ፖለቲካ
የምስራቅ አፍሪካን ስትራቴጂካዊ ቀጣናነት የሚመጥን ጠንካራ የፖሊስ ኃይል መገንባት ያስፈልጋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Apr 27, 2025 26
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካን ስትራቴጂካዊ ቀጣናነት የሚመጥን ጠንካራ የፖሊስ ኃይል መገንባት ያስፈልጋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተመሰረተበትን 116ኛ ዓመት በማስመልከት አምስተኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር የመክፈቻ መርሃ ግብር በሻምበል አበበ ቢቂላ ስታዲየም ተካሂዷል።   ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን የሺህ ዘመናት የስልጣኔ መገለጫ፣ የነጻነታቸው ፋና ወጊ እንዲሁም የተቋማት ምስረታ ታሪካቸው ማስረጃ ናት ብለዋል። ለዚህም ከ116 ዓመታት በፊት በ1901 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ፖሊስ ሁነኛ ምልክት መሆኑን አውስተዋል። ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ወቅቶች በዓለም አቀፍ መድረኮች ለአፍሪካውያን የተሟገተች ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር አህጉራዊና ቀጣናዊ የህብረት ድርጅቶችን መመስረቷን ተናግረዋል። የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች የጋራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ርዕይ ያለን ነን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ፖሊስም ከተለያዩ ሀገራት ጋር በወንድማማችነት መንፈስ በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም የበርካታ ሀገራትን የፖሊስ ሠራዊት ማሰልጠኑን፣ አንዳንድ ሀገራት የፖሊስ ተቋም እንዲመሰርቱ ድጋፍ ማድረጉንም አውስተዋል። የአፍሪካ ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግና ያለጠንካራ የፖሊስ ተቋማት አይታሰብም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በስልጠና የዳበረ፣ በቴክኖሎጂ የዘመነ፣ ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተናበበ መልኩ የሚጓዝ ብቁ የፖሊስ ኃይል መገንባት የግድ መሆኑንም ነው የገለጹት። የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ በእስያና በአፍሪካ አህጉራት መካከል ቁልፍ ቦታ ላይ የሚገኝ መሆኑን በመጥቀስ፤ ጠንካራ የፖሊስ ሠራዊት የሚያስፈልገው ቀጣና መሆኑን ተናግረዋል። ሕጋዊ የሰዎች ዝውውር እና የሸቀጦች ግብይት ለማሳለጥ፣ ቀጣናዊ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ እየረቀቁ የመጡ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል፣ ዘመናዊ፣ ጠንካራና ዝግጁ የፖሊስ ኃይል ያስፈልጋል ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ህብረቶች በኩል በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅትን ጨምሮ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ፖሊስ አደረጃጀቱን እያስተካከለ፣ የአባላቱን የስልጠና ብቃት እያጠናከረ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ አቅሙን እያዳበረ ዓለም አቀፍ ልምዶችን እያካበተ መምጣቱንም ጠቅሰዋል። ባለፉት ሰባት ዓመታት በጸጥታ ተቋማት የተካሄደው ሪፎርም ፖሊስን ይበልጥ ዘመናዊ፣ ዝግጁ፣ ደረጃውን የጠበቀ፣ ግዳጁን በብቃት የሚወጣ ተቋም እንዲሆን አድርጎታል ነው ያሉት።   አፍሪካን በሚመጥን መልኩ ተባብሮ መስራት እንደሚገባ በማንሳት፤ በየአካባቢው ያለንን እውቀት፣ ልምድ፣ ቴክኖሎጂና ብቃት ደምሮ በመጠቀም የተሻለ የፖሊስ ተቋም የመገንባት ህልምን እውን ማድረግ ይቻላል ብለዋል። የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅትም ፖሊሳዊ ህብረትና ወዳጅነትን እንደሚያጠናክር፣ ለአንድ ዓላማ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን እንደሚያዳብር አንስተዋል። የኢትዮጵያ ፖሊስ ኢትዮጵያንና አፍሪካን በዓለም መድረክ ያስጠሩ ስመ ገናና ስፖርተኞችን ማፍራቱንም አውስተዋል። የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር ቀጣናዊ ህብረትን ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የአፍሪካውያን ሰላም፣ ዕድገት እና ብልጽግና ያለ ፖሊስ ተቋማት ጥንካሬ እና ብቃት የሚታሰብ አይደለም - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Apr 27, 2025 32
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካውያን ሰላም፣ ዕድገት እና ብልጽግና ያለ ፖሊስ ተቋማት ጥንካሬ እና ብቃት የሚታሰብ አይደለም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ የኢትዮጵያ ፖሊስ የተመሰረተበትን 116ኛ ዓመት በዓልን በማስመልከት የሚካሄደውን 5ኛውን የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት የስፖርት ውድድር በውቧ አዲስ አበባ በይፋ አስጀምረናል ብለዋል።   ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዘመናዊ የፖሊስ ተቋምን ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት በመመስረት ግንባር ቀደምና ተምሳሌት ሀገር ናት ሲሉም ገልጸዋል። ባለፉት ሰባት ዓመታት ያደረግነው የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም ደግሞ ፖሊስን ይበልጥ ዘመናዊ፣ ይበልጥ ዝግጁ፣ ይበልጥ ደረጃውን የጠበቀ፣ ይበልጥ ግዳጅ ፈጻሚ እያደረገው ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፖሊስ ኢትዮጵያንና አፍሪካን በዓለም መድረክ ያስጠሩ ስመ ጥር ስፖርተኞችን ያፈራ ተቋም ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አፍሪካዊ የሆኑ ስፖርታዊ ኩነቶችን እንዲያዘጋጅ ታሪኩም ልምዱም ይረዳዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ አፍሪካውያን አፍሪካን በሚመጥን ደረጃ ተባብረን መሥራት አለብንም ብለዋል፡፡ በየአካባቢያችን ያለንን ዕውቀት፣ ልምድ፣ ቴክኖሎጂና ብቃት ደምረን ከተጠቀምን የተሻለ የፖሊስ ተቋም የመገንባት ሕልማችንን እውን ማድረግ እንችላለን ነው ያሉት፡፡   የምሥራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅትም ይሄንን ፖሊሳዊ ኅብረትና ወዳጅነት ያጠናክራል ሲሉም ተናግረዋል። ለአንድ ዓላማ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ያዳብራል። ይህ የስፖርት ፌስቲቫል ኅብረታችን የበለጠ የሚጠናከርበት እንደሚሆን አምናለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው ፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመልዕክታቸው መልካም የውውድር ጊዜ እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ለከተማችን ሰላምና የልማት እቅዶች መሳካት የድርሻችንን ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ ነን- የደሴ ከተማ ነዋሪዎች
Apr 26, 2025 113
ደሴ፤ሚያዚያ 18/2017( ኢዜአ)፡-ለከተማችን ሰላምና የልማት እቅዶች መሳካት የድርሻችንን ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ ነን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። የደሴ ከተማ የኮሪደርና ሌሎች ልማቶች ውጤታማ የሆኑት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የልማቱም ይሁን የሰላም አጋር መሆኑን በተግባር በማሳየቱ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል። ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሸህ ሙስጠፋ አህመድ፤ የሁሉም ነገር መሰረት ሰላም በመሆኑ ሰላምን አስቀድመን የልማት ስራዎችን አስከትለን በቅንጅት በመስራታችን ተጠቃሚዎች ሆነናል ብለዋል። በደሴ ከተማ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን ኮንፈረንስን ጨምሮ የጎብኝዎች እንቅስቃሴ በመኖሩ ከቱሪዝም ዘርፉ ገቢ እያገኘን ነው ሲሉም ተናግረዋል። በቀጣይም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እና የአስተዳደር መዋቅር ጋር በመተባበር ለዘላቂ ሰላምና ልማታችን ዘብ እንቆማለን ሲሉ አረጋግጠዋል። ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ቀሲስ ዘላለም ቢሆነኝ፤ የእምነት ተቋማትና የኃይማኖት አባቶች የመጀመሪያ ተግባር ሰላምን መስበክና ስለ ሰላም አብዝቶ መጸለይ በመሆኑ በዚሁ መልኩ እያገዝን ነው ብለዋል። ሌላኛዋ የደሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እቴነሽ አባተ፤ የደሴ ከተማ የሰላምና አብሮነት እሴቶች ለሌሎችም ጥሩ ማሳያ የሚሆን ነው ብለዋል። ለከተማችን ሰላምና የልማት እቅዶች መሳካት የድርሻችንን ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ ነን በማለት ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል። የደሴ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ደህንነት መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ፤ የደሴ ከተማ አስተማማኝ ሰላም መሰረቶች የህዝቡና የጸጥታ ሃይሉ ጥብቅ ትስስርና መተጋገዝ ያመጣው መሆኑን ገልጸዋል። በየሰፈሩ ነዋሪው ተደራጅቶ ሰላሙን እያስጠበቀና እየተከታተለ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ደሴ ከተማ የትኛውም አካባቢ ወንጀል ፈፃሚዎች በቅጽበት የሚያዙ መሆኑን ጠቅሰው፥ በሁሉም አካባቢ አስተማማኝ ሰላም መኖሩን አረጋግጠዋል። በከተማው በየእለቱ የተለያዩ ሁነቶችና በርካታ ኮንፈረንሶች የሚካሄዱ መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም የከተማው ነዋሪ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም የሆቴሎች፣የምግብና መዝናኛ ቤቶች እንዲሁም በሌሎች የአገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማሩት ሰዎች በእጅጉ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል። በመሆኑም የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ የወጣቱ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አጠቃላይ የነዋሪዎች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።
ሪፎርሙ ገለልተኛ እና ዘመኑን የዋጀ የፀጥታ ተቋም ከመገንባት አንፃር አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው- አቶ ኦርዲን በድሪ
Apr 26, 2025 114
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፦ሪፎርሙ ገለልተኛ እና ዘመኑን የዋጀ የፀጥታ ተቋም ከመገንባት አንፃር አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ። ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በሐረሪ ክልል የሚገኙ የጸጥታ ተቋማት 116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ የምስረታ በዓልን አስመልክቶ በከተማው የጽዳት ዘመቻ እና አረንጓዴ ስፍራዎችን እንክብካቤ ማካሄዳቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል። የሪፎርሙ አንዱ አካል የሆነው የተቋም ግንባታ ስራ ብቁ፣ ገለልተኛ እና ዘመኑን የዋጀ የፀጥታ ተቋም ከመገንባት አንፃር አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል። በተለይም የክልሉ ፖሊስ ከነበሩበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተላቆ የፀጥታ እና የህግ ማስከበር ስራዎችን በብቃት ከመፈፀም ባለፈ በዚህ አይነት የልማት ስራዎች መሳየተፉ የሰራዊቱን ህዝባዊነት የሚያመላክት እንደሆነም አመልክተዋል። በቀጣይም የተቋም ግንባታ ስራ ለማጠናከር አስፈላጊውን እገዛ እንደሚደረግ ገልጸው ዛሬ በተካሄደው የልማት ስራ ለተሳተፉ የፀጥታ አመራሮችና አባላት ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በተያዘው ዓመት በታቀደው መሰረት ያድጋል
Apr 26, 2025 140
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በተያዘው ዓመት በታቀደው መሰረት በስምንት ነጥብ አራት በመቶ እንደሚያድግ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስታወቀ። የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሚያዚያ 17 እስከ 18 ቀን 2017 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባውን ካካሄደ በኋላ መግለጫ አውጥቷል። ለሁለት ቀናት ሲካሔድ የቆየው የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቀቀ በመግለጫውም የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች በዝርዝር መመልከቱን ገልጿል።   ኢትዮጵያ በ2018 ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን ለመሻገር፤ በ2023 የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን፤ በ2040 ደግሞ ዓለም አቀፍ የብልጽግና አርአያ ለመሆን ያስቀመጠችው ርዕይ እንደሚሳካ የሚያረጋግጡ የስኬት ፍንጮች መታየታቸውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡ የስኬት ፍንጮች ፓርቲው የያዘው ፍኖተ ብልጽግና ትክክል መሆኑን እንደሚያመለክትም አትቷል። በኢኮኖሚው ዘርፍ እስከ አሁን ያለው አፈፃፀም የሚያሳየው በያዝነው ዓመት አጠቃላይ ኢኮኖሚው በታቀደው መሠረት በስምንት ነጥብ አራት በመቶ የሚያድግ መሆኑን የሥራ አስፈጻሚው መገምገሙን አረጋግጧል። በዘርፍ ደረጃ ግብርና በስድስት ነጥብ አንድ በመቶ፣ ኢንዱስትሪ በ12 ነጥብ 8 በመቶ፣ ማኑፋክቸሪንግ በ12 በመቶ፣ ኮንስትራክሽን በ12 ነጥብ 3 በመቶ፣ አገልግሎት ደግሞ በሰባት ነጥብ አንድ በመቶ የሚያድጉ መሆናቸው መገምገሙን አመልክቷል።   ባለፉት ዘጠኝ ወራት ጠቅላላ የመንግሥት ገቢ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ134 በመቶ ብልጫ ማሳየቱንም አመልክቷል። የውጭ ብድር ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ መውረዱን የጠቆመው መግለጫው፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡት ስድስት ዋና ዋና ምርቶች፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸሩ ከ82 በመቶ እስከ 386 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸውን አመልክቷል። በስንዴ፣ በሩዝ፣ በቡና፣ በሻሂ ቅጠል እና በፍራፍሬ ምርቶች በአፍሪካ ቀዳሚ ሆኖ ለመውጣት እየተደረገ ያለው ትግል ፍሬ እያፈራ መሆኑን እንደሚያሳይ መግለጫው አረጋግጧል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት ናት - ሌተናል ጄነራል መሐመድ ባሬድ
Apr 26, 2025 103
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት ናት ሲሉ የሞሮኮ ሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄነራል መሐመድ ባሬድ ገለጹ። ለአፍሪካ ሰላም እና ደህንነት እያደረገች ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል። የሞሮኮ ወታደራዊ ልዑካን ቡድን ከመከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ፋይናንስ ስራ አመራር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ ጋር ውይይት አድርጓል። የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድን በመወከል ውይይቱን የመሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ ኢትዮጵያ የጋራ ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት እና የማይቀለበስ ጠንካራ ወታደራዊ ግንኙነት ለመመስረት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል። ትብብሩን በመከባበር እና በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል። የሞሮኮ ሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄነራል መሐመድ ባሬድ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት ናት ብለዋል። በአሁኑ ሰዓትም ለአህጉሪቷ ሰላም እና ደህንነት እያበረከተች ላለው ወታደራዊ ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። የሀገራቱ ወታደራዊ ትብብርም ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነም አመልክተዋል። በአጠቃላይ የሞሮኮ ልዑካን ቡድን ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ሰራዊት ያላቸው አክብሮት ታላቅ መሆኑን ተናግረዋል። በውይይቱ ዋነኛ ወታደራዊ፣ሀገራዊ እና አህጉራዊ ትኩረት ናቸው ተብለው በተለዩ የሰላም እና አጠቃላይ ወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን የሁለቱም ሀገራት አመራሮች ገልጸዋል። በውይይቱ ላይም የመከላከያ ውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ተሾመ ገመቹን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።
ለሁለት ቀናት ሲካሔድ የቆየው የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቀቀ
Apr 26, 2025 164
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2017(ኢዜአ)፦ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ያካሔደው ጉባኤ ተጠናቋል። የጉባኤውን መጠናቀቅ ተከትሎ የወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ይቀርባል፦ ከብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 17 እስከ 18/ 2017 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባውን በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡ በዚህ ስብሰባም የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች በዝርዝር ተመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ በ2018 ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብርሃን ለመሻገር፤ በ2023 የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን፤ በ2040 ደግሞ ዓለም አቀፍ የብልጽግና አርአያ ለመሆን ያስቀመጠችው ርእይ እንደሚሳካ የሚያረጋግጡ የስኬት ፍንጮች መታየታቸውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡ እነዚህ የስኬት ፍንጮች የያዝነው ፍኖተ ብልጽግና ትክክል መሆኑን አመላክተውናል፡፡ ከብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ በኋላ አያሌ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ ከተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በየደረጃው የሚደረገው ምክክርና ትብብር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ወደ አዲስ ምእራፍ ገብቷል፡፡ ከአንድ ክልል በስተቀር፣ ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ምእራፍ በሁሉም ክልሎች ተጠናቅቋል፡፡ በሀገሪቱ የጸጥታ ችግር በነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎችም ሰላም እየሰፈነ ነው፡፡ መንግስት በተደጋጋሚ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ እጅ የሚሰጡና ወደ ሰላም ድርድር የሚመጡ ታጣቂዎች ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየጨመረ ይገኛል፡፡ የመንግሥት ሕግ የማስከበርና የማድረግ ዐቅም እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ከሶማሊያ ጋር ተፈጥሮ የነበረው ውዝግብ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ተፈትቷል፡፡ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት የተያዘው አቋም ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነቱ እየጨመረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት ከመሻሻሉም በላይ የሚደረግላት ድጋፍ እያደገ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት ጨምሯል፡፡ የዲፕሎማሲ ግንኙነቷም በሁሉም አቅጣጫ ከፍ ብሏል፡፡ እስከአሁን ያለው አፈፃፀም የሚያሳየው በያዝነው አመት አጠቃላይ ኢኮኖሚው በታቀደው መሠረት በ8.4 በመቶ የሚያድግ መሆኑን የሥራ አስፈጻሚው ገምግሟል፡፡ በዘርፍ ደረጃ ደግሞ ግብርና በ6.1 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ በ12.8 በመቶ፣ ማኑፋክቸሪንግ በ12.0 በመቶ፣ ኮንስትራክሽን በ12.3 በመቶ፣ አገልግሎት ደግሞ በ7.1 በመቶ የሚያድጉ መሆናቸው ተገምግሟል፡፡ ያለፉት 9 ወራት ጠቅላላ የመንግሥት ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ134 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ የውጭ ብድር ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 13.7 በመቶ ወርዷል፡፡ ወደ ውጭ ገበያ የሚቀርቡት ስድስት ዋና ዋና ምርቶች፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸሩ ከ82 በመቶ እስከ 386 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ በስንዴ፣ በሩዝ፣ በቡና፣ በሻሂ ቅጠል እና በፍራፍሬ ምርቶች በአፍሪካ ቀዳሚ ሆኖ ለመውጣት እየተደረገ ያለው ትግል ፍሬ እያፈራ መሆኑን አይተናል፡፡ ውድ የብልፅግና አመራሮች፣ የብልፅግና አባላትና መላው ሕዝባችን፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዝቅተኛ ኑሮ በሚኖሩ ወገኖች ላይ ጫና እንዳያሳድር አስፈላጊ የሆኑና የታቀዱ የድጋፍ መርሐ ግብሮች መከናወናቸውንም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መርምሯል፡፡ ለማዳበሪያ 62 ቢልዮን ብር፣ ለሴፍቲኔት 41.2 ቢልዮን ብር፣ ለነዳጅ 60 ቢልዮን ብር፣ ለመድኃኒት 3.5 ቢልዮን ብር፣ ለምግብ ዘይት 6.1 ቢልዮን ብር፣ እንዲሁም ለደመወዝ 38.4 ቢልዮን ብር ድጎማ ተደርጓል፡፡ ባለፉት 9 ወራት ብቻ 344790 የውጭ ሀገር ሕጋዊ የሥራ ዕድሎች እና ከ3 ሚልዮን በላይ የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡ የርቀት የሥራ ዕድሎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱ ታይቷል፡፡ የመንግሥት የልማት ተቋማትን በአዲስ አስተሳሰብና በአዲስ መንገድ መልሶ ለማደራጀትና ለመምራት መቻሉ፣ እያስገኘው ያለው ውጤት ለሌሎች አርአያ የሚሆን እንደሆነ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አሁን ያለው ጠቅላላ ገቢ 1.5 ትሪልዮን መድረሱ ታይቷል፡፡ ከባለፈው ዓመት የ9 ወራት አፈጻጸም አንጻር የዘንድሮ ገቢው የ86 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱም ተረጋግጧል፡፡ ይሄም መንግሥት የሀገርን ሀብት ለማወቅ፣ ዐውቆም በሚገባ ለማስተዳደር፣ አስተዳድሮም ወረት ለማከማቸት የተከተለው መርሕ ትክክል መሆኑን አረጋግጧል፡፡ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ዕድገት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ 9 ወራት ጋር ሲነጻጸር የ203.99 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ከ3 ትሪልየን በላይ ተሻግሯል፡፡ የ9 ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከ5 ቢልዮን ዶላር በላይ ሲሆን፣ ይሄም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ150.39 በመቶ ዕድገት አምጥቷል፡፡ ባለፉት ስምንት ወራት 473.9 ቢልዮን ብር ብድር ከንግድ ባንኮች ተለቅቋል፡፡ ይሄም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ አንጻር በ61.9 በመቶ ከፍ ይላል፡፡ ከዚህ ብድር ውስጥም 76.6 በመቶ ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ ነው፡፡ ለግሉ ዘርፍ የበለጠ ብድር መሰጠቱ፣ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ተገቢውን ሚና እንዲጫወት ያስቀመጥነው ፖሊሲ በተግባር እየተገለጠ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ለማሳካት የጀመርናቸው ሁሉን አቀፍ ጥረቶች ፍሬያቸው እየጎመራ ነው፡፡ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 50.2 ሚልዮን፣ የሞባይል ተጠቃሚዎችም 86.6 ሚልዮን ደርሰዋል፡፡ የቴሌ ብር ደንበኞችም ከ52.56 ሚሊዮን በላይ ናቸው፡፡ ዲጂታል ፋይናንስ፣ የኅብረተሰቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢኮኖሚው መሣለጥ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ነው፡፡ ባለፉት 9 ወራት በዲጂታል መንገዶች 7.73 ቢልዮን ብር ተቆጥቧል፡፡ 26.77 ቢልዮን ብር በዲጂታል በኩል ብድር ተሰጠ ሲሆን፣ የ12.51 ትሪሊዮን ብር ግብይት ደግሞ በዚሁ መንገድ ተከናውኗል፡፡ ዋና ዋና ፕሮጀክቶችን በጊዜና በተገቢ ደረጃ ለማጠናቀቅ የተሰጠው አቅጣጫ ብዙዎችን ለፍጻሜ እያበቃቸው ነው፡፡ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 98.66 በመቶ ደርሷል፡፡ የኮይሻ፣ አይሻና አሰላ የኃይል ማመንጫዎች በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት እየተጓዙ መሆናቸው ተገምግሟል፡፡ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታም የኢትዮጵያን ነገ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የቅድመ ዝግጅት ምእራፉ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ በ8 ኮሪደሮች እና በመላው ኢትዮጵያ በ65 ከተሞች እየተከናወነ መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ብዙዎቹ የመስኖ ግድቦች ወደ ፍጻሜያቸው እየደረሱ ናቸው፡፡ ከዘጠኙ የመስኖ ግድቦች ውስጥ ስድስቱ አፈጻጸማቸው ከ75 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡ “ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ቃል ከ82 ቢልዮን ብር በላይ ድጋፍ የተሰበሰበ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 6815 ትምህርት ቤቶች በመላ ሀገሪቱ ተገንብተዋል፡፡ የነባር ትምህርት ቤቶችን ዐቅም ለማሻሻል እና በግጭት የተጎዱትን ለመጠገን የተደረገው ጥረት በትውልድ ላይ ለሚሠራው ሥራ መሠረት የሚጥል መሆኑ ታይቷል፡፡ የወላድ እናቶችን እና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ የተሻለ ውጤት መመዝገቡም ታይቷል፡፡ በኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎችና የስፖርት ሥፍራዎች በቁጥርም፣ በዓይነትም እያደጉ መጥተዋል፡፡ በተለያዩ ከተሞች በመገንባት ላይ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ስታዲየሞች በመጠናቀቂያ ምእራፍ ላይ ናቸው፡፡ ይሄም ኢትዮጵያ ታላላቅ አፍሪካዊ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ለያዘችው ዕቅድ መሳካት ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኩነቶችን ለማስተናገድ ያላት መሠረተ ልማት እና የመስተንግዶ ዐቅም እያደገ ይገኛል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ66 በላይ ዓለም አቀፍ ኩነቶች በሀገራችን ተደርገዋል፡፡ በቱሪስት ፍሰት ጭማሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር በመሆን ላይ ነን፡፡ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ጸጋዎች አውጥተን ማሳየት ከቻልን፣ በቱሪዝም መስክ የቀዳሚነት ሚና መጫወት እንደምንችል ጅምሮቹ ያሳያሉ፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወኑ ተግባራት አምራችነትን በማበረታታት፣ ሥራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ በማስገባት፣ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት፣ የሀገር ውስጥ ገቢን በማሰባሰብ፣ ወጪ ምርቶችን በብዛት በማምረት፣ ከአንድ ጊዜ በላይ መሬትን ደጋግሞ በማረስ፣ ሪፎርሞችን በየዘርፋቸው አግባብ በመተግበር፣ የተመዘገቡ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ የተነሣ ራስን የመቻል ተነሣሽነት ጨምሯል፡፡ ዘጠኝ ክልሎች ሰብአዊ ድጋፍን በራሳቸው ዐቅም ከመሸፈናቸውም በላይ የሰብአዊ ድጋፍ ፈላጊዎች ቁጥርም ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ በ86 በመቶ ቀንሷል፡፡ ሂደቱ ተረጂነትን መጸየፍና አምራችነትን ባህል ማድረግ በሀገራችን ሥር እየያዘ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ውድ የብልፅግና አመራሮች፣ የብልፅግና አባላትና መላው ሕዝባችን፣ እነዚህ ስኬቶች የጉዟችን መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደሉም፡፡ ማበረታቻዎች እንጂ ፍጻሜዎች አይደሉም፡፡ ስኬቶቹ መንገዳችን ትክክል መሆኑን የሚያሳዩ የተራራ ላይ መብራቶች ናቸው፡፡ ለበለጠ ሥራ የሚያነሣሡ፣ ለበለጠ ወኔ የሚቀሰቅሱ፣ የጠለቀ ቁጭት የሚቆሰቁሱ ናቸው፡፡ በሠራናቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የጸጥታ ተቋማት ሪፎርሞች ሀገራችን ከነበረባት የህልውና አደጋ ወጥታ ወደ አስተማማኝ ህልውና እየተሻገረች ነው። ሪፎርሙ የነበረውን የህልውና ሥጋት መቀልበስ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገርን ህልውና ለመጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝ ዐቅም ፈጥሯል፡፡ ይሄም በተቃራኒው መንግሥትን በኃይል ለመጣል የነበረውን ፍላጎት አምክኗል፡፡ በተደረጉ ሀገር በቀል ማሻሻያዎች፣ በተፈጠረው ዐቅም እና ዝግጁነት ኢኮኖሚያችን ወደ ተሟላ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ገብቷል፡፡ ይሄ ደግሞ የኢኮኖሚ ሂደታችንን እና የብልጽግና ጉዟችንን የሚቀይር አዲስ ምእራፍ ፈጥሯል። የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ እና የባሕር በር ጉዳይ በቀጣናችን የአጀንዳ የበላይነት እንድንፈጥር አስችሎናል፡፡ በዚህም የተነሣ ሀገራችንን ከተከላካይነት ወደ ተጽዕኖ ፈጣሪነት አሸጋግሯታል። በመሆኑም ለውጡ ከመተከል ወደ ማንሠራራት ተራምዷል ማለት ይቻላል። መንግሥት የፈጠረው ዐቅም፣ የፀረ ለውጥ ኃይሉ መዳከም እና ዓለም አቀፍ ለውጡ የኢትዮጵያን ሪፎርም ለማሳካት የተሻለ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ መንግሥትን በኃይል ለመጣልና ፍላጎትን በጉልበት ለማሳካት የሚደረገው መፍጨርጨር ውጤት እንደማያስገኝ ሀገራዊ እውነት እየሆነ ነው፡፡ በየጊዜው ወደ ሰላም የሚመጡት ታጣቂዎች ቁጥር መጨመርም ይሄንን ያመለክታል፡፡ በአንድ በኩል እነዚህን ስኬቶች ይበልጥ ማስፋትና ማጽናት አለብን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ራሳችንን ከመሐል ዘመን ወጥመድ መጠበቅ ይገባናል፡፡ የመሐል ዘመን ወጥመድ፣ አንድ ሀገር ከፖለቲካ ሥርዓት ሽግግር በመውጣት፣ ወደ ቀጣዩ የማጽናት ምእራፍ ከመድረሷ በፊት፣ በሚገኘው የመሐል ዘመን፣ በስኬቶች ረክቶና ተዘናግቶ የመቀመጥ አባዜ ነው፡፡ ከፖለቲካ ሽግግር በመውጣትና የጸና ሥርዓትን በመትከል መካከል የሚገኝ ፈታኝ ዘመን ነው፡፡ የሀገራችን ኢኮኖሚ በማደግ ላይ ያለ እንጂ በሚፈለገው መጠን ያደገ አይደለም፡፡ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ልማት፣ በወጪ ምርቶች፣ በማዕድን፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ፣ ወዘተ. ያየናቸው ለውጦች ብንሠራ የት እንደምንደርስ አመላካቾች ናቸው፡፡ ከግባችን መድረሳችንን ግን አያበሥሩም፡፡ የፖለቲካ ባህላችን እየተለወጠ ነው፤ ነገር ግን የሠለጠነ የፖለቲካ ባህል ገና አልገነባንም፡፡ የጸጥታ ተቋሞቻችን እየዘመኑና እየደረጁ ናቸው፤ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ልክ ገና አልደረሱም፡፡ የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል የማስፈጸም አካሄድ ፋሽኑ እያለፈበት መጥቷል፡፡ ነገር ግን ገና ከፖለቲካና ከማኅበራዊ ባህላችን ተፍቆ አልጠፋም፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ገና በጅምር ላይ ነው፡፡ ዕዳችን ቢቃለልም ገና ከጫንቃችን ፈጽሞ አልወረደም፡፡ የዋጋ ግሽበትን ብንቋቋመውም፣ የኑሮ ውድነትን ግን በተገቢው መንገድ ገና አላቃለልነውም፡፡ በመሆኑም ከስኬት ማማ ላይ የደረስን መስሎን፣ በመሐል ዘመን ወጥመድ እንዳንያዝ አመራሮችና አባላት ነቅተው እንዲታገሉ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በአጽንዖት ያሳስባል፡፡ የመሐል ዘመን ወጥመድ በዋናነት የሚከሠተው በውጤት በመዘናጋት፣ ችግርን በመላመድ፣ ሀገራዊ ዕይታን ትቶ በጎጥ ውስጥ በማደር እና የሕዝብን ችግሮች በጊዜያቸውና በልካቸው ባለመፍታት ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ችግሮች የመሐል ዘመን ወጥመድን እንዳያመጡብን በአመራሩና በአባላቱ ዘንድ ትግል ሊደረግባቸው ይገባል ፡፡ ውድ የብልፅግና አመራሮች፣ የብልፅግና አባላትና መላው ሕዝባችን፣ የተዛባ ትርክት እንዳይፈጠር የብሔራዊ ዐርበኝነት ትርክትን በሚገባ ማሥረጽ ይጠበቅብናል፡፡ የሕዝብን ጥያቄዎች በየደረጃው መፍታት አለብን፡፡ ምርትና ምርታማነትን ከፍ በማድረግ የኑሮ ውድነትን የሚያቃልሉ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ የተጀመሩ ኢኒሼቲቮችን የሕዝብ ርካታ በሚፈጥሩ መልኩ ወደ ውጤት ማድረስ አለብን፡፡ ከጠላቶቻችንን ላይ የመሣሪያም የትርክትም ትጥቅ ማስፈታት ይገባል፡፡ ለጠላት ተጋላጭነትን ሊፈጥሩ የሚችሉ አሠራሮችን ማረም ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው፡፡ የአመራር ሥምሪትን መፈተሽና ማጥራት መንገዳችንን የበለጠ ምቹ ያደርገዋል፡፡ ትጋትና ቁርጠኝነትን መጨመር፣ መናበብንና ቅንጅትን ማሣለጥ አለብን፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚፈጥሩ፣ ገዥ ትርክትን የሚያሠርጹ፣ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን የሚያስከብሩ እና የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ተግባራትን ባለማሰለስ በየአካባቢያችን ተግተን ማከናወን ያስፈልገናል፡፡ የክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን በተገቢ ዕቅድ እና ቅንጅት መርተን ለውጤት ማብቃት ይገባናል፡፡ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በዚህ ዓመት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሕዝቡን የማትጋትና የማሳተፍ ሥራ ከአሁኑ መጀመር አለበት፡፡ ለመኸር የእርሻ ሥራዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና ማሽነሪዎች በተገቢ ቦታና ጊዜ እንዲደርሱ የአመራር ሚናችንን እንወጣ፡፡ አንድም መሬት ጦም በማያድርበት ሁኔታ የግብርና ሥራዎች እንዲከናወኑ እናድርግ፡፡ በአጠቃላይ፣ በሰላማዊ እና በሠለጠነ መንገድ ልዩነቶቻችን በመፍታት፣ የጀመርናቸው ሪፎርሞች በማሳካት፣ የገጠሙንን ፈተናዎች በጽናት በማለፍ፣ ተግዳሮቶቻችንን በመጋፈጥና በማሸነፍ፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን እንድናደርግ፣ የብልፅግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለብልፅግና ፓርቲ አመራርና አባላት፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ ያቀርባል፡፡ የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 18/ 2017፤ አዲስ አበባ
ሠላምን በማፅናት ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው - ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዎስ
Apr 26, 2025 98
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2017(ኢዜአ)፦ ሠላምን በማፅናት ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ገለጹ። ሚኒስትሩ በወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ ፣ አህጉራዊ ፣ ቀጣናዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል። "የመሀሉ ዘመን" በሚል ርዕስ ትንታኔ ያቀረቡት ሚኒስትሩ በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተመዘገቡ ሁለንተናዊ ድሎች ሳንዘናጋ ለበለጠ ድል መትጋት ይገባል ብለዋል። ሀገሩን የሚወድ የተሰለፈበትን ዓላማ የተረዳና ፕሮፌሽናል የሆነ ብሄራዊ የመከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል -ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በከፍተኛ ፈተናዎች ውስጥ ገንብተን በማጠናቀቅ ሀገርና ህዝብን አንገት ከማስደፋት ለማዳን የተቻለበትና የጠላቶቻችንን የተቀናጀ ሴራ ያከሸፍንበት አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ሀገራዊ ኢኮኖሚያችን ፈተናዎችን በመቋቋም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም ዓለም አቀፍና ሀገራዊ መረጃዎችን በማጣቀስ አብራርተዋል።   ባለፉት ዓመታት ብዙ ሀገራት በዲፕሎማሲው መስክ በትብብር ለመስራት ፍቃደኝነታቸውን ማሳየታቸውንና ይህንን በጎ ዕድል በመጠቀም ብሄራዊ ጥቅማችን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። የባህር በር ተጠቃሚ ለመሆን የቀረበው ጥያቄም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ፍትሃዊ አጀንዳ ሆኖ መያዙን ሚኒስትሩ አስረድትዋል። ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች በሆነው ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ እንቅስቃሴ ያለንን ሁለንተናዊ ዝግጁነት በማረጋገጥና የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ተጋላጭነታችንን ለመቀነስ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። በተከተልነው የሰላም ስምምነት የፀና ወታደራዊ ድል ተመዝግቧል ያሉት ሚኒስትሩ የሚያጋጥሙ ውስጣዊ ችግሮችን በሰላምና በይቅርታ በመፍታት በሀገርና በህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ለመቀነስ መንግስት እየወሰደው ያለው በሳል እርምጃ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡንም ተናግረዋል።   የሰላምን ጥሪ ባለመቀበል በሀይል ጥቅማችንን እናስከብራለን በማለት የሞከሩ የጥፋት ሀይሎች በተከተሉት የተሳሳተ ትርክትና ፖለቲካ ህዝቡ አንቅሮ እንደተፋቸውም ገልፀዋል። የመከላከያ ሠራዊቱ ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን በፅንፈኞች ላይ በወሰደው እርምጃም ለሀገርና ለህዝብ ስጋት ከመሆን ወርደው የራሳቸውን ህልውና ለማቆየት እየተቸገሩ መምጣታቸውን አንስተዋል ። ሠላምን ለማፅናትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ገልፀው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንም ባስመዘገባቸው ድሎች ሳይኩራራ ለበለጠ ተልዕኮ ራሱን ማዘጋጀት ይገባዋል ብለዋል። በውይይቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን ጨምሮ ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮች ተገኝተዋል።
በመዲናዋ ሰላምን በማጽናትና ወንጀልን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል- ቢሮው
Apr 26, 2025 105
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 18/2017(ኢዜአ)፦በመዲናዋ ሰላምን በማጽናትና ወንጀልን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው ከአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ጋር በመተባበር 2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ህብረተሰቡን ያሳተፉ ወንጀል መከላከል እንዲሁም ሰላምና ጸጥታን ማረጋገጥ ተግባራት ተከናውነዋል። ህብረተሰቡ የሰላም ዘብነቱን ሚና አጠናክሮ እንዲቀጥል በርካታ የሰላም ኮንፍረንሶች መካሄዱን አስታውሰው፥ በዚህም ተጨባጫ ውጤቶች መጥተዋል ነው ያሉት። ከሰላም ሰራዊት ጋር በተያያዘም በበጀት ዓመቱ በርካታ አዳዲስ አባላትን በመመልመል እና በማሰልጠን እንዲሰማሩ መደረጉንም ገልጸዋል።   እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ፥ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ በመሰራቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የወንጀል ምጣኔን መቀነስ ከመቻሉም በላይ ሰላምን በአስተማማኝ ደረጃ ማጽናት ተችሏል። አዋኪ ድርጊቶች የሚፈጸሙባቸው ቦታዎችን በጥናት በመለየት የእርምት እርምጃ መወሰዱንም ነው የገለጹት። ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖራቸው ዋጋ በመጨመር የመልካም አስተዳደር ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይም አስፈላጊው እርምጃ መወሰዱንም አብራርተዋል። በደንብ ማስከበር በኩልም ከጎዳና ላይ ንግድ እንዲሁም የኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ ህግ የተላለፉ አካላት እንዲቀጡ ማድረጉንም አንስተዋል። የመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታዎችን መቆጣጠር ላይም የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ውጤታማ ስራ ማከናወኑንም ጠቁመዋል።
ሀገሩን የሚወድ የተሰለፈበትን ዓላማ የተረዳና ፕሮፌሽናል የሆነ ብሄራዊ የመከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል -ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ 
Apr 26, 2025 110
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ(ኢዜአ)፦ሀገሩን የሚወድ የተሰለፈበትን ዓላማ የተረዳና ፕሮፌሽናል የሆነ ብሄራዊ የመከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል ሲሉየኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ። ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ከሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል። በውይይቱም ራሱን በየጊዜው እየገመገመ በሁለንተናዊ መስኩ እያበቃ የመጣ ሀገሩን የሚወድና የተሰለፈበትን ዓላማ ጠንቅቆ የተረዳ ፕሮፌሽናል ሠራዊት መገንባቱን ገልፀዋል። የመከላከያ ሠራዊት በተሻለ ዝግጁነትና ቁመና ላይ ይገኛል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተቋሙ የተሰራው ሪፎርም በርካታ ውጤቶች ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ማስቻሉንም አንስተዋል። ሀገራችን በታሪኳ በዚህ ደረጃ ብዛትና ጥራት ያለው የፕሮፌሽናል ሰራዊት ገንብታ አታውቅም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ፣ ሀገሩንና ሙያውን የሚወድ የሚሰጠውን ግዳጅ በአነስተኛ ኪሳራ የመፈፀም ብቃት ያለው ሀይል ተገንብቷል ብለዋል።   ሠራዊቱ ሀገርን ከብተና ከማዳን ባለፈ የሀገራችንን ሰላም ፣ ብልፅግናና ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት ያስመዘገባቸው ድሎች በታሪክ ሲዘከር የሚኖር መሆኑንም ገልፀዋል። በተገኙ ድሎች ባለመኩራራት የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ድሎች አጠናክሮ ለማስቀጠልና የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል። በተሳሳተ ስሌት ወደጫካ ገብተው የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላምን መንገድ በመከተል እጃቸውን ለሠራዊቱ መስጠታቸውን የገለፁት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣በተለያየ ቦታ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ፅንፈኞች ከመቼውም ጊዜ በላይ መዳከማቸውና የሰላምን ጥሪ ባልተቀበሉት ላይ የተጀመሩት የመለቃቀም ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል። የሀገራችንን እድገትና ብልፅግና ማስቀጠል የሚችል አስተማማኝ የሰላም ሀይል ማፍራት ተችሏል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በጦር ሜዳ ማሸነፍ ያቃታቸው የሀገርና የህዝብ ጠላቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የውሸት ትርክት በመፍጠር በተቋሙ ፣ በአመራሩና በሰራዊቱ ላይ የስነልቦና ጦርነት በመክፈት ለማጠልሸት ቢሞክሩም በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት በማጣታቸው ለሠራዊታችን የሚደረገው ህዝባዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል። በምድር ፣ በባህር ፣ በአየር እና በሳይበር ሀይል የተደራጀው ሠራዊታችን ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂና የውጊያ አቅም ላይ ለማድረስ እንደተቻለ መግለጻቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል። ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ በተሳሳተ ስሌት ውጊያ ለመክፈት የሚሞክሩ ሀይሎችን በአነስተኛ ኪሳራና በአጭር ጊዜ ለመደምሰስ የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት መኖሩንም አረጋግጠዋል።  
አፍሪካውያን በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በጋራ ሊቆሙ ይገባል - ሚኒስትር አይሻ መሀመድ(ኢ/ር)
Apr 25, 2025 116
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ):- አፍሪካውያን በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የጋራ ድጋፍ እንዲያደርጉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ(ኢ/ር) ጥሪ አቀረቡ። በአፍሪካ ህብረት የድጋፍና የማረጋጋት ተልዕኮ በሶማሊያ (AUSSOM) ስር ወታደሮች ያዋጡ ሀገራት(TCCs) አስቸኳይ የመሪዎች የጋራ ጉባኤ ዛሬ በዩጋንዳ ተካሄዷል። ጉባኤው በዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ በተደረገ ግብዣ የተካሄደ ነው። በጉባኤው ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ጂቡቲ እና ሶማሊያ ተሳትፈዋል። በመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በጉባኤው ተሳትፏል። በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሂሩት ዘመነም ተሳታፊ ሆነዋል።   ጉባኤው በዋነኛነት አዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮን በማጠናከር፣ በሶማሊያ እና በቀጣናው የተጋረጠውን የሽብርተኝነት የማንሰራራት ሁኔታን በመመከት ላይ ያተኮረ መሆኑን በካምፓላ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል። ጉባኤው ከሚያዚያ 14 ጀምሮ ወታደራዊ ሲኒየር ኦፊሻሎችና የቋሚ ፀሐፊዎች፣ የመከላከያ ሚኒስትሮች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ተካሂዷል። አስቸኳይ የመሪዎች የጋራ ጉባኤው ላለፉት ሶስት ቀናት በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ መክሯል። የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) ባደረጉት ንግግር የሶማሊያ መንግስት እስከ አሁን የሄደበት መንገድ አድናቆት የሚሰጠው ቢሆንም፣ የፀጥታ ተቋማትን የማጠናከርና የማቀናጀት ስራ ላይ አበክሮ መስራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የሶማሊያ የጸጥታ ኃይል በራሱ አቅም ግዳጆችን የመወጣት አቅም ላይ እስኪደርስ ድረስ ድጋፏን ማድረግ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። ፋይናንስን በተመለከተም አሁንም ከነባርና አዳዲስ የፋይናንስ ምንጮች ድጋፍ ለማግኘት ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል። የአፍሪካ ህብረት እስከ አሁን ከህብረቱ ለአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ክምችት ላይ አውሶምን ለመደገፍ የሄደበትን መንገድም አድንቀዋል። አፍሪካውያን በሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በፓን አፍሪካኒዝም እና በአፍሪካ አንድነት የጋራ መንፈስ የሶማሊያን መንግስት እንዲያግዙ ኢትዮጵያ ጥሪ ታቀርባለች ብለዋል። በአውሶም ጥላ ስር ወታደር ያዋጡ ሀገሮች በበኩላቸው በቀጣይ የአልሸባብን በአዲስ መልክ የመደራጀት እንቅስቃሴ ለመግታት በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የኤምባሲው መረጃ ያሳያል።
አካዳሚውና የጋራ ምክር ቤቱ በአቅም ግንባታና ምርምሮች በጋራ ለመሥራት የደረሱበትን ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ
Apr 25, 2025 93
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በአቅም ግንባታ፣ ጥናትና ምርምሮች ላይ በጋራ ለመሥራት የደረሱበትን ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ። ተቋማቱ ህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። የመግባቢያ ሰነዱን ወደ መሬት ለማውረድ ከሁለቱ ተቋማት የተውጣጣ የቴክኒክ ቡድን በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ የጋራ ዕቅድ አዘጋጅቷል። በዛሬው ዕለትም በተዘጋጀው ዕቅድ ዙሪያ የአካዳሚው እና የጋራ ምክር ቤቱ አመራር አባላት የተወያዩ ሲሆን፤ በአቅም ግንባታ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች በጋራ የመስራት እንቅስቃሴ ጀምረዋል።   የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰረት ደስታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በስምምነቱ መሰረት አካዳሚው ለፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባለት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ይሰጣል። በዚህም ያሉ ክፍተቶችን በጥናት በመለየት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የፖሊሲ ማማከር ሥራዎችንም አካዳሚው እንደሚያከናውን አብራርተዋል። በዚህ ዓመት ለ120 የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንደሚሰጥ ገልጸው፤ ሥልጠናው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል። በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ሁኔታዎችን በላቀ ደረጃ የሚረዳና በቂ ግንዛቤ የጨበጠ አመራር ወሳኝ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቷ፤ በተቋማቱ መካከል የተደረገው ትብብር ይሄን ግብ ለማሳካት ያለመ ነው ብለዋል።   የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ በበኩላቸው፤ ያለን አንድ አገር ነው፤ ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት መረባረብ አለብን ብለዋል። በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት የሚያስችሉ ሀሳቦች የሚንሸራሸርባቸው የውይይት መድረኮች እንደሚካሄዱም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍኖ የቆየውን የፖለቲካ ስብራት ለመጠገን መሰል ትብብሮች ቁልፍ ሚና እንዳላቸውም ነው ያስረዱት። እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ ምክር ቤቱ ከአካዳሚው ጋር በፈጠረው ግንኙነት አገራዊ አስተዋጽኦን የሚያሳድግበት ልምድ የቀሰመ ሲሆን፤ ግንኙነቱ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል።   የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አቶ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው፤ ተቋማቱ በጋራ ለመስራት መወሰናቸው ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል። ተቋማቱ በጋራ ለመተግበር የያዟቸው ግቦች እንዲሳኩ ሁሉን አቀፍ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።    
በመዲናዋ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን፣ የወንጀል መከላከል ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
Apr 25, 2025 102
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች፣ የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዦች፣ የወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊዎች የአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታን በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ገምግመዋል።   በሁሉም ክፍለ-ከተሞች በተካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በተሽከርካሪ ስርቆት፣ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ በሀሰተኛ የብር ኖቶች ዝውውር፣ በበርካታ ሞባይልና ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች ስርቆት፣ በስፖኪዮ፣ በጎማ እና በሌሎች የመኪና መለዋወጫዎች ስርቆት የተጠረጠሩ ግለሰቦች እንዲሁም የ”IMEI” ማጥፊያ ማሽን ተጠቅመው የተሰረቁ ሞባይሎች እንዳይገኙ የሚያደርጉ፣ በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ተጠቅመው ዝርፊያ የሚፈፀሙ እና በርካታ ሽሻ ማስጨሻ ዕቃዎችን ይዘው የተገኙ ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል።   በተለይም በቂርቆስና በቦሌ ክፍለ ከተሞች በቅንጅት በተካሄደ ልዩ ኦፕሬሽን ተደራጅተው በመንግስት መሠረተ ልማቶች ላይ ዝርፊያ የፈፀሙ፣ በሞተር ሳይክል ሞባይል የሚነጥቁ፣ 12 የኤቲኤም ካርድ ከግለሰቦች በማታለል ወስዶ ገንዘብ የዘረፈ ተጠርጣሪ ግለሰብን ጨምሮ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸዉ በምርመራ እየተጣራ መሆኑ ተመላክቷል። በተካሄደው ኦፕሬሽን የከተማዋ ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ መሆኑንና ወንጀልም በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱ በግምገማው ላይ ተገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማን ፀጥታ እና ደኅንነት የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተደረገ ባለው የተቀናጀ ኦፕሬሽን የፀጥታ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር እና የማድረግ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ያደገ መሆኑንም ተነስቷል። የጋራ ኦፕሬሽኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በኦፕሬሽኑ የተገኙ ውጤችም እየተገመገሙ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያና ሞሮኮ በወታደራዊ ዘርፍ በትብብር ለመስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
Apr 25, 2025 126
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፦ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ባሬድ የተመራ ልዑካን ቡድንን ተቀብለው አነጋግረዋል። ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በ1955 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ እና ሞሮኮ ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በፓን አፍሪካዊ መንፈስ ለአህጉራዊ አንድነት የጋራ ቁርጠኝነት የታየበት ትብብር እንደሆነ ገልጸዋል።   ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ እና በራባት የተካሄደው የከፍተኛ ደረጃ ወታደራዊ ልዑካን ምክክርም ሁለቱ ሀገሮች በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ጉዳዮችን እንዲፈትሹ እድል ፈጥሮላቸው እንደነበርም አውስተዋል። የሞሮኮ ሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሞሐመድ ባሬድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት ምልክት ናት ብለዋል። ወታደራዊ ትብብሩ ሀገራቱ ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ለሚኖራቸው አስተዋፅኦ የጎላ ሚና እንዳለው አመልክተዋል። የመከላከያ ውጪ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ ሁለቱ ሀገራት በየቀጣናቸው ከሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በተጨማሪ በጋራ ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት በትብብር መስራት በሚችሉባት ሁኔታዎች ላይ መምከራቸውን ጠቁመዋል።   ከሞሮኮ ወታደራዊ ተቋማት በቴክኖሎጂ ሽግግር በሳይበር በአየር ኃይልና በባህር ኃይል ኢትዮጵያ ተሞክሮ መውሰድ እንደምትፈልግ አመልክተዋል። ሁለቱ ሀገራት በቀጣይ የመግባቢያ ስምምነት ይፈራረማሉም ብለዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የአየር ኃይል የባህር ኃይል የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም የሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ውይይቱን ተከትሎ የልዑካን ቡድኑ በሆሚቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪና በአየር ኃይል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን መጎብኘቱን የሀገር መከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል።
የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማሳካት መረባረብ ይጠበቅብናል - ከንቲባ ከድር ጁሃር
Apr 25, 2025 76
ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ እድሎችን ወደ ሃብት በመለወጥና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በመሰብሰብ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማሳካት መረባረብ ይጠበቅብናል ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ። በብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ለአስተዳደሩ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ያዘጋጀው የሶስት ቀናት የማስፈፀም አቅም ማጎልበቻ ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።   ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአስተዳደሩን ነዋሪዎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የፈቱ በርካታ ልማቶች ተከናውነዋል። በተለይም ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት በማጠናቀቅ ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ያደረጉ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል። እነዚህን ውጤቶች በላቀ ደረጃ ለማሳካት በየደረጃው የሚገኘው አመራር በጊዜ የለኝም መንፈስ በቁርጠኝነት መትጋት አለበት ብለዋል። ድሬዳዋ በምሥራቁ የሀገሪቱ ክፍል ሰፊ የገበያ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት እድሎች አሏት ያሉት ከንቲባው፤ እነዚህን እድሎች ወደ ሃብት በመለወጥና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በመሰብሰብ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማሳካት መረባረብ ይጠበቅብናል ነው ያሉት።   በብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው በየደረጃው የሚገኘው አመራር በየተቋማቱ ዲጂታል አሠራሮችን በመተግበር ለህብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅበታል ብለዋል። የህዝብን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የተጀመሩ ጥረቶችን ይበልጥ ለማሳደግ ለሶስት ቀናት የተሰጠው ዘመናዊ የአመራርነት ስልጠናም ወሳኝ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል። አመራሩ በቀሰመው ዕውቀት በመታገዝና የተናበበ ቅንጅት በመፍጠር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መረባረብ እንደሚጠበቅበትም ነው ያስገነዘቡት። ስልጠናውን የተሳተፉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮችም በቀሰሙት እውቀት በመታገዝ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት፣ የዲጂታል አገልግሎት እና የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ በቁርጠኝነት እንደሚተጉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ወደ ተሟላ ዘመናዊ የአቪዬሽን ተቋም ደረጃ ማደግ ችሏል - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
Apr 25, 2025 96
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦በጠንካራ ተቋማዊ ሪፎርም እየተገነባ ያለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ወደ ተሟላ ዘመናዊ የአቪዬሽን ተቋም ደረጃ ማደግ ችሏል ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ። ዋና አዛዡ በመከላከያ አዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ከሚገኙ የክፍለ ጦር አመራሮች ጋር በአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ተገናኝተው ውይይት አደርገዋል።   በውይይቱም ላይ እንደገለጹት ጠንካራ ተቋማዊ ሪፎርምን መነሻ አድርጎ የተነሳው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአመራሩ ጀምሮ እስከ ታችኛው አባላት ደረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለለውጥ ዝግጁ ሆነው በጋራ በመስራታቸው ምክንያት ወደ ተሟላ ዘመናዊ የአቪዬሽን ተቋም ደረጃ አድጓል። ውስጣዊ አንድነቱ የጠነከረ ብሎም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችል ሙያዊ አቅም ያለው ሰራዊት እንደ ተቋም መገንባቱን የጠቀሱት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በ2022 ከአፍሪካ ተመራጭ የአቪዬሸን ተቋም ለማድረግ ከያዝናቸው ውጥኖች መካከል አንዳንዶቹ ቀድመው እየተሳኩ ነው ብለዋል።   ጠንካራ ወታደራዊ መሪ ማለት በሰላም ጊዜ ሰራዊቱን ለውጊያ የሚያዘጋጅና በአነስተኛ ኪሳራ ትልቅ ድል የሚያመጣ መሆኑንም አስታውቀዋል። የክፍለ ጦር አመራሮችም የዘመኑን ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ መከተል እንዳለባቸው እንዲሁም የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ያገናዘበ አቅም ደረጃ ላይም ራሳቸውን ለማብቃት ሊተጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።   በመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ምክትል አዛዥ ለስልጠና ዲን ኮሎኔል ዮሐንስ መኮንን አመራሮቹ የአየር ኃይልን የስኬት ጉዞ እንደ መልካም ተሞክሮ እንደሚወስዱና ለሀገራዊ አላማ ተናበው እንዲሰሩ የሚያስችል ገንቢ ምክረ ሀሳብ ከአየር ኃይል አዛዡ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በዕለቱ የክፍለ ጦር አመራሮች በተቋሙ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የግዳጅ አፈፃፀም ተግባራትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በዞኑ ሰላምን በማፅናት ህዝቡ በልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፎውን እንዲያሳደግ እየተደረገ ነው
Apr 25, 2025 76
ጊምቢ፤ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ወለጋ ዞን የሰፈነውን ሰላም በማፅናት ህዝቡ በልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፎውን እንዲያሳደግ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ አስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ኮማንደር ነጋልኝ በቃብል ገለጹ። በአካባቢው የሰፈነው ሰላም ያለ ምንም ስጋት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውን እንድያደርጉ ምች ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የዞኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሀላፊው ኮማንደር ነጋልኝ፣ በዞኑ ሰላም ሰፍኖ ህዝቡም ሙሉ ትኩረቱ በልማት ስራዎች ላይ መሆኑን ተናግረዋል። በአካባቢው የነበረው ችግር የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ አዳጋች አድርጎት መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን የሰፈነው ሰላም በዞኑ ሁለንተናዊ ልማት ላይ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በዞኑ የሰፈነው ሰላም በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ በሙሉ አቅሙ የህዝቡን የልማት እንቅስቃሴ ማገዝ እንዲችል እድል መፍጠሩንም ተናግረዋል። በተለይም ዘንድሮ በክልል ደረጃ በተዘረጋው አዲሱ የቀበሌ አደረጃጅትም መንግስት ህዝቡን በቅርበት እንዲያገለግል እድል መፍጠሩንና ለዚህም የተገኘው ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። ህዝቡ በልማት ስራው የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ለማድረግ የሰፈውን ሰላም ማጽናትና ህዝቡ የበለጠ ሰላሙን መጠበቅ እንዲችል የማደራጀት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም አስረድተዋል። ኮማንደር ነጋልኝ አክለውም አሁንም የህዝብና የመንግስት የሰላም ጥሪ ያልተቀበሉ ታጣቂዎች ላይ የሚደረገው የህግ ማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች፤ በአካባቢው በሰፈነው ሰላም የተረጋጋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ተናግረዋል። ከነዋሪዎቹ መካከል የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪው አቶ መርዳሳ አለሙ፤ የተገኘው ሰላም በዘላቂን ለማፅናት ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ '''የሰፈነው ሰላም ከጸጥታ ስጋት ተላቀን ወደ ልማት ስራዎች ፊታችን እንድናዞር አድርጎናል'' ያሉት ደግሞ የጉሊሶ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሀዊኔ መራ ናቸው፡፡ በነበረው ችግር ዋነኛ ተጎጂ የነበሩት ሴቶችና ህጻናት እንደሆኑ አስታውሰው፤ ''አሁን በሰፈነው ሰላም እፎይታ አግኝተናል፤ ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆንም ሁላችን የሚጠበቅብንን እንወጣለን'' ብለዋል። ሌላው የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ ኤጀታ ጉተማ በበኩላቸው፤በአካባቢያቸው ሰላም ሰፍኖ ትኩረታቸው የልማት ስራዎች ላይ መሆኑን ተናግረዋል። የተገኘው ሰላም እንዲጸና ከጸጥታ አካላት ጋር የጀመሩትን ትብብር እንደሚያጠናክሩ የተናገሩት ደግሞ የጉሊሶ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሀብታሙ አብዳታ ናቸው፡፡ ነዋሪዎቹ፤ በዚህ ወቅት በአካባቢው የሰፈነው ሰላም ያለ ምንም ስጋት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውን እንድያደርጉ እንዳስቻላቸው አብራርተዋል።
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ለአፍሪካ ህብረት የድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ የተጠናከረ ድጋፍ እንዲደረግ ጠየቁ
Apr 25, 2025 98
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፡ -የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) አባል ሀገራት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ለአፍሪካ የድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ(አውሶም) ጠንካራ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ። የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) የሰላም አስከባሪ ኃይል አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሀገራት አስቸኳይ ጉባኤ ዛሬ በዩጋንዳ ካምፓላ ተጀምሯል። የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በጉባኤው ባደረጉት ንግግር የአውሶም ተልዕኮን የሚያግዝ ድጋፍ መዘርጋት እንደሚገባ ገልጸዋል። የቀጣናዊ ተቋሙ አባል ሀገራት ሽብርተኞችን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ሎጅስቲክስን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል። ለሶማሊያ የጸረ-ሽብር ዘመቻ የተቀናጀ እና በበቂ ሁኔታ በፋይናንስ መደገፍ የሚያስችል አካሄድ መከተል ይገባል ብለዋል። የሶማሊያ መንግስት እና የፀጥታ ኃይሎች አልሻባብን በመዋጋት ላመጡትን ለውጥ እውቅና የሰጡት ዋና ፀሐፊው የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠል ዘላቂ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ኢጋድ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን በአባል ሀገራት ዘላቂ ሰላም፣ ደህንነት እና ልማት እንዲሰፍን በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ነው ብለዋል ዋና ፀሐፊው። ኢጋድ ሰላሟ የተረጋገጠ እና ደህንነቷ የተጠበቀ ሶማሊያ ለመፍጠር የተያዘው ራዕይ እውን እንዲሆን ከሀገሪቷ ጎን በመቆም በትብብር እንደሚሰራ መግለጻቸቸውን ኢዜአ ከኢጋድ ያገኘው መረጃ ያመለክታል። አስቸኳይ ጉባኤው የፋይናንስ ማዕቀፎች እና ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀትን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ በሶማሊያ የሚኖረውን አጠቃላይ ቆይታ ላይ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል። በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢጋድ አባል ሀገራት፣ የቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም አጋሮች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ እና የግሪክ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል- አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
Apr 25, 2025 72
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ እና በግሪክ መካከል ያለው የመንግስታት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ። በግሪክ ፓርላማ አባልና የኦርቶዶክስ ኢንተርፓርሊያመንት ጉባኤ (IAO) ኃላፊ ማክስሞስ ቻራኮፖሎስ (ዶ/ር) የተመራው የልኡካን ቡድን ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ጉብኝት አድርጓል። የልዑካን ቡድኑ አቶ ታገሰ ጫፎ እና በምክር ቤቱ የኢትዮጵያ እና የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት የወዳጅነት ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይቷል። አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የሁለቱ አገራት ለረጅም ጊዜ የቆየ የመንግስታት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከግሪክ ጋር ንግድና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ልምድ መቅሰም እንደምትፈልግና ያላትን መልካም ተሞክሮም ለማካፈል ዝግጁ ናት ብለዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ እና የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት የወዳጅነት ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ እና ግሪክ ለረጅም አመታት ያላቸውን ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል። ሁለቱ ሀገራት በቴክኖሎጂ፣ በንግድ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢነርጂ እና በተለያዩ ዘርፎች ተባብረው ቢሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ አንስተዋል። የሁለቱ ሀገራት ምክር ቤቶች ተቀራርበው በመስራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። በግሪክ ፓርላማ አባልና የኦርቶዶክስ ኢንተርፓርሊያመንት ጉባኤ (IAO) ኃላፊ ማክስሞስ ቻራኮፖሎስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ግሪክ በቱሪዝም እና በግብርናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ በርካታ ልምዶችን መቅሰም እንደምትፈልግ እና በዘርፉ አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል። ግሪክ በኮንስትራክሽን፣ በባህር ትራንስፖርት እና በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል እንደምትሻም አመልክተዋል። የግሪክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንስትመንት ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ ኃላፊው መናገራቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የህልውና ጉዳይ በሆነው የባህር በር ጥያቄ ላይ የመንግስትን የዲፕሎማሲ ጥረት እንደግፋለን - የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
Apr 25, 2025 120
ሰመራ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት የህልውና ጉዳይ በሆነው የባህር በር ጥያቄ ላይ አቋም በመያዝ የጀመረውን የዲፕሎማሲ ጥረት የሚደግፉት መሆኑን የተለያዩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ። በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ እያንቀሳቀሰች የምትገኘው ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የባህር በሯን በማጣቷ ለከፍተኛ ወጭ በመዳረግ ዋጋ እየከፈለች መሆኑ ይታወቃል። ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት የብዙ ህዝብና የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ሀገር ያለ ባህር በር ተዘግታ መኖር የለባትም በሚል መንግስት ፅኑ አቋም ይዞ እየሰራ ይገኛል።   በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አቋም በመያዝ መንግስት የጀመረው የዲፕሎማሲ ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል። በአፋር ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ (አነግፓ) ሊቀ መንበር ሐንፈሬ አሊሚራህ፤ ኢትዮጵያዊያን ቀይ ባህርን በቅርበት እየተመለከቱ የባህር በር ተጠቃሚ አለመሆናቸው በየትኛውም መመዘኛ ትክክል አይደለም ብለዋል። በመሆኑም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በመንግስት እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው በተለይም የባህር በር ጥያቄው የሁላችንም ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል። በዚህ ረገድ አነግፓ የመንግስትን የዲፕሎማሲ ጥረት በማገዝ ከፊት የሚሰለፍ መሆኑን አረጋግጠው የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም ማስቀደም የሁላችንም አጀንዳ መሆን አለበት ብለዋል። የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር(አርዱፍ) ምክትል ሊቀ መንበር አቶ መሐመድ አወል ወግሪስ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑ እርግጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል።   በመሆኑም መንግስት የጀመረውን የዲፕሎማሲ ጥረት በማገዝ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን በሚቻለው ሁሉ እግዛ እናደርጋለን ብለዋል። የአርጎባ ብሄረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አብዴን)ፀሐፊ አቶ በክሪ አህመድ፤ የባህር በር ጥያቄው ለኢትዮጵያዊያን የህልውና ጉዳይ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው ሲሉ ተናግረዋል። በመሆኑም የመንግስትን የዲፕሎማሲ ጥረት በማገዝ ያለምንም ልዩነት ለሀገር ህልውናና ብሄራዊ ጥቅም በጋራ እንሰራለን ብለዋል። የመንግስትን የዲፕሎማሲ ጥረት ፓርቲያቸው መሉ በመሉ የሚደግፈውና ለተፈፃሚነቱ የሚያግዝ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም