም ትልቅ አቅም ያላቸው መሆናቸውን አመልክተዋል። ኢትዮጵያ በ2027 የሚካሄደውን አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ ለማዘጋጀት ችቦውን በመረከቧ ኩራት እንደሚሰማት ገልጸዋል። ይኽን እድል በፅናት እና በቁርጠኝነት በመያዝ የቬይትናም፣ ኮሎምቢያ፣ ዴንማርክ እና የኮሪያ ሪፐብሊክን ስኬታማ የዝግጅት ውርስ ጨምረን እናስቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል። ጉባኤው ትብብር፣ ፈጠራ፣ አካታችነት እና ተግባር በተሰኙት የፒ4ጂ አስኳል መርሆዎች እየተመራ እንደሚካሄድም አመልክተዋል።   የኢትዮጵያ 2027 ጉባኤ በአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ልማት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና እንዲሁም ወጣቶችንና ሴቶችን ማብቃትን የአረንጓዴ ሽግግር ወሳኝ መሳሪያ የማድረግ አስፈላጊነትን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት ተርታ መሆኗን አመልክተው፤ ይህንን ለመፍታት የተግባር ቁርጠኝነቷን እያሳየች ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ከአጀንዳ 2030 እና ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር በተጣጣመ መልኩ እ.አ.አ በ2050 ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ስርዓት እውን የማድረግ ትልቅ ትልም ማዘጋጀቷን ተናግረዋል። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እና እየተስፋፋ ያለው የታዳሽ ሃይል ልማት ለዚህ ራዕይ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል። ይሁን እንጂ የትኛውም ሀገር የአየር ንብረት ቀውስን ብቻውን መቋቋም እንደማይችል አመላክተዋል። ይህንን ችግር የመፍቻ መንገዱ የጋራ አመራር እና አስቸኳይ እርምጃን የሚጠይቅ መሆኑንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የፒ4ጂ በ2018 ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለመድረኩ አስተዋፅዖ ማበርከቷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።   በምግብ ሥርዓት፣ በታዳሽ ኃይል፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገሩ ከተሞች እና በኢኮኖሚ ውስጥ ባሉ የትብብር ፕሮጀክቶች አብረን ስንሠራ የሚቻለውን አይተናል ሲሉም ተናግረዋል። እንደ ፒ4ጂ መስራች አባልነቷ፥ ቁልፍ የአየር ንብረት ስምምነቶች፣ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ማገገምን እና ዘላቂ ልማትን ለማራመድ ቁርጠኝነቷን እንደምታስቀጥልም ነው ያስረዱት። በዚህ አውድም፥ በቬይትናም መንግስት የቀረበውን የሃኖይ ዲክላሬሽን ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል። የቬይትናም መንግስት ይህንን ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ በማዘጋጀቱ፣ ለአረንጓዴና የበለጠ አካታች ዓለም ላበረከቱት አስተዋፅዖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። ቀደምት የሰው ዘርና የቡና መገኛዋን እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በዓለም ትልቁ የደን ልማት መርሃ ግብር እየተገበረች ያለችውን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመረጠች
Apr 17, 2025 223
አዲስ አበባ ፤ሚያዝያ 9/2017 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ እንደምታስተናግድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥የሀኖይ ጉባኤ አነስተኛ ቢሆኑም በሚገባ የተቀናጁ የፒ4ጂ ፕሮጀክቶች ትርጉም ያለው ውጤት እንደሚያስገኙ እና ለማሳደግም ትልቅ አቅም ያላቸው መሆናቸውን ማሳየቱን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።   ኢትዮጵያ በ2027 የሚካሄደውን አምስተኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ ለማዘጋጀት ችቦውን በመረከቧ ኩራት ይሰማታል ብለዋል። ይኽን እድል በፅናት እና በቁርጠኝነት በመያዝ የቬይትናም፣ ኮሎምቢያ፣ ዴንማርክ እና የኮሪያ ሪፐብሊክን የታየውን ስኬታማ የዝግጅት ውርስ ጨምረን እናስቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል። ጉባኤው ትብብር፣ ፈጠራ፣ አካታችነት እና ተግባር በተሰኙት የፒ4ጂ አስኳል መርሆዎች እየተመራ እንደሚካሄድ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ 2027 ጉባኤ በአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ልማት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና ብሎም ወጣቶችን እና ሴቶችን ማብቃትን የአረንጓዴ ሽግግር ወሳኝ አስፈፃሚ የማድረግ አስፈላጊነትን ትኩረት ሰጥቶ ይዘጋጃልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ ይካሄዳል
Apr 17, 2025 179
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ)፡-70ኛው አፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም(GHACOF 70) ግንቦት 11 እና 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ፎረሙ የሚካሄደው “የአየር ንብረት አገልግሎት፤ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አቅምን በጋራ ማጠናከር ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል(ICPAC) ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ፎረሙን እንዳዘጋጀ ተገልጿል። እ.አ.አ ከማርች እስከ ሜይ 2025 ያለው የአየር ንብረት ትንበያ አፈጻጸም ውይይት እንደሚደረግበት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በፎረሙ እ.አ.አ ከጁን እስከ ሴፕቴምበር 2025 ያለው ቀጣናዊ የአየር ትንበያ ይፋ እንደሚደረግ አመልክቷል። የአየር ንብረት ትንበያ እና አስተዳደር ስትራቴጂዎች ፋይዳ የተመለከተ ውይይትም ይደረጋል። በፎረሙ ላይ የኢጋድ አባል ሀገራት፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት አጋሮችንና የዘርፉ ተዋንያንን ይሳተፋሉ። ከዋናው ፎረም አስቀድሞ የአየር ንብረት ትንበያ እና ተጓዳኝ አውደ ጥናቶች እንደሚካሄዱ ኢጋድ አስታውቋል። 69ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በጥር ወር 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ የሚታወስ ነው።
የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮች ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው-  አምባሳደር ፍስሃ ሻውል 
Apr 16, 2025 290
አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ):- መንግስት የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮች ተቋማዊ መዋቅር እንዲኖራቸው ለማድረግ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻውል ገለጹ። ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ ከኢስት አፍሪካ የማዕድን ኩባንያ እና ሙገር ሲሚንቶ ኩባንያ የተወጣጣ የከፍተኛ አመራር ልዑካን ቡድን ለጉብኝት ህንድ ኒው ዴልሂ ይገኛል።   የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት አላማ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ኢኒሼቲቮች ልምድ ለመለዋወጥ እና የእውቀት ሽግግር ለማድረግ ነው። ልዑኩ በቆይታው በህንድ ያለው የኢንዱስትሪ አሰራሮችን እንደሚጎበኝ በኒው ዴልሂ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል። ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት እና የአረንጓዴ ኢነርጂ ትራንስፎርሜሽን ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል። በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል ከልዑኩ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ከካርቦን ነጻ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት የያዘቻቸውን ግቦች አንስተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የአረንጓዴ ኢነርጂ ኢኒሼቲቮች ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል። የከፍተኛ ልዑካን ቡድኑ ጉብኝት እ.አ.አ በ2019 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ይፋ የሆነው “Leadership Group for Industry Transition” የተሰኘው የመንግስት እና የግል አጋርነት ኢኒሼቲቭ አካል ነው። ኢኒሼቲቩ በህንድ እና ስዊድን መንግስታት የጋራ ሊቀመንበርነት የሚመራ ሲሆን የኢንዱስትሪ ሽግግራቸው ዘላቂነትን የሚከተል ማዕቀፍ ያላቸው አባል ሀገራት የያዘ ነው። ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በኢኒሼቲቩ አባል የሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መሆናቸውን በኒው ዴልሂ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ የተፋሰስ ልማት ስራ በግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ ውጤት አምጥቷል
Apr 15, 2025 170
አዳማ፤ሚያዝያ 7/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የተፋሰስ ልማት ስራ የአካባቢውን ስነ ምህዳር ከማስጠበቅ ባለፈ በግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ከድር ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ ከጥር 15/2017 ዓም ጀምሮ እየተከናወነ ነው።   በህዝቡ ንቅናቄ የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ስራ ሳይንሳዊ አሰራርን ተከትሎ እንዲከናወን ከክልሉ ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች ድጋፍና ክትትል ሲያደርጉ ነበር ብለዋል። በክልሉ 6 ሺህ 400 ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚሸፍን የተፋሰስ ልማት ስራ ለ60 ቀናት በህዝብ ንቅናቄ መከናወኑንም ገልጸዋል። በዚህም በርካታ የክልሉ ህዝብ መሳተፉን የገለፁት አቶ ኤሊያስ፤ ''የአካባቢውን ስነ ምህዳር ጠብቀን ለትውልድ ለማስተላለፍ መሰረታዊ ስራዎች እየተሰራ ነው'' ብለዋል። በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች ደርቀው የነበሩ የሀሮማያና ጨርጨርቅ ሐይቅን ጨምሮ ወንዞችና ዥረቶች የተመለሱ ሲሆን አሁን ላይ ለመስኖ ልማት አገልግሎት እየዋሉ ይገኛሉ ብለዋል። እንዲሁም በተፋሰስ ልማቱ በቡና፤ በፍራፍሬ፤ በደን ልማት፤ በሰብል ልማትና በስነ ምህዳር ጥበቃ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ሲሉም ገልጸዋል። ''በተመሳሳይም የአየር ጠባይ ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋምና ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ በተሰራው የተፋሰስ ልማት ስራ የአፈር መሸርሸርና መከላት መቀነስ ችለናል'' ብለዋል። በዘርፉ ለወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል አማራጭ መሆኑን የገለፁት ምክትል ሃላፊው በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ፤ በእንስሳት መኖ፤ በንብ ማነብና ማር ልማት፤ በእንስሳት እርባታና ማድለብ በባለቤትነት ተረክበው እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል። በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ ከ670 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከንኪኪ ነፃ ተደርጎ እንዲያገግም እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።    
በጉጂ ዞን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመጪው ክረምት ተከላ ተዘጋጅተዋል
Apr 14, 2025 182
አዶላ፤ ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ)፦ በጉጂ ዞን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመጪው ክረምት ተከላ መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ቡድን መሪ አቶ ወንዶ ሸርቦቴ እንዳሉት እስካሁን በዞኑ 13 ወረዳዎች በተካሄደው ስራ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡   በዞኑ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል የፍራፍሬ፣ የደን፣ የጥላ ዛፍ፣ የእንስሳት መኖና የቡና ችግኝ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ሃላፊው እንዳሉት ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚውሉ በዋናነት የቡና፣ አቦጋዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ ዘይቱን የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ለደንነት ደግሞ የሀበሻ ጽድ፣ ዋንዛና ኮሶ፣ በብዛት ቀዳሚዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡ ከነዚህም ሌላ የውበት የጥላ ዛፍና የእንስሳት መኖ የመሳሰሉት በችግኝ ዝግጅቱ ውስጥ የተካተቱ እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ የተራቆተን ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ የችግኝ መትከያ መሬት እየተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተከላ ስራው በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከ184 ሺህ በላይ የሚገመት የዞኑ ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል፡፡   በዞኑ አዶላ ወረዳ የደራርቱ ቀበሌ ነዋሪና አባገዳ ኦዳ ጎበና አንድ ዛፍ ሲቆረጥ 10 ችግኝ መትከል የተለመደው የገዳ ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ በአከባቢ መራቆትና በደኖች መመናመን ባለፉት ዓመታት በአከባቢያችን ከተከሰተው ድርቅ ብዙ ነገር ተምረናል ያሉት አባ ገዳው፤ ይኸንን ለመቀልበስ የሚያስችሉ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሥራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።፡ ችግኝ ማዘጋጀትና መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማሳደግም ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እያስተማሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የዚሁ ወረዳና ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ጎበና ዱከሌ ችግኝ ተክሎና ተንከባክቦ ማሳደግ ከማንም በላይ የእኛ የወጣቶች ድርሻ ነው ብሏል፡፡ አከባቢን መንከባከብ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ባለፉት ዓመታት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ከተከናወኑ የልማት ስራዎች ትምህርት መወሰዱን ያስታውሳል፡፡
ከሞጆና ሉሜ አካባቢዎች የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራዎች የልምድ ልውውጥ ተደረገ
Apr 12, 2025 218
አዳማ ፤ ሚያዝያ 4/2017(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ሸዋ ዞን ሞጆና ሉሜ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራዎች የልምድ ልውውጥ መረሐ ግብር ተካሄደ። ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተወጣጡ የግብርና ዘርፍ አመራር አባላት በምስራቅ ሸዋ ዞን የችግኝ ጣቢያዎችና አቮካዶ ክላስተር እንቅስቃሴን በሞጆና ሉሜ አካባቢዎች ተገኝተው ተመልክተዋል።   በዘህ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐረር ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ በሰጡት አስተያየት፤ በሞጆ ያየነው የችግኝ ጣቢያ የተደራጀና የተቀናጀ ሳይት ነው ብለዋል።   በጣቢያው ከሚከናወነው የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራ በተለይ የአቮካዶ ልማት፣ንብ ማነብና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት በአንድ ማዕከል እየተከናወነ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል። በዚህም መልካም ተሞክሮና ልምድ ያገኙበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ተሞክሮ ወደ ክልላችን ወስደን እንስፋፋለን ሲሉም ገልጸዋል።   በአፋር ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የባዮ ዳይቨርሲቲ ዳይሬክተር አቶ አሊ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ከሞጆና ሉሜ አካባቢዎች የችግኝ ዝግጅትና የተቀናጀ የግብርና ሥራ ልምድና እውቀት ያገኘንበት ነው ብለዋል ። በተለይ በመስኖ ለምግብነትና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ችግኞችን ማዘጋጀት እንደሚቻል መረዳታቸውን ጠቅሰው፤ በክልሉ ጨዋማና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ አቮካዶን ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል። ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የመጡት አቶ በየነ በላቸው በበኩላቸው፤ የሞጆ ችግኝ ጣቢያና የአቮካዶ ክላስተር በእውቀትና ክህሎት የተዘጋጀ መሆኑን ከምልከታቸው እንደተረዱ ገልጸዋል።   በተለይ አቮካዶ ከማምረት ባለፈ የአቮካዶ ችግኝ ወደ ውጭ ለመላክ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ ክልላችን ለአቮካዶ ልማት አመቺ በመሆኑ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የአቮካዶ ዝሪያዎች ከኦሮሚያ ክልል ገዝተን የማዳቀል ስራ እየሰራን ነው ብለዋል። የሉሜ ወረዳ ምክትል አስተዳደሪና የግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ለሚ ይርኮ ፤ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መረሐ ግብር በፍራፍሬና የእንስሳት መኖ ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ሲሉ ገልጸዋል።   በዚህም ሞጆን ጨምሮ በወረዳው 150 የችግኝ ጣቢያዎች ላይ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላቸው 35 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት ለ4ኛ ጊዜ የአቮካዶ ምርት ከወረዳው በማዕከላዊ ገበያ በኩል ወደ ውጭ መላኩን ጠቁመው፤ በተጨማሪ የተሻሻሉ የአቮኮዶ ችግኞችን ወደ ውጭ ለመላክ ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።   በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን በበኩላቸው፤ የመስክ ምልከታው በመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መረሐ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ዝግጅት በመሬት ላይ ያለውን የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደተሰናዳ ገልጸዋል። በተለይ የሞጆ ችግኝ ጣቢያ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ችግኞች ዝግጅት ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ፋኖሴ ፤ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ዝግጅት 60 በመቶ የፍራፍሬ፣ የእንስሳት መኖና ለውበት የሚውሉ ሲሆን፤ 40 በመቶ ለደን ልማት ነው ብለዋል።    
በዞኑ የሚገኙትን ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ደኖች በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችል ምክክር ተካሄደ
Apr 12, 2025 143
ደብረብርሀን ፤ሚያዚያ4/ 2017(ኢዜአ)፡- በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙትን የወፍ ዋሻና የመንዝ ጓሳ ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ደኖችን በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችል የ10 ዓመት አስተዳደራዊ እቅድ ምከክር ተካሄደ። የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው የአማራ ክልል አካባቢና ደን ባለስልጣን "ዊፎረስት ኢትዮጵያ" ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው። የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ተሾመ አግማስ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ጥብቅ ደኖችን በመንከባከብና በማልማት ወደ ብሔራዊ ፓርክነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።   ጥብቅ ደኖችን ወደ ብሔራዊ ፓርክነት በማሳደግም ለዘመናት በመጠበቅና በመንከባከብ የኖረውን ማህበረሰብ ከደን ልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙትን የጣርማ በርና የወፍ ዋሻ ጥብቅ ደኖችን ወደ ብሔራዊ ፓርክነት ለማሳደግ የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል። ለዚህም የ10 ዓመት አስተዳደራዊ እቅድ በማዘጋጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ተዘጋጅቶ በዛሬው እለት ለምክክር መቅረቡን አስገንዝበዋል። ይህም በደኖቹ ውስጥ ያሉ እንስሳት፣ እጽዋትና ሌሎች ሃብቶችን ለምርምር በማዋልና የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን በመሳብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ደኖቹ የካርቦን ልቀትን በመከላከል ለአለም የሚያበረክቱትን በጎ አስተዋጽኦ በማስጠናት ከካርቦን ሽያጭ የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።   በኢትዮጵያ ደን ልማት የሬድ ፕላስ ፕሮግራሞ አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ በማስቻል የስነ ምህዳር ጥበቃው እንዲሻሻል አስችሏል ብለዋል። የዛሬው የውይይት መድረክም ጥብቅ ደኖቹን በማልማትና በመንከባከብ አገራችንን በቱሪዝም ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል። ዊ ፎረስት ኢትዮጵያ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር አክሊሉ ንጉሴ (ዶ/ር) እንዳሉት በተለይም በወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን ውስጥ ለጥናትና ምርምር የሚውሉ እድሜ ጠገብ ደኖች ይገኛሉ ብለዋል።   ከመንግስት ጋር በመተባበር እምቅ ጸጋ ያለውን ጥብቅ ደን ወደ ብሔራዊ ፓርክነት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ 10 ዓመታት ከወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን የካርቦን ሽያጭ ተጠቃሚ በመሆን የአገራችን ኢኮኖሚ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አመልክተዋል። ከ1954 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት ጥብቅ ደን ሲተዳደር የቆየው የወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን በ15 ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን 8 ሺህ 739 ሄክታር መሬትን እንደሚሸፍንም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
በ21 ሺህ ተፋሰሶች ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ተከናውኗል -ግብርና ሚኒስቴር
Apr 12, 2025 135
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 4/2017(ኢዜአ)፦በ2017 በጀት ዓመት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ እስካሁን በ21 ሺህ ተፋሰሶች ላይ የሥነ አካላዊ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መከናወኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። በዚህ ዓመት በአጠቃላይ ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተፋሰስ ልማት ለማልማት በእቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን ለኢዜአ ተናግረዋል።   ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ተፈጥሮን በመጠበቅ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል። የተፋሰስ ልማቱ የመሬት መሸርሸርን በመከላከል፣የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቋቋም እና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል። እንደ አቶ ፋኖሴ ገለጻ በተያዘው በጀት ዓመት በጥቅሉ ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሥነ አካላዊና ሥነ ህይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። የሚለማው ቦታም ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ የማድረግ ሥራ ሌላው ከተያዙ ግቦች መካከል መሆኑንም ጠቅሰዋል። እንደ ክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ ከ30 ቀናት እስከ 60 ቀናት የተቀናጀ የተፋሰስና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ እስካሁንም በበርካታ አካባቢዎች የእርከን፣ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት። በተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ 20 ሺህ 800 ተፋሰሶችን ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን ባለው አፈጻጸም ከእቅድ በላይ በ21 ሺህ ተፋሰሶች መከናወኑን ገልጸዋል። በለሙ ተፋሰሶች ላይ ከ7 ሺህ በላይ ማህበራት በእንስሳት ማድለብ፣የፍራፍሬ ተክሎችን በማልማት እና በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት በእርከን እና ውኃ ማቆር ላይ የተጀመሩ ተግባራትን ተጠናክረዋል ብለዋል። በኢትዮጵያ የተፋሰስ ልማት ሥራ ውጤታማ በሆነ መልኩ ከተሰራባቸው አካባቢዎች አንዱ ምስራቅ ሀረርጌ ዞን ነው።   በዞኑ የበደኖ ወረዳ አርሶ አደር አህመድ ነጃሺ ከዚህ በፊት ተራቁቶ የነበረው መሬት እሁን እርጥበት መያዝ በመጀመሩ ምርት በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። የተፋሰስ ልማት ሥራው አሁን ላለው ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ አካባቢን ተንከባክቦ ለማስረከብ ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ በትኩረት እየተሳተፉበት መሆኑን ጠቁመዋል። የጎሮ ጉቱ ወረዳ አርሶ አደር ኃይሌ ታደሰ በበኩላቸው በተፋሰስ ልማቱ የተለያዩ ፍራፍሬ በማምረት እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸዋል። የተፋሰስ ልማቱ በአካባቢው የነበሩ ምንጮች አገግመው በቂ ውሃ እየሰጡ ነው ብለዋል። ሌላው የወረዳው አርሶ አደር እሸቱ አሰፋ በበኩላቸው፥ በተፋሰስ ስራ ባለሙት መሬት ላይ የተለያዩ ችግኞችን በመትከል እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች ነው
Apr 11, 2025 159
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 3/2017 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በመጪው መስከረም ወር ሁለተኛውን የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። ጉባዔው የሚካሄደው ባለፈው የካቲት ወር በአዲስ አበባ በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ውሳኔን መሠረት ባደረገ መልኩ መሆኑም ተጠቁሟል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) እና የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ከአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ አካባቢ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ ጋር ተወያይተዋል። ውይይቱ በቀጣይ የአውሮፓውያኑ መስከረም 2025 አጋማሽ ላይ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የዝግጅት ሥራዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተጠቅሷል።   የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ጉባዔው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ ገልጸዋል። የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው ጉባዔው አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለመቋቋም በምታደርገው ጥረት ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ጉዳዮች አቅጣጫ ለማስያዝ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል። ስለሆነም ጉባዔው በተሳካ መልኩ እንዲከናወን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ አካባቢ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲም ኢትዮጵያ ጉባዔውን ለማዘጋጀት ያሳየችውን ቁርጠኝነት እና እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶችን አድንቀዋል። የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔው በስኬት እንዲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም የሚችልና ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ የተፋሰስ ልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው - ግብርና ሚኒስቴር
Apr 11, 2025 139
አዳማ፤ ሚያዚያ 3/2017(ኢዜአ)፦ የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም የሚችልና ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ የተፋሰስ ልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። በዘንድሮው የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ እቀባ የተፋሰስ ልማት ስራ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ መከናወኑ ተገልጿል። የዘንድሮውን የበጋ ተፋሰስ ልማት ክንውንና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ዝግጅት ላይ ያተኮረ የሁሉም ክልሎች የግብርና ቢሮ አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።   የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢያሱ ኤሊያስ(ፕ/ር) በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት የተፋስስ ልማትን በሳይንሳዊ መንገድ በመምራት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚያጋጥም ድርቅና ጎርፍን የመቋቋም ስራዎች እየተከናወኑ ነው። በተጨማሪም የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ የተፋሰስ ልማት ስራ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። የተፋሰስ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ ስራ በዘመቻ ብቻ ሳይሆን ሳይንሳዊ ይዘትና አሰራርን በተከተለ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የባለሙያዎችና የአመራሮች ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። የዛሬው መድረክ በተፋሰስ ልማቱና በችግኝ ዝግጅቱ ሂደት ላይ ያገጠሙ ክፍተቶች ተገምግመው ችግሮችን በመለየት ቀጣይ የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው ብለዋል። ከተፋሰስ ልማት ስራ ጎን ለጎን ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፕሮግራም የመትከያ ጉድጓድ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል። የተፋሰስ ልማቱ ከዘመቻ ባለፈ የህዝቡ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የተደረገና ውጤታማ እየሆነ የመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።   በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን በበኩላቸው በዘንድሮው የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል። በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ21 ሺህ 379 በላይ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው ከ598 ሺህ በላይ ሄክታር ከንክኪ ነፃ የተደረገበት ነውም ብለዋል። በተፋሰስ ልማት ስራው በርካታ ህዝብ መሳተፉን የገለፁት አቶ ፋኖሴ አዲስ ከሚሰራው የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ በተጓዳኝ አምና የተሰሩትን ዕርከኖች የማደስና የመጠገን ስራ መከናወኑንም አመላክተዋል። ህዝቡ በአማካይ ለሁለት ወራት የተፋሰስ ልማት ስራውን በነቂስ ወጥቶ ሲያከናውን መቆየቱንም ገልጸዋል።
በክልሉ በህዝቡ ተሳትፎ ከ363 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተከናውኗል
Apr 11, 2025 143
ባህር ዳር፤ሚያዚያ 3/2017 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወራት በህዝቡ ተሳትፎ ከ363 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ማከናወን መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው የተካሄደው ከጥር ወር አጋማሽ እስከ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም ነው። ለስራውም 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ሰዎችን በመሳተፍ በ8 ሺህ 400 ተፋሰሶች በተፈጥሮ ሃብት መልማታቸውን ገልጸዋል። ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥም የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን፣የውሃ ማስረጊያ ስትራክቸሮች፣ውሃ ማፋሰሻና መቀልበሻ ቦይና የተራቆቱ ተራራማ አካባቢዎችን ከልሎ የመጠበቅ ስራ ይገኙበታል ብለዋል። ህብረተሰቡ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ያበረከተው አስተዋፅኦ በገንዘብ ሲተመንም ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳለው ጠቅሰዋል። ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የአፈር መከላትን በመቀነስ የሰብል ምርታማነትን መጨመር እንዳስቻለም አስረድተዋል። የክልሉ ህዝብ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ተግባር የሚያስገኘውን ጥቅም በአግባቡ እየተረዳ መምጣቱንም ጠቁመዋል። በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ አርሶ አደር የማታ ቢሰጥ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የተራቆቱ አካባቢያቸውን ወደ ለምነት እንዲመለስ አስችሏል። የመሬታቸው ለምነት በመሻሻሉም ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማስቻሉን ጠቁመዋል። አሁን ላይ በሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ቀስቃሽ ሳያስፈልገን የአካባቢው ማህበረሰብ በነቂስ በመውጣት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። ቀደም ሲል የተፈጥሮ ሃብት ልማት የተከናወነባቸው ተፋሰሶች በማገገማቸው በንብ ማነብና በእንስሳት ማድለብ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሙላት መልኬ ናቸው። በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ አርሶ አደር የኔው አላምር በበኩላቸው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የተሰራባቸው አካባቢዎች ምንጮች እንዲፈልቁ በማድረጉ በመስኖ ልማት እንዲሳተፉ ምክንያት እንደሆናቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም