በአማራ ክልል 207 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው - የክልሉ ግብርና ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል 207 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው - የክልሉ ግብርና ቢሮ

ባህር ዳር፤ ሚያዚያ 16/2017(ኢዜአ):- በአማራ ክልል በመጪው ክረምት በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 207 ሺህ ሄክታር የተጎዳ መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ባለፈው ዓመት ክረምት በክልሉ ከተተከለው ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ችግኝ በመጀመሪያው ዙር በተካሄደ ቆጠራ 85 በመቶ መፅደቁም ተመልክቷል።
በግብርና ቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የተጎዳ መሬትን በደን ለመሸፈን ጥረት እየተደረገ ነው።
እስካሁን በተደረገ ጥረትም በመንግስት፣ በግል፣ በማህበራትና በተቋማት አማካኝነት የችግኝ ዝግጅቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።
በሚከናወነው የችግኝ ተከላ በክልሉ አሁን ያለውን 16 ነጥብ 3 በመቶ የደን ሽፋን ወደ 17 ነጥብ 3 በመቶ ለማሳደግ ታሳቢ መደረጉንም አብራርተዋል።