ስፖርት
ኢትዮጵያ በሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር የሩጫ ውድድር ሁሉንም ሜዳሊያዎች አሸነፈች
Apr 27, 2025 16
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ በ5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ስፖርታዊ ውድድር ኢትዮጵያ በሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር የሩጫ ውድድር ሁሉንም ሜዳሊያዎች አሸነፈች። የኢትዮጵያ ፖሊስ የተመሰረተበትን 116ኛ ዓመት በዓል በማስመልከት 5ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር የመክፈቻ መርሃ ግብር ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተከናውኗል።   በመክፈቻ መርሃ ግብሩ የሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር እና የወንዶች የ400 ሜትር የዱላ ቅብብል የሩጫ ውድድር ተካሂዷል። በሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ወርቅነሽ መሰለ፣ የኔነሽ ሺመክት እና ማተቤ ፍቃዱ በቅደም ተከተል ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት ሁሉንም ሜዳሊያዎች ወስደዋል። በወንዶች የ400 ሜትር የዱላ ቅብብል ውድድር ደግሞ ኬንያ አንደኛ ኢትዮጵያ ሁለተኛ እንዲሁም ታንዛኒያ ሶስትኛ በመውጣት ውድድሩን አሸንፈዋል።   አሸናፊዎቹ አትሌቶች የሜዳሊያ ሽልማታቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እጅ ተቀብለዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት ሀገራት የሚሳተፉበት 5ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት ስፖርታዊ ውድድር እስከ ሚያዚያ 26/2017 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላል።
ሞገስ ጥዑማይ እና ገመኔ ማሚቴ የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር አሸናፊ ሆኑ
Apr 27, 2025 45
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድርን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ክለብ ሞገስ ጥዑማይ በወንዶች እንዲሁም የኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማዋ ገመኔ ማሚቴ በሴቶች አሸናፊ ሆነዋል። መነሻና መድረሻውን በመስቀል አደባባይ ያደረገው 4ኛ ዓመት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የ2017 ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሂዷል። በዝግጅቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይን ጨምሮ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። በውድድሩም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ክለብ ሞገስ ጥዑማይ በወንዶች እንዲሁም የኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማዋ ገመኔ ማሚቴ በሴቶች የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር አሸነፊ ሆነዋል። በዚህም በ10 ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያ ታምርት የወንዶች የሩጫ ውድድር፦ 1ኛ. ሞገስ ጥዑማይ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የወርቅ ሜዳሊያ እና የ300 ሺህ ብር፣ 2ኛ.ጅራታ ሌሊሳ በግል የብር ሜዳሊያና የ200 ሺህ ብር እንዲሁም 3ኛ. ሲዳ አማና ከሸገር ከተማ የነሀስ ሜዳሊያ እና የ100 ሺህ ብር ሽልማት አሸናፊ በመሆን ከኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እና ከኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ እጅ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተረክበዋል።   በተመሳሳይ በ10 ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያ ታምርት የሴቶች የሩጫ ውድድር፦ 1ኛ. ገመኔ ማሚቴ ከኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ የወርቅ ሜዳሊያ እና የ300 ሺህ ብር፤ 2ኛ.አበዙ ከበደ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብር ሜዳሊያና የ200 ሺህ ብር እንዲሁም፤ 3ኛ. ማርታ አለማየሁ በግል የነሀስ ሜዳሊያ እና የ100 ሺህ ብር አሸናፊ በመሆን ከባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እና ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ዕጅ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተረክበዋል። የሩጫ ውድድሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን ውድድሩም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 4ኛ ዓመት ዝግጅትን አስመልክቶ የተሰናዳ መሆኑ ተገልጿል።
ተጠባቂው የለንደን ማራቶን
Apr 27, 2025 39
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 19/2017 (ኢዜአ)፡- 45ኛው የለንደን ማራቶን ዛሬ ረፋድ ላይ ይካሄዳል። በሁለቱም ጾታዎች የሚደረጉ የዓለም የአትሌቲክስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል። በሴቶች አትሌት ትዕግስት አሰፋ እና አትሌት ሲፋን ሀሰን የሚያደርጉት ፉክክር በጉጉት እንደሚጠበቅ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል። ሁለቱ አትሌቶች በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በማራቶን ውድድር እስከ መጨረሻው እልህ አስጨራስ ፉክክር አድርገው ሲፋን አንደኛ፣ ትዕግስት ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው የሚታወስ ነው። አትሌቶቹ ከኦሊምፒኩ መልስ ዳግም በወሳኝ የአትሌቲክስ መድረግ ላይ ተገናኝተዋል። አትሌት ትዕግስት 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሴኮንድ በርቀቱ የዓለም ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት ባለቤት ናት። ሲፋን 2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ የዓለም ሶስተኛ ፈጣን ሰዓትን አስመዝግባለች።   ኬንያዊቷ የማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ሩት ቼፕጌቲች እና የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ የሆነችው ሌላኛዋ ኬንያዊ አትሌት ፔሬዝ ቼፕቺርቺር በውድድሩ ላይ አይሳተፉም። ሌላኛዋ ኬንያዊ ጆይስሊን ጄፕኮስጌ የሀገሬው ሰዎች ተስፋ የጣሉበት አትሌት ናት። በወንዶች በፓሪስ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው አትሌት ታምራት ቶላ እንዲሁም ኬንያዊው ኢሊውድ ኪፕቾጌ እና ሌላኛው የሀገሩ ልጅ አሌክሳንዳር ሙቲሶ ሙናዮ የማሸነፉን የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል። ሙናዮ የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ነው።   ዩጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ ሌላኛው ተጠባቂ አትሌት ነው። አንጋፋው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በጉዳት ምክንያት ከውድድሩ ውጪ መሆኑ የሚታወስ ነው። በሁለቱም ጾታዎች የሚያሸንፉ አትሌቶች በተመሳሳይ የ55 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ያገኛሉ። እ.አ.አ በ1981 የተጀመረው የለንደን ማራቶን በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የጎዳና ላይ ውድድር ሲሆን በዓለም ላይ ተጠባቂ ከሆኑ ውድድሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ነው።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ለኢትዮጵያ ፖሊስ ስፖርተኞች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አስረከቡ
Apr 26, 2025 57
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በአምስተኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ድርጅት የስፖርት ውድድር ላይ ለሚሳተፉ የኢትዮጵያ ፖሊስ ስፖርተኞች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አስረክበዋል። ኮሚሽነር ጀነራል በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት መንደር በመገኘት ባደረጉት ንግግር የወከላችሁት ብዙ መሥዋዕትነት የተከፈለበት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ነው ብለዋል። ስለሆነም በስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ በመሆን የወከላችሁትን መላ የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት ክብር ከፍ በማድረግ በድል አድራጊነት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እንድታውለበልቡ በማለት ስፖርተኞቹን ማሳሰባቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል። 5ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት የስፖርት ውድድር ከነገ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል። ውድድሩ የተዘጋጀው 116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምስረታ በዓል ቀንን በማስመልከት ነው። በስፖርት ውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የጂቡቲ፣ የኬንያ፣ የታንዛኒያ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የዩጋንዳ እና የሩዋንዳ የፖሊስ ተቋማት በስድስት የስፖርት አይነቶች ይሳተፋሉ። አትሌቲክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ዒላማ ተኩስ፣ ቦክስ፣ ዳርት እና እጅ ኳስ ውድድሩ የሚካሄድባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው።
የክሪስታል ፓላስ እና የአስቶንቪላ የኤፍኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ 
Apr 26, 2025 65
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፡- የእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል። በዚህም ክሪስታል ፓላስ ከአስቶንቪላ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ15 በዌምብሌይ ስታዲየም ይጫወታሉ። በሩብ ፍጻሜው ክሪስታል ፓላስ ፉልሃምን 3፣ አስቶንቪላ ፕሪስተን ኖርዝ ኢንድን በተመሳሳይ 3 ለ 0 በማሸነፍ ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል። ክሪስታል ፓላስ የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን አንስቶ አያውቅም። በታሪኩ ሁለት ጊዜ ለፍጻሜ አልፎ በሁለቱም አጋጣሚ በማንችስተር ዩናይትድ ተሸንፏል። ተጋጣሚው አስቶንቪላ የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን ሰባት ጊዜ ከፍ በማድረግ ስኬታማ ከሆኑ ክለቦች መካከል ይጠቀሳል። የ46 ዓመቱ አንቶኒ ቴይለር ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል። ሁለተኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ነገ በኖቲንግሃም ፎረስት እና ማንችስተር ሲቲ መካከል ይደረጋል። የእንግሊዝ የኤፍኤ ካፕ ውድድር እ.አ.አ 1871 የተጀመረ ሲሆን 154 ዓመታትን ያስቆጠረ የዓለማችን አንጋፋው የእግር ኳስ ውድድር ነው።
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ 
Apr 26, 2025 54
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፡- የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 34ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል። የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ቼልሲ እና ኤቨርተንን በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ያገናኛል። ቼልሲ በ57 ነጥብ 6ኛ ደረጃን ሲይዝ ኤቨርተን በ38 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ጨዋታው ሰማያዊዎቹ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፏቸውን ለማሳካት በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ የሚባል ነው። ኤቨርተን ማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በጥንካሬ ለማጠናቀቅ ብርታት የሚሆነውን ውጤት ያስገኝለታል። ኒውካስትል ዩናይትድ ከኢፕስዊች ታውን፣ ብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢዮን ከዌስትሃም ዩናይትድ፣ ሳውዝሃምፕተን ከፉልሃም እና ዎልቨርሃምፕተን ዎንድረርስ ከሌይስተር ሲቲ በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይጫዋታሉ። ነገ ሊቨርፑል ከቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ቦርንማውዝ ከማንችስተር ዩናይትድ ይጫወታሉ። ሊቨርፑል በነገው ጨዋታ ካሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ያረጋግጣል።
ክልል አቀፍ የእግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮናው በታርጫ ከተማ ይካሄዳል
Apr 26, 2025 46
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ)፦የደቡብ ኢትዮጵያ ምዕራብ ህዝቦች ክልል የእግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ከነገ ጀምሮ በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ ይካሄዳል። ሻምፒዮናው "ስፖርታዊ ጨዋነት ለክልሉ ህዝቦች ትስስር እና አንድነት!" በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል። ውድድሩ በክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ እና በክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጋራ የተዘጋጀ ነው። የቢሮው ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ ለሻምፒዮናው አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። የሻምፒዮናው አላማ በተያዘው ዓመት በሚደረገው ሀገር አቀፍ ሻምፒዮና ክልሉን የሚውክሉ ክለቦችን ለመምረጥ መሆኑን አመልክተዋል። ውድድሩ ከስፖርታዊ ሁነቱ ባሻገር ማህበራዊ ትስስር ለማጎልበት እና ትውውቅን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግረዋል። በውድድሩ ላይ ከክልሉ ስድስት ዞኖ የተወጣጡ ከ450 እስከ 600 ስፖርተኞች እንደሚሳተፉም ነው የጠቆሙት። ስፖርተኞች እና ሌሎች የውድድሩ ተሳታፊዎች ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ ሁኔታ ውድድራቸውን እንዲያደርጉ እና ትስስራቸውን እንዲያጎለብቱ ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ተጠባቂው የኤል ክላሲኮ ደርቢ 
Apr 26, 2025 68
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18 /2017 (ኢዜአ)፦ በስፔን ኮፓ ዴል ሬይ (የንጉሱ ዋንጫ) ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ዛሬ የሚያደርጉት የፍጻሜ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 5 ሰዓት በሲቪያ ከተማ በሚገኘው ዴላ ካራቱጃ ስታዲየም ይካሄዳል። በግማሽ ፍጻሜው ባርሴሎና አትሌቲኮ ማድሪድን እንዲሁም ሪያል ማድሪድ ሪያል ሶሲዬዳድን አሸንፈዋል። የባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ታሪካዊ ተቀናቃኝነት ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ ነው። ሁለቱ ክለቦች እ.አ.አ በ1902 ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ባርሴሎና 3 ለ 1 አሸንፏል። ቡድኖቹ የወዳጅነትን ሳይጨምር እስከ አሁን 259 ጊዜ እርስ በእርስ የውድድር ጨዋታዎችን አድርገዋል። በዚህም ሪያል ማድሪድ 105 ጊዜ ሲያሸንፍ ባርሴሎና 102 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 52 ጊዜ አቻ ወጥተዋል። ሁለቱ ክለቦች በስፔን ካፓ ዴል ሬይ ሲገናኙ የዛሬው ለ37ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 37 ጨዋታዎች ባርሴሎና 16 ጊዜ አሸንፏል። ሪያል ማድሪድ 13 ጊዜ ባለድል ሆኗል። 8 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል። ባርሴሎና የኮፓ ዴል ሬይ ዋንጫን 31 ጊዜ በማንሳት የበላይነቱን ይዟል። ሪያል ማድሪድ ለ20 ጊዜ ውድድሩን አሸንፏል። ሁለቱ ክለቦች በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ባርሴሎና ጨዋታዎቹን አሸንፏል። ባርሴሎና በስፔን ላሊጋ 4 ለ 0 እንዲሁም በስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ፍጻሜ 5 ለ 2 ሎስ ብላንኮሶቹን ማሸነፉ የሚታወስ ነው። ቡድኖች ካላቸው ወቅታዊ ብቃት አንጻር ባርሴሎና ጨዋታውን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝቷል። የ39 ዓመቱ ሪካርዶ ደ ቡርጎስ ቤንጎሲ ተጠባቂውን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም