መጣጥፍ - ኢዜአ አማርኛ
መጣጥፍ
ደመና ማበልጸግ በኢትዮጵያ የአራት ዓመት ጉዞና ስኬት
Apr 25, 2025 340
ደመና ማበልጸግ(Cloud Seeding) ምንድን ነዉ? የደመና ማበልጸግ በደመና ውስጥ ያለውን የዝናብ መጠን ወይም ዓይነት የሚለውጥ(የሚጨምር) የአየር ሁኔታ መቀየሪያ ዘዴ ነው። ይህም ማለት በመሰረታዊነት ዝናብ ሊሆን የሚችልን ነገር ግን አቅም ያጣን ደመና ወደ ዝናብ እንዲቀየር በማፋጠን መዝነብን የመጨመር ተግባር ነው። የደመና ማበልጸግና ማዝነብ ቴክኖሎጂ በ1940ዎቹ የተጀመረ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ። ደመና ማበልጸግ ቴክኖሎጂን ለመተግበር የተለያዩ መንገዶች ቢኖሩም በዋናነት በአውሮፕላን፣ ባሎን፣ ሮኬት፣ ድሮን እና መሬት ላይ በሚቀመጥ ጀነሬተር በመታገዝ ደመና ላይ ጨው መሰል ብናኝ በመርጨት በዝናብነት ወደ ምድር የማይወርድ ደመናን አቅም ኖሮት እንዲዘንብ ወይም እንዲወርድ ማድረግ ነው። ይህ ሂደት ሰው ሰራሽ ሲሆን የደመና መዝነብን አቅም ከ15-30 በመቶ በማሳደግ ዝናብ እንዲከሰት የማድረግ አቅም አለው። ይህ ቴክኖሎጂ በተለያዩ ሀገራትና ጊዜያት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በ2013 ዓ.ም ሀገራችን ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጋር ባላት ጠንካራ ግንኙነትና ትብብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ችሏል። በወቅቱም ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ማዕከል በመጣ አውሮፕላንና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የአየር ላይ ኦፕሬሽን ተደርጓል፤ የማቴሬሪያልና የሙያ ድጋፍ ተገኝቷል።ድርቅ አጋጥሞ በነበረበት በቦረና ጉጂ አካባቢ የዝናብ ማዝነብ ኦፕሬሽን ተከናውኗል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚሰጠው አቅጣጫ ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የተለያዩ ተቋማትን አስተባብሮ ሀገራችን የቴክኖሎጂው ባለቤት የምትሆንበትን መሰረተ ልማትና ሲስተም እንዲያበለጽግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ሲስተሙን ከመጠቀም አልፎ ከዚህ ቀደም በቻይና ተመርቶ ስንጠቀምበት የነበረው የደመና ማበልጸጊያ(ማዝነቢያ) ግራውንድ ጀነሬተር በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስተባባሪነት በሀገራችን በሙሉ አቅም መሥራት ተችሏል። በራስ አቅም ልንሰራው በመቻላችን የቴክኖሎጂ ባለቤትነታችንን ከማረጋገጥ ባሻገር የውጭ ምንዛሪን በማዳን ከፍተኛ አገራዊ ጥቅም ሊገኝበት ችሏል። በ2015 ዓ.ም የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ውሎ በሀገራችን በዝናብ እጥረት የሚያጋጥመውን አደጋ ለመከላከል ለዝናብ ማዝነቢያ የግራውንድ ጄኔሬተር ማምረቻ የሚሆን የፕሮጀክት በጀት መድቧል። የፕሮጀክት በጀቱንም የማምረት ሥራው ሂደትና ስኬት እየታየ በሁለት ዙር ለመልቀቅ ከኢፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር ውል በተፈራረመው መሰረት በመጀመሪያው ዙር 20 ግራውንድ ጀነሬተር ማምረት ሥራ በስኬት በማጠናቀቅ በኦሮሚያ ክልል በሚፈለግበት ወረዳዎች በሟቋቋም ወደ ኦፕሬሽን እንዲገቡ ተደርገዋል። በሁለተኛው ዙር 25 የግራውንድ ጀነሬተሮቹን የማምረት ሥራው ተጠናቋል፡ ወደ ኦፕሬሽን እንዲገቡም ተደርገዋል። በአጠቃላይ 45 ጄኔሬተሮች በማምረት የዝናብ እጥረት ለሚያጋጥማቸው ቦታዎች (ደቡብና ምሥራቅ ኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞን፣ በሶማሊ ክልል፣በእንጦጦ ተራራ) ተተክሏል። የአየር ንብረት እና ክላውድ ሲዲንግ መሰረታዊ እውቀት፣የሲስተም ተከላና ኦፕሬሽን በመስክና በታቀደ ስልጠና አቅም ተገንብቷል። ድሮንን በመጠቀም ሙከራዎች ተደርገዋል። በሚቀጥሉት ጊዜያት በአየር ላይም ኦፕሬሽን ስናደርግ ቴክኖሎጂን በራስ አቅም፣ ባለሙያና ቴክኖሎጂ ለመስራት ጥናትና ትግበራው የሚቀጥል ይሆናል። በአገር ደረጃ የሚመለከታቸውን ተቋማት በማሳተፍ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትና ተጠቃሚነታችንን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ምርምርና ከፍ ያለ ሥራ ይሰራል። የደመና ማበልጸግ በኢትዮጵያ ፕሮጀክት በዋናነት በኦፕሬሽናልና በተግባራዊ ምርምር ቴክኖሎጂን የመጠቀም፣አስቻይ መሰረተ ልማት የማቋቋም፣ የደመና ማበልጸግ ቴክኖሎጂ ልማትን በሚያሳልጡ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ተልዕኮውን የሚፈጽም ነው። ይህ ፕሮጀክት ወደ ስራ ሲገባ የተለያዩ ዓላማዎችን አንግቦ ሲሆን የመጀመሪያው በሀገራችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ከባለድርሻ አካል ጋር በመሆን እገዛ ማድረግ፤ በምርምር ፣ ልማት እና ትግበራ ላይ የተመሰረተ ዳመናን ማልማት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ማስቻል ፣በዘርፉ ልህቀት ማዕከል ማቋቋም ነው። ከዚህ በተጨማሪ የዳመናን ማልማት ምርምር፣ ልማት እና ትግበራን ለማሳለጥ የሚያግዙ ሀገራዊ የፖሊሲና የመሠረተ-ልማት ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ማቅረብ፤ እንዲሁም በዳመና ልማት ዙሪያ የሚሰማሩ ባለድርሻ አካላት እና የተቋማት ትስስርን ምቹ ምህዳር መፍጠር ነው።
ሀዘንና ደስታ የተሰናሰሉበት ትዕይንተ ጥበብ - "ኩርፍወ"
Apr 23, 2025 425
(በእንዳልካቸው ደሳለኝ - ከኢዜአ ወልቂጤ ቅርንጫፍ) "ኩርፍወ ጨዋታ" በጉራጌ የተለያዩ ድራማዊ ትዕይንቶች የሚገለፁበት ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ትውፊታዊ እሴት ነው። ይህ ትውፊታዊ ክንዋኔ ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት እንደተጀመረም ከአፈ ታሪክ መረዳት ይቻላል። ይህ ጨዋታ አዝናኝና ማራኪ እንዲሁም ብዙ ጊዜያትን ካስቆጠሩ ባህላዊ ጭፈራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው። ሀዘንና ደስታን አንድ ላይ በማሰናሰል የሚተገበር ሲሆን ተጀምሮ እስኪያልቅም የሚያጓጉ ትዕይኖች ይታዩበታል። "የኩርፍወ ጨዋታ" ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ፣ ሞትና ትንሳኤ ጋር ተያይዞ የሀዘንና ደስታ መግለጫ ነው። ለሁለት ሳምንታት በዙር ይከወናል። የመጀመሪያው በሰሞነ ህማማት ተጀምሮ እስከ ትንሳኤ የሚቆይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከትንሳኤ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሳኤ ይሆናል፡፡ ይሄኛው ዙር ልጃገረዶቹን ብቻ ሳይሆን ወጣቶች እንዲሁም እናትና አባቶችን ጭምር የሚያሳትፍ ነው። ከትንሳኤ በኋላ መጫወትን ይመርጡታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በደስታ ለመጫወት፣ የፍስክ ምግብና መጠጥንም መጠቀም ስለሚያስችል ነው። የ"ኩርፍወ ጨዋታ" መከወኛ ስፍራ ጨፌ ወይም ወንዝ በሚገኝበት አካባቢ ሲሆን ልጃገረዶች ከየቤታቸው ሲወጡ ተጋጊጠውና አምረው ደምቀው መታየት ስላለባቸው ሁሉም ባህላዊ የክት ልብሳቸውን ለብሰውና ተውበው ይገኛሉ። ኩርፍው አስደናቂ ከሆኑ ገፅታዎቹ መካከል ሁለት መልኮችን አንድ ላይ አሰናስኖ ማንፀባረቁ ነው። የልጃገረዶቹ የእጅ እንቅስቃሴና የእግር አጣጣል በጉራጌዎች ለጀግና የሚከወነውን "ወርኮ" የተሰኘ ሙሾ የሚያንጸባርቅ ሲሆን ዜማው ደግሞ የደስታ ቅላፄ መሆኑ ነው። የኩርፍወ ጨዋታ የራሱ ዜማ እና ግጥም ያለው ሲሆን ከዜማ አውራጇ ቀጥሎ ሁሉም ተጫዋች አዝማቹን ተቀባብለው ያዜማሉ። አዝማሪ፡- ተቀባዩ ኩርፍወ ኩርፍወ (2×) ኤዋዬ ኩርፎ ኩርፍወ ኩርፎ ኩርፎ ዋዬ ኩርፎ ኩርፎ ሞቴም ባማማቴ ጎር ቲገባ ዘር ይገባ እንደገና በተለየ ዜማ ኩርፍወ -----------------------ዋይ (2×) ኩርፍወ በሞቴ ዃም ባማማቴ ውርሰንበት ገባቴ ......... እያሉ ረዘም ባሉ ግጥሞች ያዜማሉ። ዜማና ግጥሞቹ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ በቅብብሎሽ የመጡ ናቸው። የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ልጃገረዶች ለምልሞና ማራኪ ገጽታ ይዞ በበልግ ወራት በስፋት በሚበቅለው "አምባሬ" ከተባለው የተክል ቅጠል ዝርያ በማገልደም ይጫወታሉ ብለዋል። ጨዋታው በዞኑ በይበልጥ በምሁር አክሊል ወረዳ እንደ ሚዘወተርም አመላክተዋል። ልጃገረዶቹ አምባሬ የሚባለው ተክል ቅጠል ከእነስሩ ነቅለው በመሸንሽን ወገባቸው ላይ አስረው ልክ እንደ ጉራጌ ባህላዊ ለቅሶ እንቅስቃሴ እጆቻቸውን ዘርግተው እግራቸውን ደግሞ ከመሬት ከፍና ዝቅ በማድረግ ነው ሚጫወቱት።ልጃገረዶች ከየቤታቸው ሲወጡ ባህላዊና የክት ልብሳቸውን ከመልበስ በተጨማሪ በአምባር እና በአልቦ ጌጦች ተሽቆጥቁጠው ፀጉራቸውን ሹርባ በመሰራት ከየአቅጣጫው ወደዚሁ ስፍራ ይተማሉ ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ መከራና ሞት በደስታ መቀየሩን በጭፈራው ይጎላል ነው ያሉት። ኩርፍወ ከሌሎች ባህላዊ የጉራጌ ባህላዊ እሴቶች የሚለየው ራሱን የቻለ ዜማ ፣ ግጥም እና የክዋኔ ስርዓት ያለው መሆኑን ነው። የ"ኩርፍወ ጨዋታ" ማሳረጊያ ላይ ልጃገረዶች አምቾን ወንዶች በማያገኙት ቦታ ላይ ደብቀው ይቀብራሉ። የደበቁትን አምቾ ወንዶች ካላገኙት የልጃገረዶች የወደፊት መፃኢ ዕድል ብሩህ ተስፋ እንዳለው፤ ካገኙት ደግሞ ለወንዶች የተሻለ ጊዜ ይመጣል ተብሎ እንደሚታመን ወይዘሮ መሰረት ይጠቅሳሉ። ይህ እሴት ጥናት እና ምርምር እንዲደርግበት እንዲሁም ለዘመናት የዘለቀው ድራማዊ ስርዓቱ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲሉም ተናግረዋል ። በዞኑ የኩርፍወ ጨዋታ ከሚዘወተርበት በዋናነት የሚጠቀሰው የምሁር አክሊል ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳህሉ ወልደማርያም በበኩላቸው ኩርፍወ እርስ በርስ የሚያቀራርብ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴት የሚያንፀባርቅ ነው ብለዋል። አብሮነትና አንድነትን ከመስበክ አንጻር ያለው ሚና የላቀ መሆኑን አውስተው ባህሉ በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ ቢቆይም ከነበረበት እንዲያንሰራራ ተደርጓል ነው ያሉት። ልጃገረዶች በኩርፍወ ጨዋታ ድራማዊ ትዕይንትን በማሳየት በአንድ በኩል ደስታቸውን ሲያንጸባርቁ በሌላ ጉኑ ሲያዝኑ ይስተዋላል። ጨዋታው የሰሙነ ህማማት የሚሆንበት ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁዳውያን የደረሰበት መከራ፣ ስቃይና ሞት ከዚያም የክርስቶስ ትንሳዔን ለማመላከት ነው። ባህላዊ ትውፊቱ ይዘቱን ሳይለቅ በየአካባቢው እንዲተገበርና የቱሪስት መስህብ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራም መሆኑን ነው አቶ ሳህሉ የገለጹት። አቶ አለምይርጋ ወልዴ ከልጅነታቸው ጀምሮ ልጃገረዶች ኩርፍወን ሲጫወቱ መመልከታቸው እና በአሁኑ ወቅት ከዚህ እሴት ጋር ተያይዞ መፅሀፍ ለማሳተም እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ። እንደእሳቸው ገለጻ ኩርፍወ ሁለት ኩነቶችን የያዘ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል መሰቀሉንና ሞትንም አሸንፎ ከመቃብር መነሳቱን ምክንያት በማድረግ የሚከወን ነው። በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በሰሞነ ህመማት ሀዘንን በኩርፍወ እንጉርጉሮ ይገልፃሉ። ከህማማት መጀመሪያ እስከ ስቅለት ባለው ጊዜ በጉራጌ ለጀግና "ወርኮ" በሚባለው የሙሾ ሥርአት መሰረት ልጃገረዶች ሲያዜሙ ይስተዋላል። ከትንሳኤ እለት እስከ ዳግማዊ ትንሳኤ ደግሞ የኩርፍወ አጨፋፈር፣ ዜማና ግጥሞች ለየት ባለ መልኩ ነው የሚቀርቡት። የጌታን መነሳት ምክንያት በማድረግ ደስታቸውን የሚገልጹበት ነው። ከትንሳኤ እስከ ዳግማዊ ተንሳኤ የሚያዜሙት ዜማ ከሰሞነ ህማማት ልዩነት አለው። የሚበዛ ትዕይንት የሚበዛውና ጭፈራ ያለው መሆኑንም ነው የተናገሩት። ወይዘሮ ጀምበርነሽ አርጋ በምሁር አክሊል ወረዳ ግናብ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። የኩርፍወ ጨዋታ በልጅነታቸው አምረውና ደምቀው ያሳለፉት ውብ ባህላዊ ስርዓት መሆኑን ያነሳሉ። የኢየሱስ ክርስቶስ በእለተ አርብ የደረሰበተን ሞት እና ስቃይ በማስመልከት ሀዘናቸውን የሚገልጹበትና ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱን የሚያሳየው ጫወታ ላይ ከመሳተፍ ባለፈ ከየቤታቸው ምግብ በማዋጣት በጋራ በልተውና ጠጥተው ያሳልፉበት ባህላዊ እሴት እንደ ነበር አስታውሰዋል። ይህ እሴት እንዳይጠፋ ዛሬ ላይ ለወጣት ሴቶች ለማሸጋጋር ልምዳቸውን እያጋሩ መሆኑን ነው የገለጹት። በወረዳው ግናብ ቀበሌ የምትኖረውና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኩርፍወ ጨዋታ ላይ በንቃት እየተሳተፈች መሆኗን የተናገረችው ደግሞ ወይዘሪት ሰላም ምትኩ ናት። የኩርፍወ ጨዋታ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቶችን አጣምሮ የያዘ ልዩ ትዕይንት እንደሆነ አንስታ ጭፈራው፣ ዜማው እና ድራማዊ ትዕይንቱ ይበልጥ እንደሚስባት ተናግራለች። ከበሮዋን ይዛ፣ ማስጌጫ ቅጠሉን በወገቧ አገልድማ በዜማና ጭፈራ ወጣት ወንዶች በተገኙበት ከሰሞነ ህማማት እስከ ዳግማዊ ትንሳኤ ትውፊታዊ ስርአት በጠበቀ መልኩ እንደምታሳልፍም አውስታለች። መንግስት ይህን ባህላዊ እሴት ለመታደግ እየሰራ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ወይዘሪት ሰላም አመላክታለች። ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል ኑረዲን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀት ክፍል ተጠሪና የቋንቋ መምህር ናቸው። ኩርፍወ በትዕይንት የተሞላና ለረጅም ዘመናት በቅብብሎሽ የተሻገሩ ግጥሞች አሉት ይላሉ። ልጃገረዶቹ ደብቀው የሚቀብሩትን አሚቾ (የኮባ ስር የውስጠኛው ክፍል) ለማግኘት የሚደረገው ግብግብ። የተደበቀው እንዳይገኝ ቦታውን ለማሳት የሚደረግ ጥረት። ወንዶች የተቀበረበት ነው ብለው የሚያስቡትን ቦታ ማሰሳቸው የትዕይንቱ አካላ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ወንዶች የተደበቀውን አሚቾ ፈልገው ካገኙት ዘመኑ ለእነሱ ገዳም እንደሚሆን ሲታመን ካላገኙት ደግሞ የሴቶች መልካም ዘመን ነው ተብሎ ይታሰባል። የኩርፍወ ጨወታ ባለቤቶች ልጃገረዶች እንደመሆናቸው መጠን ወደፊት ስለሚገጥማቸው ትዳርም ጭምር መልካምነት የተቀበረው አሚቾ የማሳየት ብቃት ይኖረዋል ተብሎ ስለሚታመን እጅግ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ነው ጨዋታውን የሚያስኬዱት። ይህ ትዕይንት ዘርፈ ብዙ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ሀላፊነቱን ለመወጣት ይሰራል ሲሉም ነው ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል የገለጹት።
ዝነኛው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ የዓለም የክላሲካል ሙዚቃ አዋርድ ሽልማት አገኘ
Apr 16, 2025 303
አዲስ አበባ ፤ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ):- ዝነኛው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ በሩሲያ ሞስኮ በተካሄደው “ብራቮ አዋርድ” በተሰኘ የዓለም የክላሲካል ሙዚቃ አዋርድ በክላሲካል ሙዚቃ ዘርፍ ሽልማት አግኝቷል። ስነ ስርዓቱ በሞስኮ ጥንታዊው ቦልሾል ቴአትር አዳራሽ ተከናውኗል። በሽልማቱ ላይ የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት ከሆኑት ሩሲያ፣ ቻይና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ህንድ፣ ሰርቢያ እና ቤላሩስ የተወጣጡ ታዋቂ ሙዚቀኞች፣ የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ ደራሲዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና የዘርፉ ተዋንያን ተገኝተዋል። በሁነቱ ላይ የታደሙት በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ (ዶ/ር) ለዝነኛው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ለተበረከተለት ሽልማት የእንኳን ደስ አለህ መልዕክት አስተላልፈዋል። ፒያኒስቱ ኢትዮጵያ ለሩሲያ ህዝብ በማስተዋወቅ ለተወጣው ሚና ያላቸውን አድናቆታቸውን ገልጸዋል። አምባሳደር ገነት የሽልማቱ አዘጋጆች ኢትዮጵያ ለሙዚቃ እና ለባህል ልውውጥ እያበረከተች ላለው አስተዋጽኦ ለሰጡት እውቅና ምስጋና ማቅረባቸውን በሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
ከተሞችን ያነቃቃው የኮሪደር ልማት - የጭሮ ኮሪደርን በጨረፍታ
Apr 1, 2025 501
የጭሮ ወተት ገበያ ከከተማው ዋና መንገድ ግራና ቀኝ የሚካሄድ የተጨናነቀ ገበያ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ በርካቶች ከማለዳ እስከ ማታ ገዥና ሻጮች ይገናኙበታል። የዚሁኑ የገበያ ማእከል እንቅስቃሴ ለመቃኘት የኢዜአ ሪፓርተር ወደ ስፍራው ባቀናበት ወቅት በገበያው ግራና ቀኝ በመንገዱ ዳርቻ ቁፋሮ እየተከናወነ ሲሆን ግብይቱም ሞቅ ደመቅ እንዳለ እንደቀጠለ ነው። በገበያው አመሻሽ ላይ ወተት እየሸጡ ካገኘቸው መካከል ወይዘሮ ሳርቱ አሊ፤ በአካባቢው የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የመንገድ ስራው ሌት ተቀን የሚከናወን በመሆኑ የወተት ገበያው በምሽትም በርካታ ተጠቃሚዎች ስላሉት ለመሸጥ መገኘታቸውን ነገሩን። ከዚህ በፊት በተለይም በምሽት ገበያው ቀዝቀዝ ያለ እንደነበር አስታውሰው የኮሪደር ልማቱ ከተጀመረ ግን በየቀኑ በምሽት አራት ጀሪካን ወተት ሽጠው የሚመለሱ መሆኑን ጠቅሰው ''ልማቱ ስራም ገበያም ፈጥሮልናል'' ይላሉ። በጭሮ ከተማ ምሽት ጭምር የሚደራው የወተት ገበያ ከአስር ብር ጀምሮ በመግዛት የሚጠቀሙ መሆኑን ሸማቾችም ይናገራሉ። በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠራቸው እንዳለ ሆኖ በጥራትና በፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ። በመሆኑም ከዚህ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ የፕሮጀከቶች መጓተት ችግር የተፈታበትና ሌት ተቀን የሚሰራበትን የስራ ባህል የፈጠረ መሆኑን ለማየት ችለናል። የኮሪደር ልማት ስራው በአጭር ጊዜ በጥራት ለማከናወን እየተደረገ ያለው የመንግስት የስራ አመራር እና በባለሙያዎች ጥረትም የሚደነቅ ነው። በጭሮ የኮሪደር ልማት በማህበር ተደራጅተው እየሰሩ ካሉ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች መካከል ወጣት ጀማል ኑሬ እና አምስት ጓደኞቹ በኮሪደር ልማቱ የስራ ዕድል አግኝቷል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ከስራ ዕድል ፈጠራም በላይ በዩኒቨርሲቲ የቀሰሙትን የምህንድስና ትምህርት በተግባር ለመፈፀም ያስቻላቸው መሆኑን ይናገራል፡፡ የኮሪደር ልማት ስራ ከዚህ ቀደም ሲከናወኑ ከነበሩት የመሰረተ ልማት ስራዎች የሚለየው በመንገዶች ግራና ቀኝ የሚከናወኑ የውበት ስራዎች እንዲሁም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ የእግረኛ መንገድ፤ የአደባባይ የድልድይና የመሳሰሉ ተዛማጅ ስራዎች በአንድ ላይ መያዙ ነው፡፡ በዚህም ከተማን ከማዘመን እና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በእኩል ደረጃ ተጠቃሚ ማድረጉ ኮሪደር ልማቱ ልዩ ጠቀሜታዎች ናቸው፡፡ ''የኮሪደር ልማት ስራው ሲጠናቀቅ እኔም ሙሉ ልምድና ዕውቀት አዳብሬ እወጣለው'' ያለው ወጣቱ ከገቢ በተጨማሪ እንደ ልምድ ማካበቻ እና መማሪያ በማየት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ከጨርጨር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በሰርቬይንግ ሙያ የተመረቀው የሱፍ ቀመር በኮሪደር ልማቱ የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሆነው ሌላኛው ወጣት ነው፡፡ የኮሪደር ልማት በርካታ ስራዎች በአንድ ላይ የሚከናወንበት በመሆኑ ከሙያው በተጨማሪ ሌሎች ሙያዎችንም ለመቅሰም ያስችለዋል፡፡ የከተማው ነዋሪዎችም የኮሪደር ልማቱን ጠቀሜታ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ችግሮች ጋር በማያያዝ ይገልጹታል፡፡ ጭሮ ከተማ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ጅቡቲ የሚጓዙ ተሸከርካሪዎች የሚተላለፉባት ከተማ በመሆኗ የመንገዱ ጥበት ከትራፊክ መጨናነቅ ጋር ተያይዞ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማው ተጀምሮ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት መንገዱን በእጥፍ እያሰፋው በመሆኑ የትራፊክ ፍሰቱን የተሸለ ከማድረግ ባለፈ የኢኮኖሚ እንንቅስቃሴውንም በመጨመር ከተማዋን የሚያነቃቃ ነው ይላሉ በከተማው የቡርቃ ጭሮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ከድር እስማኤል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ዕድሜ ጠገቧን ጭሮ ዳግም ወደ ቀድሞ ውበቷ እንደሚመልሳት ተስፋ አላቸው፡፡ ጭሮ ከተማ አሁን ቀን ወጥቶላታል የሚሉት አቶ ከድር ከዚህ በላይ ለከተማዋ የሚያስደስት ነገር ባለመኖሩ በተጠየቁት ሁሉ ልማቱን ለማገዝ ዝግጁ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡ የጭሮ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጀማል ጎሳዬ እንዳሉት በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት እነዚህን ሁለት ዋና የአስፋልት መንገዶች ስፋት በእጥፍ በማሳደግ ወደ 40 ሜትር ከፍ የማድረግ ዓላማ አለው፡፡ ይህም የከተማዋዉን የትራፊክ እንቅስቃሴ ከማሳለቱም በላይ ለፈጣን የንግድ እንቅስቃሴውም የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ይላሉ፡፡ በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት በከተማው ለሚገኙ ወጣት ባለሙያዎች ሙያቸውን የሚያዳብሩበት እና በልማቱ ለተሰማሩ ሌሎች ግለሰቦች የስራ ዕድል የተፈጠረበት በተጨማሪም በጥቃቅን የመንገድ ዳር የምግብ አገልግሎት ለሚሰጡ ነዋሪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጠ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከተቆረቆረች ረጅም አመት ላስቆጠረችውና ለደከመችው ከተማ ዳግም መነቃቃት የፈጠረ እና የከተማዋን እምቅ ኢኮኖሚ በማንሰራራት ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ነዋሪዎቿ ገልጸዋል፡፡ የጭሮ ከተማ ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ ድረስ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች ለማረፍ የሚመርጧት ከተማ በመሆኗም ልማቱ ሲጠናቀቅ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝላት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህም በከተማው ተጀምሮ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ዘርፈ ብዙ እና የከተማዋን ተስፋ ያለመለመ ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው፡፡ ለዚህ ነው ወይዘሮ ሳርቱ አሊ እና ሌሎች የጭሮ ከተማ ነዋሪዎች የኮሪደር ልማቱን ለማገዝ የሚችሉትን ሁሉ ለመወጣት የተዘጋጁት።
የአፍሪካዋ ግዙፍ መዲና -አዲስ አበባ
Mar 31, 2025 692
አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ የገበያ ባለሙያ እና የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር ክሪስ ቦራቲን በዴይሊ ኤክስፕረስ ጋዜጣ ቋሚ አምደኛ ነው። ክሪስ ቦራቲን በእንግሊዙ ዕለታዊ ጋዜጣ ዴይሊ ኤክስፕረስ ላይ ስለ መዲናዋ በከተበው ጽሁፍ ላይ። ጋዜጠኛው በጋዜጣው ላይ በዓለም ላይ ሊጎበኙ ይገባቸዋል የሚላቸውን ምርጥ ቦታዎች የተመለከቱ ጽሁፎችን በአምዱ ላይ በስፋት ያቀርባል። የወቅቱ ለጉብኝት ተጠቋሚ ቦታ አዲስ አበባ ሆናለች። ክሪስ “Africa's huge mega-city that's one of the highest capitals in the world” በሚል ርዕስ በጋዜጣው ላይ ባሰፈረው የግል ምልከታ ጽሁፉ ላይ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና በአፍሪካ ከሚገኙ ግዙፍ ሜትሮፖሊታን ከተሞች አንዷ ናት ሲል ገልጿታል። በፈጣን የዕድገት ጎዳና ላይ የሚገኙት አፍሪካ ከተሞች የዓለምን ቀልብ ስበዋል። ለአብነት ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺህ 355 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው የአፍሪካ መዲናዋ ከተማ ትጠቀሳለች። ይህቺ መዲና ማናት ቢሉ በእንጦጦ ጎረብታ ግርጌ በተራሮችና ገመገሞች ዙሪያዋን ተከባ የምትገኘው አዲስ አበባ ናት። አዲስ አበባ ለምድር ወገብ የቀረበች ብትሆንም ቅሉ ከፍተኛ ቦታ ላይ በመገኘቷ ዓመታዊ ሙቀቷ በአማካይ 18 ዲግሪ ሴልሺየስ ገደማ ብቻ ነው። ይህም የዓለማችን 4ኛዋ ከፍተኛ ቦታ ላይ የምትገኘው ከተማ ያደርጋታል። አዲስ አበባ እ.አ.አ በ2025 የህዝብ ብዛቷ ወደ ስድስት ሚሊዮን ይጠጋል። የህዝቡ ቁጥር በየዓመቱ ከአራት በመቶ ላይ እያደገ ይሄዳል። የታዋቂው የምርምር ተቋም ማክሮትሬንድስ መረጃ በዋቢነት አጣቅሷል። ይህም አዲስ አበባን በአፍሪካ እያደጉ ካሉ ፈጣን ከተሞች አንዷ ከመሆኗ ባሻገር በብዙ መመኛዎች እጅግ ግዙፏ ከተማ እንድትሆን እንዳደረጋት አመልክቷል። አዲስ አበባ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ የተቆረቆረች፣ እ.አ.አ በ1889 የኢትዮጵያ መዲና የሆነች ከተማ ናት። ከዛ ጊዜ በኋላ ዋንኛ የፖለቲካ፣ ባህል እና ኢኮኖሚ መናኸሪያ ሆናለች። የብሪሊያንት ኢትዮጵያ የአስጎብኚ ድርጅት ኩባንያ ባለሙያዎች አዲስ አበባ በርካታ ብዝሃ ማንነቶች ያላቸው ህዝቦች እና ዓለዐም አቀፍ ነዋሪዎች የሚገናኙበት ሲል ይገልጻታል። መዲናዋ ከሀገር በቀል ቋንቋዎች በተጨማሪ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛ እና አረብኛም ይወሩባታል። ክሪስ አዲስ አበባ በርካታ ታዋቂ ስፍራዎች እና የቱሪዝም መዳረሻዎች ያሏት ከተማ መሆኗንም ይገልጻል። በመዲናዋ ሊጎበኙ ይገባቸዋል ያላቸውን ቦታዎችንም በጽሁፉ ላይ ጠቆም አድርጓል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም በብዛት ከሚጎበኙ ስፍራዎች አንዱ መሆኑንና ጎብኚዎች በዓለም ቀደምት ከሚባሉ የሰው ዘር ቅሪተ አካላት መካከል አንዷ የሆነችውን ሉሲን የመጎብኘት እድል ያገኛሉ ሲል ተናግሯል። ፀሐፊው ሌላ በከተማዋ መጎብኘት አለባቸው ብሎ ካስቀመጣቸው ቦታዎች አንዱ የመስቀል አደባባይ ነው። አደባባዩ የተለያዩ ህዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትን ጨምሮ ለተለያዩ ሁነቶች እንደሚስተናገዱ ገልጸዋል። መስቀል አደባባይ በመስከረም ወር በክርስትና እምነት ተከታዮች በደማቅ ሁኔታ የተከበረውን የደመራ መስቀል በዓል ማስተናገዱን አውስቷል። የአዲስ አበባ የከፍታ ጫፍ የሆነው እንጦጦ ተራራ ከባህር ጠለል በላይ የ3200 ሜትር ርዝማኔ አለው። ተራራው የእጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እና የዳግማሚ ምኒሊክ የቀድሞ ቤተ መንግስት ይገኛል። ቦታው አዲስ አበባን ቁልጭ አድርጎ ለማየት እና ለረጅም የእግር እግር ጉዞ የሚሆኑ መንገዶችን ይዟል። ተጓዡ ፀሐፊ ቡና በኢትዮጵያውያን ህይወት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያለው መጠጥ እንደሆነ ለመረዳት መቻሉንና በዚህ ረገድም አዲስ አበባ በርከት ያሉ ካፌዎች እና የቡና መጠጫ ስፍራዎች እንዷላት ለመታዘብ መቻሉን ገልጿል። በተጨማሪም የአዲስ አበባ ዋና ገበያ ናት ያላት መርካቶ በአፍሪካ ሰፊው ክፍት ገበያ እንደሆነችም በጽሁፉ ላይ አስፍሯል። የደራ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደርግባት መርካቶ በህንጻዎች መካከል ባሉ የመተላለፊያ መንገዶች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የመሸጫ ቦታዎች ከቅመማ ቅመም ጀምሮ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ሽያጭ ይከናወንባታል ሲል ተናግሯል። አዲስ አበባ በፍጥነት እየተለወጠች ያለች ከተማ መሆኗን የገለጸው ጉምቱው የጉዞ ፀሐፊ የግንባታ እና የመሰረተ ልማት ስራዎች በመዲናዋ እየተከናወኑ እንደሚገኝ በመግለጽ ሀተታውን ቋጭቷል።
በክልሉ ተማሪዎች ስለ ግብርና ታክስ በቂ እውቀት ይዘው እንዲያድጉ ግንዛቤ እየጎለበተ ነው
Mar 29, 2025 147
ቦንጋ፤መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፦የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተማሪዎች ስለ ግብርና ታክስ በቂ እውቀት ይዘው እንዲያድጉ የታክስና ጉምሩክ ክበባት ተቋቋመው ግንዛቤ እያጎለበቱ መሆኑ ተገለጸ። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አቀፍ የታክስና ጉምሩክ ክበብ ተማሪዎች የጥያቄና መልስ የውድድር መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሄደ። ከመሠረቱ የተገነባ ትውልድ ሀገርን ይገነባል" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ውድድሩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ የገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ነው። በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አልማው ዘውዴ እንዳሉት፣ ተማሪዎች ስለ ግብርና ታክስ በቂ እውቀት ኑሯቸው ታማኝ ግብር ከፋይ እንዲሆኑ የታክስና ጉሙሩክ ክበባት ሚና የላቀ ነው። ለዚህም በክልሉ ባሉ ትምህርት ቤቶች ክበባትን በማደራጀት ተማሪዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ተሳተፎ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ተማሪዎች ላይ መስራት ነገ ሀገርን የሚወድና ግብሩን በታማኝነት የሚከፍል ትውልድ ማፍራት ነው' ያሉት ሀላፊው ግብርንና ታክስን በታማኝነት የሚከፍል ትውልድን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል'' ብለዋል። የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሕይወት አሰግድ በበኩላቸው በክልሉ የተጀመሩ ልማቶችና የዜጎች ፍላጎት ለመመለስ ገቢን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። ክልሉ ሲመሰረት ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥታ ያልሆነ ታክስ እና ታክስ ያልሆነ ገቢ ሲሰበሰብ ከነበረበት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ዘንድሮ ወደ 10 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። ገቢውን አሟጦ ለመሰብሰብ የተለያዩ አደረጃጀቶች በመጠቀተም ስልጠናዎች እና ምክክሮች እየተደረጉ መሆናቸውን ያነሱት ወይዘሮ ሕይወት፣ ከዚህም ዋናው የትምህርት ትቤቶች የታክስ እና ጉምሩክ ክበባት መሆናቸውን ገልፀዋል። በየትምህርት ቤቶች የተጀመሩ የታክስ እና ጉምሩክ ክበባት ትውልዱ የታክስ እና ጉምሩክ አስተዳደር ምንነትን እና ህጎች ላይ መሰረታዊ እውቀት እንዲኖራቸው እና ህገ-ወጥነት እና ኮንትሮባንድን የሚፀየፍ ዜጋ እንዲሆኑ ማስቻል ነው ብለዋል። የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር ጅማ ቅርንጫፍ ስራ የታክስ አስተዳደር ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ነጋሶ አብዲሳ፣ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ የሀገር ጉዳይ በመሆኑ ለማሳካትም ግንዛቤ ማስፋት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ግብር ከፋዩ፣ ማህበረሰቡና ትውልዱ ስለግብር ግንዛቤ እንዲሰፋ በትምህርት ቤት ደረጃም የተለያዩ ክበባትን በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው የገቢ አሰባሰብ አቅም እንዲጨምር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል። በመድረኩ ላይ የክልል አመራሮች፣ ርዕሰመምህራን፣ተማሪዎችና ሌሎች ባለድሻዎች ተገኝተዋል።
የካቲት እና ኢትዮጵያ
Feb 26, 2025 526
በአየለ ያረጋል በየክፍላተ-ዓለሙ ዓመታት በወራት ሲመነዘሩ የራሳቸው መልክና መገለጫ ይኖራቸዋል። እንደየንፍቀ ክበቡ ወቅቶች የራሳቸው ጸባይ፣ ክዋኔ፣ ትውስታና ትዕምርት ይቸራቸዋል። ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ባለ13 ወር ጸጋ ናት። ከጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመርም ሰባት ዓመት ከስምንት ወራት ልዩነት አላት። በባሕር ሃሳብ ምሁራን የኢትዮጵያን ወቅቶች መጸው(መኸር)፣ ሐጋይ(በጋ)፣ ፀደይ(በልግ) እና ክረምት በሚል አራት ወቅቶችና አውራኅ ይከፍሉታል። ሁሉም አውራኅ፣ እያንዳንዱ ወራት በራሳቸው ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቀለማትን ይጎናጸፋሉ። የወራቱ ቅላሜና ሕብርነት ልዩ መልክዓ-ኢትዮጵያን ይፈጥራል። ከዘመን መባቻው መስከረም እስከ ማዕዶተ-ዘመኗ ጳጉሜን ወራቱ በሰማይና በምድሩ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ውቅራቸው ግላዊ ገጽታ ይነበብባቸዋል። የኢትዮጵያ ወራት ስያሜ ከመልክና ግብራቸው ይመነጫል። ከሁሉም ወራት ግን ከታሪካዊ ሁነቶች አንጻር የካቲት ልዩ ገጽታ አለው። አሁን ወቅቱ በጋ ወይም ሐጋይ ነው። ወርኅ የካቲትንም የሐጋይ አውራኅ ደማቁ ገጽ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ውስጥ ወርኅ የካቲትን ያክል በየታሪክ ህዳጉ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ የወሰነ ወቅት ያለ አይመስልም። የካቲት የበጋ ወርኅ አልፎ የበልግ ጊዜ መግቢያ ነውና የቋንቋ ሊቃውንቱ 'የካቲት'ን ስያሜ 'የመከር ጫፍ መካተቻ፤ የበልግ መባቻ " ይሉታል። የመኸር ምርት የሚከተትበት ነው። በኢትዮጵያ ዘመን ስሌትም መንፈቅ ዓመት ወይም ስድስተኛው ወር ነው። ወርኅ የካቲት በመካከለኛው ዘመን ዝነኛውን ንጉስ አፄ ሠርፀድንግልን፣ የአድያምሰገድ ኢያሱን ልጅ ዳግማዊ አፄ ዳዊት(አድባር ሰገድን)፣ “የዘመናዊት ኢትዮጵያ ጠንሳሽ ናቸው” የሚባሉትን አፄ ቴዎድሮስንና ንግስት ዘውዲቱን አንግሷል። በሌላ በኩል ኢማም አሕመድ ኢብራሂምን(ግራኝ አህመድ)፣ አፄ ሚናስን፣ እቴጌ ጣይቱን፣ እቴጌ መነንን፣ ንጉስ ወልደጊዮርጊስን፣ ራስ ደስታ ዳምጠውን፣ ራስ አሉላ እንግዳን እና ሌሎች የዓድዋ ብሔራዊ የጦር ጀግኖችን አሳርፏል። ከኪነ-ጥበብ መስክ ደግሞ ወርኅ የካቲትን ያህል የሞት ዶፍ የወረደበት ወቅት እንደሌለ ብዙዎቹ ይስማማሉ። ለአብነትም ሞገደኛው ብዕረኛ አቤ ጉበኛ እረፍት የካቲት 2፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር የካቲት 12፣ ጸጋዬ ገብረመድህን የካቲት 18፣ ማሞ ውድነህ የካቲት 23፣ እንዲሁም ተወዳጁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ እንደወጣ የቀረው የካቲት 24 ነበር። የካቲት በርካታ የምንኮራባቸው ሰዎች የተወለዱበትና በሞት ያጣንበትም ወር ነው። የካቲት ታላቅ የሰማዕትነት ወር ነው፤ በ1929 ዓ.ም 30 ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በጅምላ በአካፋና በዶማ በግፍ የተጨፈጨፉት በወርኅ የካቲት ነው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የጣሊያን ወራሪን በማሳፈር ለጥቁር ሕዝቦች ቀንዲል የሆነውን የዓድዋ ድል የተቀዳጀችው በየካቲት መገባደጃ ወቅት ነበር። መልከ-ብዙው ዓድዋ ድል፤ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ተከውኗል። በዚያች ተዓምረኛ ዕለት በዓድዋ ተራሮች መንደር መድፎች አጓርተዋል፤ መትረየሶች አሽካክተዋል፤ እሳት ወርዷል፤ ጥይት ዘንቧል፤ ጎራዴ ተመዟል፤ ጦር ተሰብቋል። በጥቅሉ የክቡር ሰብዓ ዘሮች ደም ተገብሯል። የዓድዋ ድል ህያውነት፣ እንቆቅልሽነት፣ አድማስ ዘለል ታሪክነት፣ የዓለም ነፀብራቅነት፣ አፍሪቃዊነት፣ ኢትዮጵያዊነት ተዘርዝሮ አያልቅም፤ በዓድዋ ጦርነት የተመዘገቡ የይቅርታ፣ የፍቅርና የርህራሄ እሴቶች ከጥቁር ሕዝቦች ድልነት አሻግረው ለእያንዳንዱ ሰው ድል አድርገውታል። ከየካቲት ድሎች ዓድዋ ይድመቅ እንጂ ቅድመ-ዓድዋም ሆነ ድኅረ-ዓድዋ ጦርነት ደማቅ ድሎች ተመዝግበዋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በወርኅ የካቲት የግብጽን ወረራ በጉራ፣ የሶማሊያ ጦርነትን በካራማራ፣ ድል ተቀዳጅታለች። የካቲት 12 ጭፍጨፋ እና የካቲት 23 የዓድዋ ድልን ጨምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የማንነት፣ የሀዘን ሁነቶችና ተፃራሪ ታሪኮችን አስተናግዷል ይኸው ወርሃ የካቲት። የ1928ቱ የጣሊያን ወረራ በሽሬ፣ በተንቤን እና በአምባራዶም የጦር ሜዳዎች የተከለከለ መርዝ በኢትዮጵያዊያን ላይ ተርከፍክፎ እንዲቃጠሉ መደረጉም የታሪክ ድርሳናት እማኝ ናቸው። ወርኅ የካቲት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ታላላቅ አብዮቶች፣ ታላላቅ ድሎች ተከውነውበታል። ለኢትዮጵያ ሕልውና እንደ ክብር የደም ግብር የቀረበበት፣ በየጋራና ሸንተረሩ የትውልድ መስዕዋትነት የተከፈለበት ጊዜ ነው። የካቲት የድልና የዕድል፤ የደምና ገድል ወር ነው። አሳዛኝም፤ አስደሳችም! የካቲትና የኢትዮጵያ ታሪክ ግንኙነት ድል የተገኘበት፣ መጥፎ ጠባሳዎችንም ያተምንበት ወቅት በመሆኑ ወርኅ የካቲትን በግጥምጥሞሽ የተሞላ፤ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። የካቲት ወር 2010 ዓ.ም በኢህአዴግ ላይ የነበሩ አመጾች የተባባሱበትና ፖለቲከኞች ከእሥር የተፈቱበት ነው። የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኃላፊነት ለመልቀቅ ለፓርቲው መልቀቂያ ደብዳቤ ያቀረቡበት ነው። ከኢትዮጵያ አልፈው እንደ ዓድዋ ያሉ ለጥቁር ሕዝቦች ትግል አብነት የሆኑ ታሪኮች የተፈጸሙበት፣ አብዮት የተካሄደበትና የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የተወሰነባቸው ክስተቶችን ያስተናገደ ወር እንደሆነ ያነሳሉ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የማንነት፣ የሀዘን ሁነቶችን ማስተናገዱን አስተናግዷል። የወርሃ የካቲት ሁነቶች ተጻራሪ ታሪኮች እንደሆኑ የካቲት 12 እና የካቲት 23ን ለአብነት ይጠቀሳሉ። በርግጥ ወርኅ የካቲት ከኢትዮጵያ አልፎ በአጠቃላይ የመብትና ነፃነት ትግሎች የተስተናገዱበት ሲሆን በአገረ- አሜሪካ ጥቁሮች ለእኩልነትና ነፃነት የታገሉበት ወቅት በመሆኑ የታሪካቸው አካል በማድረግ ያከብሩታል። ለመሆኑ ወርኅ የካቲት ከኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ጋር የመጣባቱ ምስጢር ምን ይሆን? ለጉዳዩ አመክንዮ የሰጡ የታሪክ ምሁራን ወርሃ የካቲት ገበሬው የሚያርፍበት፣ ወንዞች ደርቀው ሰው የሚገናኝበት በመሆኑ እንዲሁም የጾም ወቅት መሆኑ የውጭ ጠላቶች አስልተው እንደሚመጡ ጠቅሰው፤ ለአብነትም በሰንበትና በፆም ወቅት የተደረገውን የአድዋ ጦርነት ያነሳሉ። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ገበሬ የሆነባት ኢትዮጵያ ካሏት 13 ወራት መካከል ወርኃ የካቲት ለገበሬው ጥጋብ፣ ለመንግስታት ደግሞ የግብር መሰብሰቢያ ወር መሆኑን በማውሳት። ወርኃ የካቲት ምርት ተሰብስቦ ጎተራ የሚገባበት፣ ሰርግ የሚሰረግበት፣ ሽፍታ የሚበረታበት ወቅት ነው። በ'ግብር ገብር! አልገብርም!' በሚል ግብግብ የገበሬ አመጽ የታየበት ወር መሆኑ ይወሳል። በሌላ በኩል ወቅቱ ተማሪዎች ከአንደኛው መንፈቅ ዓመት ወደ ሁለተኛው የሚሸጋገሩበት ነው። በዚህም ተማሪዎችም ለንቅናቄ ይነሳሳሉ። በ1960ዎቹ የተደረገውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመሬት ለአራሹ፣ የዴሞክራሲ፣ የኃይማኖትና የብሔር ጥያቄዎችን ያነሱበትና አብዮት የቀሰቀሱበት እንደነበር የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ። የካቲት በርካታ የምንኮራባቸው ሰዎች የተወለዱበትና ያጣንበትም ወር መሆኑን ለምን ብለን ባንጠይቅም፤ ግጥምጥሙ ግን አጃይብ ያሰኛል። ኢትዮጵያ በየካቲት ወር ባሳለፈቻቸው ታሪኮች ልትማር፣ ትውልዱም ታሪኩን ሊያውቅ ይገባል።
የበይነ-አፍሪካዊያን ትስስር ተምሳሌት - አሊኮ ዳንጎቴ
Feb 20, 2025 459
ቀደምት ፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኞች አንዱ ህልማቸው በኢኮኖሚና ፖለቲካ የተሳሰረች፣ ራስ በቅ አፍሪካን ዕውን ማድረግ ነበር። ጥሬ ዕቃዎቿ ላይ እሴት የሚጨምሩ ኢንዱስትሪዎች ባለቤት የሆነች፣ ከውጭ ምርቶች ጥገኝነት የተላቀቀችና በምግብ ራሰ በቅ የሆነች፣ በበይነ-ቀጣናዊ የኢኮኖሚና ንግድ የተሳሰረች አፍሪካን ዕውን ማድረግ ነበር ጽኑ መሻታቸው። ለዚህም አንዳንድ የአፍሪካ መንግስታት ከቅኝ ግዛት ነጻ በወጡ ማግስት ጀምሮ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል ስትራቴጂ ነድፈዋል። ለዚህ ደግሞ ግዙፍ አፍሪካ በቀል ኩባንያዎችን መስርቶ ምርታማነትን መጨመር፣ ሀገራትን በልማት ማስተሳሰር እና ብርቱ አህጉር አቀፍ የግል ዘርፍ መገንባት የሞከሩ አሉ። ባለሙያዎችም ከመንግስት መር ኢኮኖሚ ልማት ይልቅ ለዘላቂ ዕድገት የግል ዘርፍ መራሽ አፍሪካ አቀፍ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚያሻ ይወተውታሉ። የአፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደትና ትስስር በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት ቢቀነቀንም አህጉራዊ የስምምነት ማዕቀፍ ሆኖ የወጣው በአፍሪካ ሕብረት አስቸኳይ ውሳኔ በፈረንጆቹ 2018 ነበር። ይሄውም አፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ነው። ከ2021 ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። ስምምነቱን 54 አባል ሀገራት ፈርመዋል። 48ቱ ሀገራት በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶቻቸው አፅድቀውታል። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ማዕቀፍ ታዲያ የግል ዘርፋን የሚያበረታታ ነው። ይህ ደግሞ በአፍሪ ሀገራት የሚገኙ ከበርቴዎች ከትውልድ ሀገራቸው ተሻግረው በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱና አፍሪካ አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ተጠቃሚነት እንዲጎለብት መልካም ዕድል ይዞ ይመጣል። ናይጄሪያዊው ከበርቴ አሊኮ ዳንጎቴ የአፍሪካ የግሉ ዘርፍ ቁንጮ ናቸው። በፎርብስ መጽሔት መረጃ በተያዘው ዓመት የ67 ዓመቱ ቢሊየነር ዳንጎቴ 23 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ሀብት አካብተዋል። ዳንጎቴ በአፍሪካ ኢንቨስመንትቻውን እያሰፉ ነው። ይህ እንቅስቃሴያቸው ደግሞ የራስ በቅና የበይነ-አፍሪካዊያን ትስስር ተምሳሌቱ ቱጃር ያሰኛቸዋል። አሊኮ ዳንጎቴ ከሰሞኑ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ብለው ለኢትዮጵያ አዳዲስ መረጃዎችን አብስረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር መክረዋል። ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ ያላቸውን የሲሚንቶ ምርት መጠን በዕጥፍ ለማሳደግ ወስነዋል። ከማዕድን(ሲሚንቶ) በተጨማሪም በሌሎችች ኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት የአዋጭነት ገበያውን እየፈተሹ ስለመሆኑ እንዲሁ። ለአብነትም የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባትን ጨምሮ የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በሚያሳድጉ ዘርፎች ለመሰማራት አቅደዋል። በስኳር ልማት እንዲሁ። ናይጄሪያዊው የአፍሪካው ቀዳሚው ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ በሲሚንቶ፣ የነዳጅ ማፈላለግ፤ የማዕድን ማውጣት፤ የማዳበሪያ እና የተፈጥሮ ጋዝ ማጓጓዝ ስራዎች ላይ በስፋት ተሰማርተዋል። ናይጄሪያን ጨምሮ በ20 የአፍሪካ ሀገራት በቢሊዮኖች ዶላር የሚገመት ኢንቨስትመንት አፍስሰዋል። ለአብነትም በሲሚንቶ ዘርፍ ከናይጄሪያ በተጨማሪ በኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣ ሴኔጋል፣ ካሜሮን፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ጋና እና ኮትዲቭዋር የሲሚንቶ ፋብሪካ ገንብተዋል። በናይጄሪያ ሌጎስ የአፍሪካ ግዙፉን የዳጅ ማጣሪያ ገንብተዋል። ስገንብተዋል። የነዳጅ ማጣሪያው ጋና እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት ነዳጅ ይልካል። ኩባንያው የአውሮፕላን ነዳጅን ወደ አውሮፓ ለመላክም አቅዷል። ከባድ ናፍጣ የመላክ እቅድ አለው። የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣረያ የአፍሪካ የነዳጅ ጥገኝነት ለመቀነስ ተስፋ ተሰንቆበታል። ኩባንያቸው በግብርና፣ ምግብ ማቀነባበሪያ፣ በስኳር፣ በፋይናንስ አገልግሎት፣ መሰረተ ልማትና ኢነርጂ፣ ማዳበሪያ፣ በምግብ እና መጠጥ እና ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ኮንስትራክሽን እና ሌሎች ዘርፎች በኢንቨስትመንት ተሰማርቷል። አሁንም አፍሪካን እያካለለ ነው። ቱጃሩ ዳንጎቴ በብረታ ብረት፣ በታዳሽ ኃይል፣ በጤና እና ፋርማሲዩቲካል ዘርፎችም ያላቸውን ኢንቨስትመንት በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የማስፋት ግብ ይዘዋል። የአሊኮ ዳንጎቴ እንቅስቃሴ ከቀደምት ፓን አፍሪካዊያን ህልም ጋር የተጣጣመ ነው። አፍሪካን በአፍሪካ በቀል ኢንዱስትሪ ማልማት፣ ስራ ዕድል መፍጠር፣ ከውጭ ምርት ጥገኝነትን መቀነስ፣እሴት የተጨመረባቸወን የአፍሪካ ምርቶች ወደ ሌሎች አህጉራት መላክና አፈሪካዊያን ማስተሳሰር ለዚህ ሁነኛ አብነት ናቸው። ዳንጎቴን መሰል የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ውጤታማነት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ለአህጉራዊ አጀንዳዎች ስኬት የግሉ ዘርፍ ምሰሶ በመሆኑ ለአፍሪካ ዘላቂ ዕድገት የመንግስታት እና የግሉ ዘርፍ እጅና ጓንት መሆንን ይጠይቃል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሁልጊዜም ምክረ ሀሳብ ነው።
ጥቂት ስለ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ
Feb 18, 2025 350
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አዲሱ የዓለም የፉክክር መድረክ እየሆነ መጥቷል። በልብወለድ ወይም በምናብ የሚታሰቡ ፈጠራዎች፤ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እውን እየሆኑም ይገኛሉ። እ.ኤ.አ ከ2012 ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ ዕድገት ያሳየው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአሁኑ ጊዜ ከሰዎች የቀን ተቀን ሕይወት ጋር እየተዛመደ መጥቷል። በዕለት ተዕለት የሰዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መጠቀሚያዎች እንመልከት። 👉ቻት ጂፒቲ (ChatGPT): ጥያቄዎችን ለመመለስ፣ ሀሳቦችን ለማመንጨት እንዲሁም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን ለማግኘት የሚረዳ ነው። 👉ግራመርሊይ (Grammarly) : በፅሁፍ ውስጥ የግራመር (ሰዋሰው) እንዲሁም የስርዓተ ነጥብ ስህተቶች የሚያርም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መጠቀሚያ ነው። 👉ካንቫ (Canva) : የተለያዩ ግራፊክስ ስራዎችን በቀላሉ የሚሰራልን መጠቀሚያ ነው። 👉ኦተር ኤአይ (Otter.ai) : በድምፅ የምንናገራቸውን ወደ ፅሁፍ (text) የሚቀይር መጠቀሚያ ሲሆን በአብዛኛው በትምህርት ቤት ውስጥ ለሌክቸር ይጠቀሙታል:: 👉ክራዮን (Craiyon) : ፅሁፍ ብቻ በመፃፍ የምንፈልገውን ፎቶ ለመፍጠር የሚረዳ መጠቀሚያ ነው። 👉ሬፕሊካ (Replica) : የኤ አይ ቻት ቦት ሲሆን ስለ አዕምሮ ህክምና የሚያማክር እንዲሁም የግል የአዕምሮ ህክምና ምክር የሚሰጥ ነው። 👉ማይክሮሶፍት ቱ ዱ (Microsoft To Do): የቀን ሥራዎቻችንን ለማቀድ እና ለማደራጀት የሚያግዝ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መጠቀሚያ ነው። 👉ሄሚንግዌይ ኤዲተር (Hemingway Editor): የኦንላይን መፃፊያ ሲሆን አፃፃፋችን የጠራ እና ሀሳብን የያዘ እንዲሆን የሚያግዝ መጠቀሚያ ነው። 👉ጎግል አሲስታንት (Google Assistant): የቨርቹዋል አጋዥ መጠቀሚያ ሲሆን የቤት ውስጥ ስማርት መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር፣ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲሁም አስታዋሽ በመሆን ያገለግላል። 👉ጎግል ፎቶ (Google Photos): ፎቶዎችን ለማደራጀት እንዲሁም ለመፈለግ የሚረዳ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መጠቀሚያ ነው።
የአድዋን መንፈስ እንልበስ- ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሌይ
Feb 18, 2025 315
ወርሃ የካቲት የጥቁሮች ወር ነው። ካሪቢያን ጥቁሮች በጥቁሮች የትግል ታሪክ ጉልህ አሻራ ያላቸው መሰረተ አፍሪካ ህዝቦች ናቸው። ካሪቢያን ዜጎች ኢትዮጵያን አብዝተው ይወዳሉ። ለመላው ጥቁር ሕዝቦች አንድነትና ትግል ንቀናቄ አድዋን እንደ እርሾና እሴት ያወሳሉ። በቅርብ በ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የታደሙት የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሌይ በሕብረቱ ጉባዔ ላይ ያደረጉት ንግግር በርካቶችን ያስደመመና ያስደነቀ ነበር። ከመልዕክታቸው ውስጥ ተከታዮቹን ሃሳቦች መዘናል፦ 👉 አድዋ በ24 ሰዓታት ውስጥ የአውሮፓዊያንን የራስ መተማመን ትምክህት ያሽመደመደ፤ የአፍሪካዊያንና ትውልድ አፍሪካዊያንን ልጆች መንፈስ ያጎመራ፣ መልካምነት ድል ያደረገበት፣ ብርሃን በጨለማ ላይ የነገሰበት ሁነት ነው። 👉 ዛሬ እናንተ ፊት የቆምኩት ይህን መንፈስ ታጥቄ ነው። አድዋ የፓን አፍሪካኒዝም እርሾ ነበር። 👉 የአድዋ ድል ለነጻነትና ትግል እንድንነሳሳ ባቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነጻነት ድል እንድንቀዳጅ ምዕራፍ የከፈተ ድል ነው። አድዋ የአንድነት ውጤት ነው። 👉 እናንተ ፊት የቆምኩት የፓን አፍሪካዊነት ፈር ቀዳጆችን ሕልም ሰንቄ ነው። 👉 እኛ የካረቢያን ትውልዶች ከአፍሪካ ወንድምና እህቶቻችን ጋር ሕብረታችንን ማጠናከር እንሻለን። 👉 ትናንት በእኛ መከፋፈል ራሳቸውን ለበላይነት ያነገሱ ሃይሎችን እያሰብን አንድነታችንን አጠናክረን ነገን እንገንባ ወይም እንደ ትናንቱ ተነጣጥለን እንጥፋ የሚለው ምርጫ የኛ ፋንታ ነው። 👉 ስለዚህ የአድዋን መንፈስ ተላብሰን ከፊታችን የሚጠብቀንን መልከ ብዙ ፈተና በአንድነት እንጋፈጥ። 👉 ከአፍሪካ ውጭ የጥቁሮች ምድር ከሆነችው ባርባዶስ ተነስቼ ኢትዮጵያ የተገኘሁት ለአፍሪካና ካረቢያን ህዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት ጥሪ ነው። 👉 ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥለሴ በዓለም ላይ አንደኛና ሁለተኛ መደብ ዜጋ መኖር የለበትም እንዳሉት ዛሬም በየትውልዱ በዓለም ላይ ኢ-ፍትሃዊነትና አግላይነት ስርዓት ይወገድ ዘንድ መታገል አለብን። ለዚህ ደግሞ የአድዋ ድልና የፓን አፍካዊነት መንፈስን እንልበስ። 👉 የጋራ መዳረሻችንን ለመቀየስ ከወሬ ይልቅ ተግባር ላይ አተኩረን በትጋት እንስራ። የትናንት ቁስልን እያከክን ሳይሆን ብሩህ ነገን ለመገንባት በጋራ እንቁም። 👉 ከፊታችን የተደቀነ አደገኛ ፈተና እንዳለ ተገንዝበን ፈተናውን በአንድነት ለመጋፈጥ ሞራላዊ ግዴታችንን እንወጣ። 👉 የአድዋን መንፈስ እንልበስ!
አዲስ አበባ በአሕመድ ሴኩ ቱሬ አንደበት
Feb 15, 2025 225
(62 ዓመታት ወደኋላ) ________________ አሕመድ ሴኩ ቱሬ ከቀደምት የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኞች አንዱ ነበር። በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር በነበረቸው የምዕራብ አፍሪካዊነቷ ሀገረ-ጊኒ የነጻነት ታጋይና ፖለቲከኛ ናቸው። ድሕረ ነጻነት የሀገሪቷ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆነዋል። በፈረንጆቹ አቀጣጥርግንቦት 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ ከታደሙና አስደማሚ ንግግር ካሰሙ መሪዎች መካከል አንዱ ሴኩ ቱሬ ነበሩ። ለዛሬ ከፕሬዝዳንት አሕመድ ሴኩ ቱሬ አዲስ አበባን እና ኢትዮጵያን በወቅቱ የገለጹበትን መንገድ እነሆ ብለናል። “…. አዲስ አበባ የታሪክ ክስተት መውጠኛ ስፍራ ናት። በአፍሪካ አወንታዊ የለውጥ ሽግግር ታሪክ መቁጠሪያ ነጥብ ሆናለች። ይህ ቅጽበት የአፍሪካ የተሟላ አርነት ማብሰሪያ ነው፤ የአፍሪካ ሰው ከነምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊ፣ ወታደራዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ውቅሩ ነጻ የሚወጣበት። ይህ ስፍራ አፍሪካዊያን መንግስታትን ውጤታማ የሚያደርግ የፈጠራ ክዋኔዎች የመለኮሻ ዘመንም ነው። ለምን ቢሉ አፍሪካዊያን ወደ አንድ በመመጣት ህዝባቸውን ከሰቆቃ እንዲያገግም፣ የጋራ ስልጣኔ እንዲያንሰራራ፣ ሰብዓዊ እሴቶችና ባህላቸው ፈጣን እመርታ እንዲያመጣ ግብ የሰነቁበት ነውና። የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ነው። ኢትዮጵያዊያን ለአፍሪካ ነጻ መውጣት በጀግንነት ተዋግተዋል። የሕዝብ ነጻነት እንዲጠበቅ ብሎም ሰዎች ያለማንም የውጭ አካል ጣልቃገብነት መብታቸው ተከብሮ መዳረሻቸውን በራሳቸው ይተልሙ ዘንድ መንገድ የጠረጉ እና የራሳቸውን ጉዳይ በተሟላ ሉዓላዊነት እንዲፈጽሙ በተግባር ያሳዩ ህዝቦች ናቸው። ዛሬ በኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ የአፍሪካ ጉባዔ እየተካሄደ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ምንጊዜም በአፍሪካ ታሪክ ገጾች ውስጥ ደማቅ አሻራ አንብራለች። መላው የአህጉሪቷ ህዝብ የመለወጥ መሻቱን በቅጡ እንዲገነዘብ የተካሄደ ሁነት ነው። በ1885ቱ(በአውሮፓዊያን አቆጣጠር) የበርሊን ጉባዔ በኢኮኖሚ የጠገቡ ስርዓት አልበኛ የአውሮፓ መንግስታት ስልጣኔያቸውን ለማስፋፋት ሲሉ ያላቸውን ሀይል ተመክተው አፍሪካን እንደ ኬክ ቆራርሰው ሊቀራመቱ ተሰባስበው ነበር። ዛሬ ግንቦት 1963(በአውሮፓዊያን) ግን ምርጥና ሐቀኛ የአፍሪካ ልጆች ስለራሳቸው እና ስለእናት ምድር አፍሪካ ታምነው በንጹህ ማንነት የጋራ መዳረሻ መንገድ ለመቀየስ አዲስ አበባ ተሰባስበው እየመከሩ ነው። የአፍሪካ ትንሳኤዋ ዛሬ ነው። አፍሪካ በአንድ ነጠላ መንግስት ህጋዊ መልክ ትይዝ ዘንድ ልዩ መተዳደሪያ ሰነድ(ቻርተር) ማለትም አፍሪካዊያንን በወንድማማችነት፣ በማይናወጥ አጋርነት፣ በሰዎች መብትና ጥቅም፣ በሰላምና ነጻነት እንዲሁም በፍትህ መርሆች ውህደት የሚፈጥሩበት አጋጣሚ ነው። የአዲስ አበባ ጉባዔ የዛሬን አፍሪካ ችግሮች ምላሽ በመስጠት ላይ ብቻ የተወሰነም አይሆንም። አፍሪካ የዓለም አካል መሆኗን ልብ ይሏል። በዓለም ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሰው ልጅ ሕይወት፣ ሰላም፣ ደህንንትና ዕድገት መንስኤ የሆኑ የጋራ ተግዳሮቶች ሁሉ አፍሪካን ይገዷታል…”።
የአፍሪካውያን የዛሬ ስራ ለነገ ተስፋቸው
Feb 14, 2025 252
በዓለም በትልቅነቷ በሁለተኝነት የምትጠቀሰው አፍሪካ የህዝብ ቁጥሯ በ2024 (እ.ኤ.አ) አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። አህጉሪቷ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፣ የሰጡትን የሚያበቅል ለም አፈር ያላት፣ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የምትተርፍ መሆኗም በብዙዎች የተመሰከረለት ነው። ይሁንና አህጉሪቷ ለበርካታ ዓመታት በጦርነት፣ በበሽታ፣ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ስትጠቃ ኖራለች። ከተመሰረተ 50 ዓመታትን የተሻገረው የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት "እ.ኤ.አ በ2063 መሆን የምንፈልገው" ብለው የተለያዩ እቅዶችን ነድፈው ወደ ተግባር ገብተዋል። ''እኛ አፍሪካውያን በ2063 መሆን የምንፈልገው'' በሚል ባሰፈሩት አጀንዳ በርካታ የአህጉሪቷ የልማትና የብልጽግና ትልሞች ተቀምጠዋል። በዚህም ሁሉን አቀፍ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት የተረጋገጠባት፣ በልማትና በኢኮኖሚ የተዋሃደች፣ ሰላምና ደህንነቷ የተጠበቀና በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ የጎለበተ አህጉር መፍጠር ይገኙበታል። በኢኮኖሚ የፈረጠመች፣ የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠችና ለዜጎቿ ምቹና አስተማማኝ አህጉር የማድረግ እቅዱን ለማሳካት የተለያዩ ጥረቶች ተጀምረዋል። የአገራቷ መሪዎችም እነዚህን የልማት እቅዶች ከየአገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለገቢራዊነቱ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። አፍሪካ በ50 ዓመታት ለማሳካት የያዘችው አጀንዳ ሁሉን አቀፍ የልማት እቅድ፣ ከዓለም ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታና በአፈጻጸም ቁርጠኝነት ክፍተት እስካሁን የሚፈለገውን ያህል ውጤት ያለመመዝገቡም ይገለጻል። መሪዎቹ ይህን እቅዳቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር የነበራቸው ቁርጠኝነት ማነስ፣ የውጭ ተጽእኖ ማየል ዕቅዶቹ እንዳይሳኩ ምክንያት ሆነዋል። በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጽዕኖን የምታስተናግደው አፍሪካ አሁንም ቢሆን ተደጋጋሚ ድርቅና ጎርፍን እንዲሁም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዜጎቿን እየፈተኑ ይገኛሉ። የምርትና ምርታማነት እጥረት፣ የሰለጠነ የሰው ሃይልና ቴክኖሎጂ አቅም ውስንነት፣ የሌሎች አገራት ጣልቃ ገብነትና ሌሎች ችግሮችን በመፍታት አጀንዳዋን ለማሳካት ብዙ ይቀራታል። አፍሪካ በ50 ዓመታት ውስጥ ለመሳካት ያቀደችውን በተግባር ለማጠናቀቅ 38 ዓመታት ይቀሯታል። በዚህ ረገድ የተወሰኑ አገራት የተሻለ ኢኮኖሚ በማስመዝገብ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና፣ መሰረተ ልማትና ቴክኖሎጂን በማሟላት የተሻለ ዕድገት ማስመዝገባቸው ይነገራል። በአህጉሪቷ በተመሰረቱ የተለያዩ ጥምረቶች አገራት እርስ በእርስ በመሰረተ ልማትና በሃይል በማስተሳሰር ረገድ መልካም የሚባሉ ጅምሮች ታይተዋል። ይሁንና የዓለምን ተለዋዋጭ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች በአግባቡ በመረዳት የዜጎችን ህይወት በተጨባጭ መቀየር፣ ሰላማዊ፣ በኢኮኖሚ የዳበረች፣ በዓለም መድረክ እኩል ድምጽ ያላት አህጉር የመፍጠር እቅዱን እውን ለማድረግ በርካታ ቀሪ ስራዎች መኖራቸው የአደባባይ ሀቅ ነው። እያንዳንዱ አፍሪካዊ ዜጋ አጀንዳ 2063ን በአግባቡ ተገንዝቦ ለትግበራው የድርሻውን መወጣት እንዲችልም በቂ የግንዛቤ ስራ ሊሰራ ይገባል። የአፍሪካ መሪዎች በአጀንዳ 2063 የተያዙ ግቦች በትክክል እንዲተገበሩ ዜጎቻቸውን አስተባብረው በቁርጠኝነት መስራት ግድ ይላቸዋል። የአጀንዳ 2063 እውን መሆን ዋነኛ ተጠቃሚ የሚያደርገው የአህጉሪቷን ዜጎች እንደመሆኑ እቅዱን ለማሳካት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው። የአፍሪካ አገራት የጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ለመምከርና የአህጉሪቷን መጻዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግ በአንድ ጥላ በሚያሰባስባቸውና በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ ይገናኛሉ።
ኢትዮጵያ እና የሕብረቱ ወሳኝ አካል የሆነው ምክር ቤት
Jan 17, 2025 788
የአፍሪካ ሕብረት ቁልፍ ተቋም ነው- የሕብረቱ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት። የፊታችን የካቲት ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ በሚደረገው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ከሚቀረቡ ዝርዝር አጀንዳዎች አንዱ የዚህ ምክር ቤት አባላት ምርጫ እንደሚሆን ይጠበቃል። ኢትዮጵም በቅርቡ ለምክር ቤቱ አባል ለመሆን ፍላጎቷን ይፋ አድርጋለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ለመሆን ያላትን መሻት በአዲስ አበባ ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች አብስረዋል። ለመሆኑ የሕብረቱ የሰላምና የደህንነት ምክር ቤት ስራው ተልዕኮና ሚና ምንድነው? አባላቱም እንደ ሀገር ምን ፋይዳ ይሰጣቸው ይሆን የሚለውን እንናስቃኝዎ! የምክር ቤቱ ለመመስረቻ ጥንስስ የተጠነሰሰውና የማቋቋሚያ ሕግ ማዕቀፍ የጸደቀው በአውሮፓዊያኑ 2002 በደርባን(ደቡብ አፍሪካ)በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ ስብስባ ነበር። በአውሮፓዊያኑ ታኅሣሥ 2003 ወደ ስራ ገባ። ባለፈው ዓመት (ግንቦት 2016 ዓ.ም) ምክር ቤቱ 20ኛ ዓመት የምስረታ ቀኑን በአዲስ አበባ አክብሯል። ምክር ቤቱ በአህጉሪቷ ግጭቶች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ መከላከል፣ የግጭት አስተዳደርና አፈታት ላይ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪ አካል ነው። በአህጉሪቷ ለሚከሰቱ ግጭቶች ጊዜውን የጠበቀ እና በቂ ምላሽና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ለአፍሪካ የሰላም እና ደህንነት ማዕቀፍ (African Peace and Security Architecture) ቁልፍ ምሰሶ ነው። የምክር ቤቱ አወቃቀር፣ ተልዕኮና ሚና ከአወቃቅር አኳያ ምክር ቤቱ ዕኩል ድምጽ ያላቸው 15 አባል አገራት ይኖሩታል። አባላቱም በሕብረቱ የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ይመረጣሉ። በመሪዎች ጉባዔ አባልነታቸው ይጸድቃል። ከአባላቱ መካከል አምስቱ ለሶስት ዓመታተ፤ ቀሪዎቹ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ስልጣን አላቸው። ምክር ቋሚ አባል አገር የለም። የአባልነት ጊዜ የጨረሱ ሀገራት ግን ድጋሚ የመመረጥ መብት አላቸው። አባላት የሚመረጡት ግን በቀጣናዊ ውክልና እና በተራ ቅደም ተከተል መርህ ነው። ይኼውም ማዕከላዊ፣ ምሥራቃዊ፣ ደቡባዊ እና ሰሜናዊ ቀጣናዎች ሶስት አባል ሀገራት ሲሆኑ የምዕራብ ቀጣና ግን አራት አባል አገራት ይኖራቸዋል። በምክር ቤት ሕገ ደንብ መሰረት ለምክር ቤቱ አባል ለመሆን ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ይሄውም የአፍሪካ ሰላምና ደህንነትን በማስተዋወቅና በማረጋገጥ ያለው አስተዋጽኦ፣ በቀጣናዊና በአህጉር አቀፍ ደረጃ በሰላም ማስከበር እና በሰላም መፍጠር ውስጥ ያለው ሚና፣ ቀጣናዊና አህጉር አቀፍ የግጭት መፍቻ ኢኒሺቲቮች ለመሳተፍ ያለው ፍላጎት እና ኃላፊነት ለመውሰድ ያለው ቁርጠኝነት፣ ለአፍሪካ ህብረት የሰላም ፈንድ የሚያደርገው አስተዋጽኦ፣ ለሕገ መንግስት አስተዳደር፣ የሕግ የበላይነት እና የሰብዓዊ መብቶች ያለው ከበሬታ እንዲሁም ለአፍሪካ ሕብረት የፋይናንስ መዋጮ ግዴታዎች ያለው ተገዢነት እና ቁርጠኝነት አንድን አገር አባል ሆኖ እንዲመረጥ የሚያስችሉት መስፈርቶች ናቸው። ምክር ቤት ከሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ጋር በመጣመር ከስር የተመላከቱ ስልጣንና ተግባራቱ ተሰጥቶታል። . ዘር ማጥፋትና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሊያመራ የሚችል የግጭት አዝማሚያን መተንበይ፣ አስቀድሞ በመከላከልና የግጭት መንስዔዎችን ለይቶ ፖሊሲ መቀየስ። የጦር ወንጀሎች፣ ዘር ማጥፋት እና የሰብዓዊነት ወንጀሎች ሲፈጸሙ ለመሪዎች ጉባዔ ሕብረቱን ወክሎ ጣልቃ መግባት የሚችልበትን ምክረ ሀሳብ ያቀርባል። . ለግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ በማስቻል ሰላም መገንባት ላይ ይሰራል።የአፍሪካ ሕብረት አጠቃላይ የጋራ የመከላከያ ፖሊሲ ይተገብራል። . ለሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ፈቃድና ስምሪት ይሰጣል፤ የሰላም አስከባሪ ኃይል የስራ ኃላፊነት ጨምሮ ተልዕኮውን የተመለከቱ መመሪያዎችን ያወጣል። . በአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት ኢ-ሕገመንግስታዊ የመንግስት ለውጥ ሲኖር ማዕቀብ ይጥላል። . የፀረ-ሽብርተኝነትን ዓላም አቀፍ ስምምነቶች የአባል ሀገራት ትግበራን ይከታተላል። በመልካም አስተዳደር፣ በሕግ የበላይነት፣ የሰብዓዊ መብቶች እና መሰረታዊ ነጻነቶች እና ሰብዓዊ መብቶች ላይ ጥበቃ ያደርጋል። ቀጣናዊና አህጉራዊ የተቀናጀ የሰላምና ደህንነት አሰራርን መፈጸሙንም እንዲሁ። በጦር መሳሪያ ቁጥጥርና ትጥቅ የማስፈታት የሕግ ማዕቀፎችን ትግበራ ይደግፋል። . የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራትን ነጻነት እና ሉዓላዊነትን ስጋት ላይ የሚጥሉ የኃይል እርምጃዎችን በመመርመር እርምጃ ይወስዳል። . በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ወቅት ለሰብዓዊ ድጋፍ ያስተባብራል። አፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የሰላምና ደህንነት የስራ ክፍል ውስጥ የሚገኘው የምክር ቤቱ ሴክሬተሪያት ለምክር ቤቱ የኦፕሬሽን ስራዎች የቀጥታ ድጋፍ ያደርጋል። ምክር ቤቱ በአህጉሪቷ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት፣ “Panel of the Wise” በተሰኘው የአፍሪካ ሕብረት የማማከር አደረጃጀት፣ በአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል እና የሕብረቱ የሰላም ፈንድ ድጋፍ ይደረግለታል። በምክር ቤቱ በስሩ ያሉት ወታደራዊ አባላት እና የባለሙያዎች ቡድን ኮሚቴዎች፣ የአፍሪካ የሰላምና ደህንነት ማዕቀፍ (APSA)፣ የአፍሪካ የሴቶች ግጭት መከላከል እና የሰላም ድርድር ኔትወርክ (FemWise–Africa) እንዲሁም የሰላምና ደህንነት ማስከበር ተልኮዎች ሌሎች ደጋፊ አካላት ናቸው። ምክር ቤቱ ከቀጣናዊ የኢኮኖሚ ተቋማት እና ከሌሎች ቀጣናዊ አደረጃጀቶች ጋር ግጭትን አስቀድሞ መከላከል፣ አስተዳደር እና መፍትሄ ላይ በጋራ ይሰራል። ከተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እና ሌሎች መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት እንዲሁም ፓን-አፍሪካ ፓርላማ እና የአፍሪካ የሰብዓዊና የህዝብ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ ከሌሎች የአፍሪካ ህብረት አደረጃጀቶች ጋር በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይም በትብብር እየሰራ ይገኛል። የአፍሪካ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት ኃላፊነቶች፣ አደረጃጀቶች እና የቅንጅት አሰራር ማዕቀፎች በአህጉሪቷ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያለውን ቁልፍ የውሳኔ ሰጪነት አቅም የሚያሳይ ነው። ኢትዮጵያ እና ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ለመወዳደር የፈለገቸው ለሶስት ዓመት (በአውሮፓዊያኑከ2025 እስከ 2027) ድረስ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የሕብረቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮች ለአፍሪካ የዋለችውን ታሪካዊ ሚና ከግንዛቤ በማስገባት በውሳኔ ሂደቱ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል። በርግጥ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ያላት ቁልፍ ሚና ተገቢነቱ አያጠራጥርም። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ለረጅም ዘመናት በቁርጠኝነት ሰርታለች። የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ሄኖክ ጌታቸው (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት አባል ሆና ማገልገሏን ያስታውሳሉ። ምክር ቤቱ የአሁኑን ስያሜውን ከማግኘቱ በፊት በቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) ማዕቀፍ ከእ.አ.አ 1993 እስከ 2000 ባለው ጊዜ አባል ሆና ማገልገሏን ገልጸዋል። በአፍሪካ ሕብረት ደግሞ በአውሮፓዊያኑ ከ2004 እስከ 2010 እንዲሁም ከ2014 እስከ 2016 አገልግላለች። ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ሆና ብትመረጥ ብሔራዊና ቀጣናዊ ፍላጎቶቿንና ጥቅሞቿን ከማስጠበቅ እና አንጻር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንደምታገኝ ሄኖክ(ዶ/ር) ይናገራሉ። የምክር ቤቱ አጀንዳዎች ከብሔራዊ ጥቅሞቿ ጋር አጣጥሞ ለመሄድና ፍላጎቶቿን የሚጻረሩ ጉዳዮች ለመከላከል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላትም በማንሳት። የአፍሪካ ዋንኛ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ አብዛኛውን ትኩረቱን አፍሪካ ቀንድ ከማድረጉ አንጻር ኢትዮጵያ በአካባቢው ባሉ ጉዳዮች ላይ ያላት ሚና እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው ያሉት ከፍተኛ ተመራማሪው። ቀጣናው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሚስብ መሆኑ ያሉ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ የበኩሏን ድርሻ መወጣት እንደምትችልም ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ አባልነት የሕብረቱ የመመስረቻ ቻርተርና የህግ ማዕቀፎች እንዲጠበቁ፣ አህጉራዊ አጀንዳዎችን ለማራመድ፣ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈንና በቀጣናው ከምትጫወተው ሚና አንጻር በርካታ ጠቃሜታዎችን እንደምታገኝ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ለመሆን የተሻለ የተወዳዳሪነት ብልጫ እንዳላት ያነሳሉ። ለምን ቢባል አንድም ኢትዮጵያ በሩዋንዳ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በላይበሪያ፣ በኮንጎ፣ በሶማሊያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት በሰላም ማስከበር ተሳትፎ በማድረግ ያላት ልምድ ነው። አንድም የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ መሆኗና ከዚህ ቀደም በምክር ቤቱ የነበራት ግልጋሎት እንደ የተወዳዳሪነት ብልጫ እንድታገኝ ያስችላታል። አባልነቷን ለማረጋገጥ ግን ከሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችና ሌሎች የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን ይጠበቃል ይላሉ። ምከር ቤቱ በሕብረቱ የሰላም እና የደህንነት ምክር ቤት የአፍሪካ የሰላምና ደህንት ጉዳዮች ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪ አካል በመሆኑ አባል ብትሆን ካላት ታሪካዊ አበርክቶ አኳያ ይበልጥ ለአህጉራዊ ሰላምና ደህንነት ገንቢ ሚና እንደምትጫወት ዕሙን ነው።
ወንዞቿን ከብክለት ወደ ትሩፋት ለመለወጥ የተነሳችው አዲስ አበባ
Jan 13, 2025 644
አዲስ አበባ ከተቆረቆራች አንድ ከግማሽ ምዕተ ዓመት ልትደፍን ጥቂት ዓመታት ይቀራታል። ከተማዋ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ዑደት አስኳል ሆና ሁሉን አስተናግዳለች። ዕድል ቀንቷት ከኢትዮጵያዊያን አልፋ የአፍሪካዊያን መዲና ሆናለች። ዘመን ችሯት የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከል አድርጓታል። ከአፍሪካ ወደ ዓለም፤ ከዓለም ወደ አፍሪካ መግቢያና መውጫ በር ናት። የሀገሪቷ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት የስበት ማዕከል ናት። በፍጥነት ያደገችና ነዋሪቿን ያበዛች፤ ምጣኔ ሀብትን ያጎለመሰች ከተማ ናት። ዳሩ የከተሜነት መዋቅራዊ ፕላኗ አኳያ ውስንነቶች እንደሚስተዋልባት በባለሙያዎች ዘንድ ይነሳል። ትውልድን ታሳቢ ያደረገ ዘመን ተሻጋሪ፣ ለኑሮ ምቹና ስሟን የሚመጥን የክትመት ዕቅድ ይዛ ባለመጓዟ ውበትም፤ ኑረትም፣ ምቾትም አጉድላለች። በጽዳትና ውበቷ ረገድ በእንግዶቿም ዘንድም ለትቸት ተጋልጣ ታውቃለች። ከአዲስ አበባ ድክመቶች አንዱ የብዙ ወንዞች ባለቤት ሆኗ አንዱንም እሴት ጨምራ ወደ ሀብትትነት አለመቀየሯ ነው። ፈሳሽ ወንዟን አልምታ በውበት አለመፍሰሷ። በመዲናዋ ከ76 ያላነሱ ዋና እና ገባር ወንዞች ይገኛሉ። ዳሩ በየዘመኑ የከተማ ልማት ዕቅዶች የወንዝ ዳርቻን ታሳቢ ባለማድረጋቸው ወንዞቿ ለገጽታዋ ውበት ሳይሆን ሳንካ ሆነዋታል። የከተሜነት ወጓ ከወንዞቿ ልማት ጋር አልተመራም። የሰዎች አሰፋፈር ከዓለም አቀፋዊ የከተሜነት ልክን አልጠበቀም። ይህ ደግሞ ወንዞች ለነዋሪዎቿ ጠንቅ እንጂ ትሩፋት እንዳይሆኑ አድርጓል። በርካታ ሀገራት ከተሞች ጥቂት ወንዞቻቸውን ለጌጥም፤ ለበረከትም አውለዋል። ባለበዙ ወንዞች ባለቤቷ አዲስ አበባ ግን "ጽድቁ ከርቶ..." እንዲሉ ከወንዞቿ ጥቅሟ ቀርቶ፤ ጠንቋ በዝቶ ቆይታለች። ወንዞቹን ለምተው ለዘርፈ ብዙ አገልግሎት ከመዋል ይልቅ ለብክለት ተጋልጠው ለሕዝብ ጤና ጠንቅ ነበሩ። በክረምት ወራትም ጎርፍ እየተሞሉ ነዋሪዎችን ለአደጋ አጋልጠዋል። እነሆ አሁን የዘመናት ክፍተቷን ለመቅረፍ ተነስታለች። ከተማ አቀፍ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ተጀምረዋል። የመዲናዋን ወንዞች ከሕዝብ ጤና ጠንቅነት ወደ ጥቅም የመለወጥ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል። በአዲስ አበባ ከሚፈሱ ወንዞች መካከል እስካሁን አንድ ወንዝ ለቱሪስት መስህብነት፣ ለመዝናኛነትና ለሌላ አገልግሎት ለማዋል የተሰራ የተፋሰስ ልማት እየተከናወነ ነው። የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የበርካታ ሀገራት ከተሞች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ወንዞችን አልምተው ለቱሪስት መነሃሪያ እንዲሆኑ በማስቻል ለቱሪዝም ዘርፍ እመርታ ወሳኝ ድርሻ እንዲይዙ ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ። አዲስ አበባ ግን በርካታ ወንዞችን ታቅፋ ይህን መልካም ዕድል አልምታ ሳትጠቅም በመቆየቷ ቁጭት የሚፈጥር ጉዳይ እንደሆነ ያነሳሉ። እናም እየተከናወነ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት የህብረተሰቡን አኗኗር ብቻ ሳይሆን ለተፋሰስ ልማትም ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ወንዞች ከጠንቅነት ወደ ህዝብ ጥቅምነት የመለወጥ ስራዎች እንደቀጠሉ ከንቲባዋ አብስረዋል። በዚህም አዲስ አበባ ካሏት 76 ወንዞች መካከል አንድ ሶስተኛው ትልልቅ ወንዞቿ ለቱሪስት መዝናኛ አገልግሎት መዋል የሚችሉ ናቸው ብለዋል። ከነዚህም መካከል እስካሁን ሁለት ወንዞችን በወንዝ ዳርቻ ልማት በማስገባት ወደ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የመለወጥ ጉዞ መጀመሩን ተናግረዋል። በትናንትናው ዕለት የከተማዋ አመራሮች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማቶችን ጎብኝተው ነበር። ከተጎበኙ የከተማ ልማት ስራዎች መካከል የቀበና ቁጥር-1 እና 2 እንዲሁም ከእንጦጦ-ፍሬንድ ሽፕ- ፒኮክ የወንዝ ዳርቻ ልማት ይገኝበታል። ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የወንዝ ዳርቻ ልማት ከብክለት ነጻ አካባቢን በመፍጠር፣ ከተማዋን ጽዱና አረንጓዴ በማድረግና በሽታን በመከላከል ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። የእንጦጦ-ፍሬንድ ሽፕ- ፒኮክ የወንዝ ዳርቻ ልማት የተለያዩ ፓርኮችን በማስተሳሰር በፕላን የተገነባ ከተማን እውን ማድረግ የሚያስችል እንደሆነ በማብራራት። በቀበና ቁጥር 2 እንዲሁም ከእንጦጦ- ፍሬንድ ሽፕ- ፒኮክ የወንዝ ዳርቻ አፍንጮ በር አካባቢ የመጓተት ችግሮችን በመቅረፍ ስራው በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። 70 ደረጃ እና 40 ደረጃ ታሪካዊ ቅርስነታቸውን ጠብቀው እየታደሱ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ከዕይታ ተደብቆ የቆየውን የራስ መኮንን ሀውልት ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ዕድሳት ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ፒያሳ አካባቢ እየተሰራ የሚገኘው የወንዝ ዳርቻ ልማት አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የሩጫ፣ የሳይክል፣ የመዋኛና ሌሎች ቦታዎችን ነው። ልማቶቹ አለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችንና ሁነቶችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ እንደሆኑ ከንቲባዋ በጉብኝቱ ወቅት አብራርተዋል። የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ፓርኪንግ፣ የታክሲ ተርሚናል፣ ሱቆችንና ሌሎች ልማቶችን አካቶ እየተሰራም ነው። ፕላኑን የጠበቀ ዘመናዊ ከተማን እውን የሚያደርግ ከንቲባዋ ጠቁመዋል። የወንዝ ዳርቻን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አቀፍ የልማት ስራዎች ዘመናዊ ከተማን ያሟሉ በመሆኑ ለአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ይጨምራሉ።
የምግብ ሉዓላዊነት፤ ከተረጂነት እና ጠባቂነት መላቀቂያ መንገድ
Jan 10, 2025 492
ኢትዮጵያ ራሷን ከተረጂነት ለማላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች። የዜጎችን የምግብ ፍላጎት በራስ የምርት አቅም የመሙላት ስራ በማከወን ከውጭ አገራት ምርት ጠባቂነት ለመላቀቅ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው። ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ከልመና ወጥታ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ ገበያ መላክ መጀመሯ ትልቅ ታሪካዊ ድል ነው። ከውጭ የኢኮኖሚ ጥገኝነት በመላቀቅ የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት ለማስከበር በስንዴ ልማት የተመዘገበውን ስኬት በሌሎች የግብርና መስኮች ለመድገም በመሰራት ላይ ይገኛል። በሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ሻይ ቅጠልና ሌሎች የተለያዩ ሰብሎች ላይ እየተከናወነ ያለው ስራ ተጨባጭ ውጤቶች እያስገኘ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምግብ ዋስትናና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ የአመራር ቁርጠኝነት ከዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) የአግሪኮላ ሜዳልያ በጥር ወር 2016 ዓ.ም ያበረከተው ሽልማት ለምግብ ሉዓላዊነት ጥረት የተሰጠ እውቅና ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ መንግስት ረሃብን ሙሉ በሙሉ ከማስቀረት ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ብሔራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን በሽልማቱ ወቅት ገልጸው ነበር። ኢትዮጵያ በርካታ ያልተነኩ ጥሬ ሃብቶች፣ ተስማሚ የአየር ንብረትና ለስራ ትጉ የሆነ ወጣት እንዳላት እና እነዚህን ሃብቶች ታሳቢ በማድረግ የታሪክ አውራ የሆነችውን ሀገር ልማት ወደፊት ለማራመድ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዋጋ እንደከፈልን ሁሉ ከምግብ ጥገኝነት ለመላቀቅ በትጋት መስራት እንደሚገባ ተናግረው ነበር። የምግብ ሉዓላዊነት፣ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት፣ የበጀት ሉዓላዊነት፣ ታላቁን የሀገር ሉዓላዊነት በጽናት የሚያቆሙ ናቸው። እነዚህን የሉዓላዊነት ዘርፎች ለማስከበር አዲሱ ዓይነት አርበኝነት ያስፈልገናል። ይህም የብሔራዊነት አርበኝነት መሆኑንም ከዚህ ቀደም መናገራቸው ይታወቃል። የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገበችውን አኩሪ ድል በዘመናዊ ግብርና የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ እንደግመዋለን ሲሉ ገልጸው ነበር። በዓድዋ የዘመኑ ጀግኖች የሀገራቸውን የግዛት ሉዓላዊነት እንዳስከበሩት ሁሉ፣ የዚህ ዘመን ትውልድ ደግሞ ሌላ የራሱን ታሪክ መጻፍ እንዳለበት አንስተዋል። በዚህ ዘመን ደግሞ የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ድሉን ለመድገም ትልቅ ተጋድሎ እያደረገች ነው ብለዋል። ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያሏትን ጸጋዎች እና ሀብቶች አሟጦ በመጠቀም ከተረጂነት ተላቆ ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች። ከነዚህ ስራዎች መካከል አንዱ ከረድኤት ተቋማት ከሚደረግ የሰብዓዊ ድጋፍ ተላቆ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተደረገ ያለው ጥረት ይገኝበታል። የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በራስ አቅም የሰብዓዊ ድጋፍን መሸፈን ይገባል በሚል እሳቤ አዲስ ስትራቴጂ ነደፎ እየሰራ ይገኛል። ይህ በስራ ላይ የዋለው ፖሊሲ የሀገርን ሉዓላዊ ነፃነት እና የዜጎችን ክብር በማስጠበቅ አደጋን በራስ አቅም ምላሽ በመስጠት የክምችትና የመጠባበቂያ ፈንድ አቅምን ማጎልበት የሚያስችል መሆኑን አስታወቋል። ለዚህም ሀገር አቀፍ የስትራቴጂክ መጠባበቂያ ክምችት አቅም ከ23 በመቶ ወደ 47 በመቶ የሚያሳድጉ ዘመናዊ የክምችት መጋዘኖች እየተገነቡ መሆኑን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል። ይህም የመፈጸም አቅምን በማሳደግ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን በሚል ስኬታማ የአሰራር ማሻሻያ ሥርዓት መዘርጋቱን የሚያሳይ ነው። በ2016 ዓ.ም ጸድቆ ወደ ስራ የገባው የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲ ዋነኛ ማጠንጠኛው በራስ አቅም የሰብዓዊ እርዳታን መሸፈን ላይ ያተኮረ ነው። የክልሎች ራስን የመቻል ስራዎች ፖሊሲው የውጭ እርዳታን ብቻ ሳይሆን ክልሎች ከፌደራል መንግስት ድጋፍ ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ አቅም መገንባት ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ የሚያመላክት ነው። በዚሁ መሰረት ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ስድስት ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄዎችን በራሳቸው መሸፈን የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል። በቀጣይም ሁሉም ክልሎች ራሳቸውን እንዲችሉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጿል። በኦሮሚያ ክልል ለመጠባበቂያ እህል ክምችት የሚውል ከ43 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመኸርና በበጋ ወራት እርሻ በማልማት 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ መረጃ ያመለክታል። በክልሉ ከማኅበረሰቡ የቆየ የመረዳዳት እሴት ተቀድቶ በክልሉ "ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ" በሚል ስያሜ በተቋም ደረጃ ተቋቁሞና ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየሰራ ይገኛል። እየተከናወነ የሚገኘው የእርሻ ሥራ ክልሉ አሁን ላይ ያለውን 100 ሺህ ኩንታል የመጠባበቂያ እህል ክምችት ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የሚያሳድግ መሆኑንም ተመላክቷል። በክልሉ የምርት ማከማቻ መጋዘኖችን በሕዝብ ተሳትፎ በክልሉ በሚገኙ 21 ዞኖችና በተመረጡ ስምንት ከተሞች ላይ ለመገንባት የዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው ወደ ስራ ተገብቷል። በአማራ ክልል ከተረጅነት ለመላቀቅና እርዳታን በራስ አቅም ለመሸፈን በ36 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመጠባበቂያ እህል ክምችት የሚውል ሰብል ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል። በክልሉ በ2016/17 ምርት ዘመን ልማቱን በ36 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለማካሄድ ታቅዶ እስካሁን ከ27 ሺህ 700 ሄክታር የሚበልጥ መሬት በመለየት ወደ ተግባር መግባቱን ቢሮው ገልጿል። ለምርት ማሳደጊያ የሚውል 1 ሺህ 914 ኩንታል ማዳበሪያና 1 ሺህ 154 ኩንታል ምርጥ ዘር ቀርቦ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሚገኝም እንዲሁ። በራስ አቅም የመጠባበቂያ እህል በማምረት ዕርዳታን ሳይጠበቅ ለችግር ለሚጋለጡ ዜጎች ተደራሽ በማድረግ ክልሉን ከተረጅነት ለማላቀቅ የተያዘው ግብ እንዲሳካ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ቢሮው አመልክቷል። ሌላኛው የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ የመሸፈን አቅም ጥረት ማሳያ የሲዳማ ክልል ነው። በክልሉ ለአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ የሚሆን የምግብ ሰብል ክምችት በወል መሬት የማልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተጠቁማለ። በዚህም በክልሉ በመኸር እርሻ 800 ሄክታር የወል መሬት ለአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ እንዲሆኑ በተለያዩ ሰብሎች መልመካቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። የሲዳማ ክልል የተረጂነት ጉዳይ የሉአላዊነት ጉዳይ መሆኑን ከግምት በማስገባት በራስ አቅም የመጠባበቂያ ምግብ ክምችት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብአዊ እርዳታን በራስ አቅም ለመሸፈን የክልሉ መንግስት የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በራሱ እያለማ ያለው የሰብል ማሳ የዚሁ ስራ ማሳያ ነው። ኮሚሽኑ በዘንድሮው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በ56 ሄክታር ማሳ ላይ በቆሎ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተር እና ሌሎች ሰብሎችን እያለማ እንደሚገኝ ገልጿል። በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች በምግብ ራስን መቻል እና ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን በሚል መርህ የተለያዩ ሰብሎች እየለሙ መሆኑንም አመልክቷል። ሌላኛው በተሞክሮነት የሚጠቀስ ስራ እያከናወነ የሚገኘው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ነው። ክልሉ ለድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋ በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል። እምቅ የልማት አቅምን በመጠቀምና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን መቻል የክልሉ መንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው አድርጎታል። በዚህም በቀጣይ ሁለት ዓመታት በክልሉ የሴፍቲኔት መርህግብር ተጠቃሚዎችን ወደ ዘላቂ ልማት በማሸጋገር ከተረጂነት የሚወጡበት ልዩ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። አረንጓዴ አሻራ እና የሌማት ትሩፋትን በማስተሳሰር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በክልሉ ከተረጂነት ወጥቶ ራስን ለመቻል እየተደረገ ያለው ጥረት ማሳያ ናቸው። ሌሎች ክልሎችም በራሳቸው አቅም የሰብዓዊ ድጋፍ ለመሸፈን በመስራት ላይ ይገኛሉ። ተግባራቱ ከተረጅነት ለመላቀቅና እርዳታን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተደረገ ያለውን የባህል ለውጥ በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው። የመውጫ ሀሳብ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ወገኖችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል አሁናዊ በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ ክምችትና ዝግጅት መኖሩን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። መንግስት በተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚከሰቱ አደጋዎችን መቋቋም የሚያስችሉ ሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተዋል። በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች የሚከሰቱ አደጋ ስጋቶችን ለመቋቋምና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለመድረስ ማህበረሰቡ እርስ በርስ የሚተጋገዝበትን ስርዓት ለማጠናከር ትኩረት መደረጉንም እንዲሁ። በሌላ በኩል የመጠባበቂያ ክምችት በመፍጠር ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም በዘላቂነት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ሀገራዊ አቅም ለመፍጠር ወደ ስራ መገባቱንም ኮሚሽነሩ አንስተዋል። በዚህም ካሳለፍነው ክረምት ጀምሮ እስከ በ2017/2018 የምርት ዘመን 253 ሺህ ሄክታር መሬት በማረስ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ወይም 20 ሚለዮን ኩንታል ምርት በማምረት መጠባበቂያ ክምችት ለመያዝ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። እስከ አሁንም 108 ሺህ ሄክታር መሬት መታረሱን ገልፀው፤ ይህም የዕቅዱን 43 ከመቶ ይሸፍናል ነው ያሉት። ዕቅዱን ዕውን በማድረግ እንደ ሀገር ሙሉ የመጠባበቂያ ክምችት በመያዝ በፌደራልና በክልል ደረጃ ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ። በሀገር ደረጃ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት አቅም የሚፈጥሩ ናቸው። ኢትዮጵያ ከ26 ሀገራት ለመጡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን አስጠልላ ከለላና የተለያዩ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ትገኛለች። እንደ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት መረጃ ከሆነ በስደተኞች ስም የመጣ ማንኛውም ድጋፍ ለታለመለት ዓላማመዋሉን የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ከዋና መሥሪያ ቤት ጀምሮ የስደተኛ ማዕከላት ድረስ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ዘርግቶ እየሠራ ይገኛል። በዚህም መሠረት ሩሲያ የደቡብ ሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የገቡና በጋምቤላ ክልል ለተጠለሉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) በኩል 1 ሺህ 632 ነጥብ 4 ሜትሪክ ቶን የስንዴ ድጋፍ ትናንት አድጋለች። የስደተኞች ሰብዓዊ ድጋፍ ከተለያዩ መንግስታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚደረግ ድጋፍ በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ሲከናወን ቆይቷል፤ የአሁኑ ድጋፍም የተደረገው ለተመሳሳይ ዓላማ እንደሆነም አገልግሎቱ አመልክቷል። ኢትዮጵያ የአጋር አካላት ድጋፍ መቀዛቀዙን ተከትሎ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የተለያዩ አገራት ስደተኞች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥሪ ማቅረቧ ይታወቃል። ዓለም አቀፍ ረጂ አካላትም ስደተኞች ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ መሠረታዊ አቅርቦት እንዲያገኙ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ስትገልጽ ቆይታለች። በሀገር ደረጃ እየተደረጉ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት አቅም የሚፈጥሩ ናቸው። ኮሚሽኑ የሰብዓዊ አገልግሎት፣ ዘላቂ ልማትና የሰላም ጥምረትን በማረጋገጥ ዕውቀት መር በራስ አቅም አደጋን ምላሽ የሚሰጥ ተቋም ለመገንባት የማሻሻያ እርምጃዎችን ወስዷል። የራስ አቅም ግንባታው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በ2030 ዓ.ም ለአደጋ ስጋት የማይበገር ማህበረሰብን ለመገንባት እቅድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ሀገራዊ ትልሙ ኢትዮጵያን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብር፣ ነጻነት እና ሉዓላዊነት የሚያሸጋግር መልካም ጅማሮ ነው።
የኃይል ልማት ለቀጣናዊ ትስስር
Jan 3, 2025 404
ወዳጅ ማብዛትና አጋር ማበራከት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መርህ ነው። ፖሊሲዋ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያና ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ለቀጣናዊ ትስስር፣ የጋራ እድገትና ተጠቃሚነት ትኩረት የዲፕሎማሲዋ አስኳል ነው። ቀጣናዊ ትስስሩን ዕውን ለማድረግ ከፊት ተሰላፊ ሀገር ናት። በዚህም በትብብር ዲፕሎማሲና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጎልበት የጋራ ልማትን ማረጋገጥ ሰርክ ታነሳለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ የሁልጊዜም ፍላጎት በቀጣናዊ ትብብር ከጎረቤት አገራት ሰላም እንዲመጣ በትብብር መሥራት፣ አብሮ ማደግና በጋራ መበልጸግ መሆኑንም በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣል። ከቀጣናው ሀገራት ትብብር መስኮች አንዱ በኃይል መሰረተ ልማት መተሳሰር መሆኑ እሙን ነው። ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ መባሏ በምክንያት ነው። ከወንዞቿ በዓመት 124 ቢሊዮን ኪዩብ ሜትር እንዲሁም ከከርሰ ምድር ከ36 እስከ 40 ቢሊዮን ኪዩብ ሜትር ውሃ ሀብት እንዳላት መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ የውሃ ሀብቷ ደግሞ ታዳሽ ኃይል ግንባታ አይተኬ ሚና አለው። የውሃ ሀብቷ ከፀሐይ፣ በነፋስ እና በጂኦ-ተርማል የኃይል አማራጮች ጋር ተዳምሮ ከ300 እስከ 400 ጊጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አላት። በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅዷ ኢትዮጵያ የምታመነጨውን የኃይል መጠን አሁን ካለበት 4 ሺህ 818 ሜጋ ዋት ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ለማሳደግ ግብ ተቀምጧል። የተሻሻለው የኢነርጂ ፖሊሲዋም ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ዕውነታ መሰረት ያደረገ እና ጎረቤት ሀገራትን በኃይል መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ያለመ ነው። በ10 ዓመት መሪ ዕቅዱ መሰረት ለጎረቤት አገራት እየቀረበ ያለውን 2 ሺህ 803 ጊጋ ዋት ሰዓት ሽያጭ ወደ 7 ሺህ 184 ጊጋ ዋት ሰዓት ለማሳደግ ውጥን ተይዟል። ኢትዮጵያ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ለጅቡቲ በ2011፣ ለሱዳን በ2012፣ ለኬንያ በ2022 እንድሁም በቅርብ ጊዜ ለታንዛኒያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ጀምራለች። የኃይል ሽያጩ በየዓመቱ እያደገ መጥቶ በ2015 በጀት ዓመት ወደ 101 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር እንዳደገ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመለክታል። የቀጣናው ከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ (ሃይዌይ) ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ ኢትዮጵያና ኬንያን፤ በቅርብ ወደ አገልግሎት የገባው ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ኬንያንና ታንዛኒያ አስተሳስሯል። የኃይል አቅርቦቱ ከሶስቱ ሀገራት ባሻገር ለቀጣናው ሌሎች ሀገራትም ትስስር መሰረት ጥሏል። ኢትዮጵያ በቀጣይ ለደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲና ሌሎች አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል የመሸጥ ዕቅድ ይዛለች። ወደ ደቡብ ሱዳን የሚደረገው ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በሂደት ላይ መሆኑ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኃይል አቅርቦት ረገድ የጋራ ልማትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ ነው የምታቀርበው። ሀገራቱ ከኢትዮጵያ የሚገዙት የኃይል አቅርቦት ደግሞ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፋቸው እመርታ ፈጥሯል። ይህ ደግሞ ወዲህ የጎረቤት ሀገራትን ቅድሚያ የሰጠውን ፖሊሲዋን በተግበር የገለጠ ነው፤ ወዲያ ደግሞ ከውጭ ምንዛሬ ግኝት ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስርን ለማጎልበት አይተኬ ሚና ይኖረዋል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት እንዲሁም ለአፍሪካ አጀንዳ 2063 ዕውን መሆን በኢነርጂ ዘርፍ ያላትን ቀዳሚ ስፍራ ያረጋገጣል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትስስር ሌላው በረከት ነው። ግንባታው በመጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ገጸ ብዙ ፕሮጀክት ነው። ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ልዩ በረከት ይዞ የመጣ፤ የታዳሽ ኃይል ልማት አብነት ነው። በዐባይ ወንዝ የዘመናትን ብክነትና ቁጭት የቋጨ ነው። በሌላ ጎኑ በራስ አቅም ብቻ የተጠናቀቀ ነው። በአፍሪካ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ ግድብና ለቀጣናው ሀገራት ትስስር መልህቅ ስለሆነም ፓን አፍሪካዊ ፕሮጀክት ያሰኘዋል። ኃይል ማመንጨት የጀመረው ግድቡ በዓመት 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል። እስካሁን በግድቡ አራት ተርባይኖች ኃይል እያመነጩ ነው። ግድቡ ተጠናቆ የሁሉም ተርባይኖች ስራ ተጠናቆ ወደ ምርት ሲገባ ሀገራዊ የኃይል አቅምን 130 በመቶ ያሳድጋል። ይህ ደግሞ አንድምታም ብዙ ነው። ሀገራዊ የኃይል ፍላጎትን ከመሸፈን አልፎ በቀጣነው ሀገራት ተደራሽ በመሆን የኢትዮጵያን አፍሪካን የማስተሳሰር ቀንዲልነት ያጎላል። ለዚህ ነው ግድቡ ለቀጣናው ሀገራት ገጸ በረከት ነው የሚያሰኘው። በርግጥ ከሕዳሴው ግድብ ባሻገር ሌላው ከአፍሪካ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የኮይሻ ኃይል ማመንጫም ለቀጣናዊ ትስስር መፋጠን ሌላው እድል ነው። በጥቅሉ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል የሀገራት ኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናክር እና የኢትዮጵያን የመሰረተ ልማት የማስተሳሰር ጽኑ ፍላጎት ማሳያ ነው። በተጨማሪም በክቀጣናው ዘላቂ የኤሌክትሪክ ገበያ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ክፍለ አሕጉራዊ ጥረት ነው። ጥረቱ የምሥራቅ አፍሪካ የሃይል ቋት (The Eastern Africa Power Pool-EAPP) በቀጣናው ሀገራት መካከል ድንበር ተሻጋሪ የሃይል ንግድ እና የሃይል መስመር ትስስርን ለማሳለጥ እኤአ በ2005 የተቋቋመ ተቋም ግብ እውን ከማድረግ ባለፈ አሕጉራዊ ምጣኔ ሃብታዊ ትስሰርን የሚያፋጥን ነው።
የቤተ መንግሥቱ ነገ…
Dec 28, 2024 13505
(እንደ ፈረንሳዩ ቨርሳይ፤ እንደ ሩስያው ፒተርሆፍ) በአየለ ያረጋል ማሟሻ… ከምድራችን ግንባር ቀደም ተናፋቂ አብያተ መንግሥታት መካከል ቬርሳይ አንዱ ነው። ከፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ በስተምዕራብ ወጣ ብሎ ይገኛል። ‘የሩስያዋ ቨርሳይ’ የሚሰኘው በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ የሚገኘው ፒተርሆፍ አብያተ መንግስሥታት ሌላው ነው። ሁለቱም አብያተ መንግሥታት ዛሬ አብያተ-መዘክሮች ሆነዋል። ተፈጥሮ፣ ታሪክና ቅርስ የተዛነቀባቸው የዕልፍ አዕላፍ ቱሪስቶች መነሀሪያ ናቸው። በአንድ ስፍራ የሀገር መልክ እና ልክ የተገለጠባቸው። የአዲስ አበባው ብሔራዊ ቤተ መንግሥትም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ‘የአፍሪካ ቨርሳይ’ መባሉ አይቀሬ ነው። ለምን ቢሉ ዘመንና ስፍራ ቢለያቸውም የታሪክ ዑደታቸው፤ የዘመን ቀለማቸው፣ የብዝሃ ቅርስ ባለቤትነታቸው ያመሳስላቸዋልና! የፈረንሳይ ንጉሳዊያን ቤተሰቦች በፈረንሳይ አብዮት ከቨርሳይ ቤተ-መንግሥት ተባረዋል። የሩስያ ዘውዳዊ ስርዓት (ፃሮች ስርዓት) በኮሚኒስቶች አብዮት ከፒተርሆፍ ቤተ-መንግሥት ላይመለስ ተገርስሷል። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሠለሞናዊ ዘውዳዊ ስርዓት ከብሔራዊ ቤተ መንግሥት ፍጻሜውን አግኝቷል!! ቨርሳይ ቤተ መንግሥት ለፈረንሳይ ከአራት ምዕተ ዓመታት በፊት ነው። ቨርሳይ ላይ የፈረንሳይ ግዛተ አፄ ንጉሥ ሉዊ 13ኛ ለአዳኞች ዕልፍኝ ገነባ። ልጁ ንጉሥ ሉዊ 14ኛ ደግሞ የቨርሳይ ቤተ መንግሥትን መሰረተ። በጊዜው ቅንጦት ተብሎ ፈረንሳያዊያን ‘እግዚኦ’ አሉ። በፈረንጆቹ 1661 የነገሰው ንጉሥ ሉዊ 14ኛ ግን ለመንግስቱ ክብር ዕፁብ ድንቅ የሆነውን የቨርሳይ ቤተ መንግሥቱን አነፀ። ሌሎች ነገሥታትም አሻራቸውን እያከሉ ኖሩበት። በተለያዩ አገልግሎቶችን አስተናግዶ፣ የፈረንሳይን አብዮት ጨምሮ መልከ ብዙ ታሪካዊ ሁነቶችን አስተናግዶ ዘመናት ተሻገረ። በጎርጎሬሳዊያኑ 1837 በወቅቱ ንጉስ ሉዊ ፕሊፕ የቨርሳይ ቤተ-መንግሥት ወደ ቤተ መዘክርነት ተለወጠ። እነሆ የቀድሞው ቨርሳይ ቤተ-መንግሥት ከነግርማ ሞገሱ 400 ዓመታትን ዘለለ። ዛሬ ከዓለማችን ምርጥና ዝነኛው ቤተ መዘክሮች አንዱ ነው። በአውሮፓዊያኑ ዘመን ቀመር በ1979 ዓ.ም ከጎንደሩ የፋሲል ቤተ መንግሥት ጋር በዩኔሰኮ የዓለም ቅርስነት ተመዘግቧል። በፈረንሳይ ባህልና ቅርስ ሚኒስቴር ስር ይተዳደራል። የቨርሳይ ቤተ-መዘክር ኪነ ሕንጻ ብቻ አይደለም። ስነ ውበት፣ ኪነ ሕንጻና ኪነ ጥበብ ጥግ የሚነበብበት ከ800 ሄክታር በላይ የሚሸፍን ሠፊ ምድረ ግቢ ነው። ቤተ መንግሥቱ 63 ሺህ 154 ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ 2 ሺህ 300 ቤቶች አቅፏል። የንጉስ ማደሪያ ቤት፣ ቋሚ ዐውደ ርዕዮች፣ ፋፏቴዎች፣ ሙዚየም፣ አረንጓዴ ስፍራ፣ የፈረሰኞች አካዳሚ፣ የገበያ ስፍራ፣ መናፈሻዎች፣ የቴኒስ መጫዎቻ ቦታ እና ሌሎች የተለያዩ ክዋኔ ስፍራዎችን በውስጡ አምቆ ይዟል። ቨርሳይ በጌጣጌጦቹ፣ በቅርፃ ቅርጾቹ፣ በስዕል ጥበቦቹ ሁሉ አጃይብ የሚያሰኝ ስፍራ ነው። ቨርሳይ ቤተ መንግሥት ቨርሳይ የፈረንሳይ የኩራት ትዕምርት ነው። የዓለማችን ቀዳሚዋ የቱሪስት መዳረሻ በሆነችው ፈረንሳይ ከተወዳጅና ተመራጭ የሀገሪቷ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል ቨርሳይ አንዱ ነው። በየዓመቱ 15 ሚሊዮን ሕዝብ ይጎበኘዋል። ይህ ማለት ከምስራቅ አፍሪካዋ ሩዋንዳ ጠቅላላ ሕዝብ ቁጥር የበለጠ ጎብኚ ቨርሳይ ላይ በየዓመቱ ይጎርፋል ማለት ነው። ከ2 ሺህ 500 በላይ ቀጥተኛ፣ ከ10 ሺህ በላይ ተዘዋዋሪ ስራ ዕድል ፈጥሯል። ቨርሳይን ጨምሮ ፈረንሳይ በዓመት እስከ መቶ ሚሊዮን ዶላር ገቢ ታመነጫለች- በትናንት ታሪክና ቅርሷ። ፒተርሆፍ ቤተ-መንግሥት የዘመናዊት ሩስያ መስራች ታላቁ ፒተር ቀዳሚ በንጉሥ ሉዊ 14ኛ ዘመን ወደ ፈረንሳይ ተሻገረ። በቨርሳይ ቤተ-መንግሥትን በክብር ተስተናገደ። በተመለከተው ትዕይንት ተደነቀ፤ ተገረመ። የፒተርሆፍ ቤተ መንግሥትን እንዲያንጽ ምክንያት ሆነው። ፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ይገኛል። ቀዳማዊ ፒተር በአውሮፓዊያኑ 1709 ታነጸ። ብዙሃኑ ፒተርሆፍን ‘የሩስያው ቨርሳይ’ ይሉታል። የክረምቱ ቤተ መንግሥትም ይሰኛል። የሩስያ ታሪክ፣ ጥበብና ቅርስ ማዕከል ነው። የሩስያ ጣሪያ አለባ ቤተ መዘክር(Open air musuem) በምትሰኘዋ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ከሚገኙ ቀዳሚ የቱሪስት መነሃሪዎች መካከል አንዱ ፒተርሆፍ ነው። ፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት በ3 ሺህ 934 ሄክታር ላይ ያረፈው ፒተርሆፍ በውስጡ ግዙፍ ቤተ መንግሥት፣ ዕውቁ የሳምሶን ፋውንቴን፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ፏፏቴዎች፣ መናፈሻዎች፣ ማራኪ ኪነ ሕንጻዎች፣ ጥንታዊ ስዕላት፣ ቤተ መዘከር እና ሌሎች የከበሩ ቅርሶችን ይዟል። የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ ፒተርሆፍን ምድረ ግቢ የማየት ዕድል ያገኘሁ ሲሆን ታሪክ፣ ቅርስና ተፈጥሮ እንዴት መሳ ለመሳ ተሰናስነው ሀሴትን እንደሚያላብሱ ታዝቤያለሁ። ሩስያዎች ታሪክና ቅርሳቸውን እንዴት ለዘመናት ጠብቀው እንጀራ እያበሰሉበት እንዳለም እንዲሁ። በአውሮፓዊያኑ በ1990 በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። በየዓመቱ በአማካይ ስድስት ሚሊዮን ቱሪስቶች ይጎበኙታል። ከቅዱስ ፒተርስበርግ ብቻ ሳይሆን ከመላዋ ሩስያ ምርጥ ቱሪስት መዳረሻዎች መካከ አንዱ ነው። ፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት በኢትዮ-ሩስያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የራሱ ታሪካዊ አሻራ እንዳለው መጥቀስ ተገቢ ነው። ይሄውም ከአድዋ ድል አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በ1887 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ(የራስ ደስታ አባት) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ሩስያን ሲረግጥ ደማቅ አቀባበል የተደረገለት በፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት ነበር። በፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ ልዑክ በፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት ፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ ከአጼ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ የተላኩ ስጦታዎችን ለንጉስ(ጻር) ኒኮላስ ዳግማዊ እና ለባለቤታቸው ቀዳማዊት አሌክሳንድራ ያስረከቡት ፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት ነበር። ከሩስያ ሲመለሱም ለአድዋ ጦርነት ስንቅ የሆኑ የጦር መሳሪያዎች እና የቀይ መስቀል አባላትን አስከትለው ተመልሰዋል። ይህም የሩስያው ቨርሳይ(ፒተርሆፍ) ከኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስራት ሌላ ታሪካዊ ገመድ እንዳለ ያረጋግጣል። ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ለኢትዮጵያ የምድረ ቀደምቷ ሀገር ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መንግስት የአአፄ ኅይለሥላሴን 25ኛ ዓመት(የብር ኢዮቬልዮ) የንግሥና ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ የተገነባ ነው። በ1953 ዓ.ም የመፈንቀለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ገነተ ልዑልን(አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ለቀው እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ መኖሪያቸው ይሄው ቤተ-መንግሥት ነበር። በደርግ ዘመን ወደ ‘ብሔራዊ ቤተ መንግሥት’ነት ስሙ ከመለወጡ በፊት ‘ኢዮቬልዮ ቤተ መንግሥት’ እየተባለ ሲጠራ ቆይትል። ከታላቁ ወይም ከዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ጋር በማነጻጸር ደግሞ የታችኛው ቤተ-መንግሥትም ይባል ነበር። በደርግ ዘመን ፋውንቴኖችና ሌሎች መዝናኛ ስፍራዎች ተገንብተውለታል። በኢሕአዴግ መንግሥት ደግሞ የርዕሰ ብሔሮች መኖሪያና እንግዳ መቀበያ ሆኖ አገልሏል። ሀገራዊ የክብር ክዋኔዎች መስተናገጃ ነው። የእንግሊዟን ንግስት ቪክቶሪያ ጨምሮ በርካቶች የዓለማችን ዕውቅና ዝነኛ መሪዎች ተስተናግደውበታል። በዚህ ቤተ መንግሥት የንግስቷ እልፍኝ የተባለ ክፍልም እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ። በኢጣሊያናዊው የኪነ ሕንፃ ባለሙያ ራፋዔል ፔትሮን የተነደፈው ቤተ መንግሥቱ፤ የኢትዮጵያን ባህላዊ የኪነ ሕንፃ እሴት እና የዘመናዊ ኪነ ህንፃ ለዛ አጣምሮ የያዘ እንደሆነ ይነገርለታል። አፄ ኅይለሥላሴ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት አፄ ሃይለሥላሴ (ያኔ ልዑል አልጋወራሽ ራስ ተፈሪ) በፈረንጆቹ 1924 የተመረጡ 39 አባላትን ያቀፈ ልዑክ መርተው መካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓን መጎብኘታቸው ይታወሳል። በአውሮፓ ሀገራትም የዓለማችን ምርጥ አብያተ መንግስታትና ታሪካዊ ስፍራዎችን ተመልክተዋል። ራስ ተፈሪ ከጎበኟቸውና ቀልባቸውን ከሳባቸው የፈረንሳይ ታሪካዊው ስፍራዎች መካከል የቬርሳይ ቤተ መንግሥት ይገኝበታል። አልጋ ወራሹ የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉዞ በሆነው በዚሁ ጉብኝት ወቅት ከፈረንሳይ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል። በውይይታቸውም ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ዋስትና ጉዳይ ቀዳሚው አጀንዳ እንደነበር ታሪክ ያወሳል። አስገራሚው ነገር ከአንድ ምዕተ ዓመት በኋላ በቅርቡ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ንግግር ያደረጉት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት አማኑኤል ማክሮን ‘ኢትዮጵያ የባህር መውጫ በር ያስፈልጋታል የሚለው ንግግር ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ ያሰኘዋል። የቤተ መንግስቱ ስፋት፣ ዘመናዊነትና ኪነ ሕንፃ ውበት ብቻ ሳይሆን በውስጡ የያዛቸው ቅርሶችና ያስተናገዳቸው ታሪኮች የተለዬ መልክ እንዲኖረው ያደርጋል። የዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ መነሻ ሀብቶችን አቅፏል። የቤተ መንግስቱ መገኛ ስፍራ የአዲስ አበባ ከተማ የተወጠነበት አስካል በመሆኑ ከሌሎች ታሪካዊ ስፍራዎች ሌላው ልዩ ገጽታው ያላብሰዋል። ቤተ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ብዝሃ ታሪክ ባለቤትነትና የምንጊዜም ነጻ ሀገርነት ማሳያ ትዕምርትም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከአራት ዓመት በፊት ቤተ መንግስቱንና ቅርሶቹን እያስጎበኙ፤ ያልተገለጠው ሀብት እሴት ተጨምሮበት ለጎብኚዎች ክፍት የማድረግ ሃሳባቸውን ማጋራታቸው ይታወሳል። ቤተ መንግስቱ ታድሶ ለሕዝብ ክፍት ቢደረግ ለሀገር ምን ያህል በረከት ይዞ እንደሚመጣ የሰጡት ማብራሪያም የብዙሃኑን ቀልብ የሳበ ነበር። ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከፍልውሃ፤ ከፊንፊኔ ባሕል አዳራሽ፣ ከግዮን ሆቴል እና ከአፍሪካ አዳራሽ ጋር የተያያዘ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የቤተ መንግሥት ምድረ ግቢ ከፍልውሃና ፊንፊኔ አዳራሽ ጋር ተዳምሮ ከ70 እስከ 80 ሄክታር ስፋት አለው። በትልልቅ ዛፎች ውብ ሀመልማላዊ ገጽታ የተላበሰ፤ ድንቅና ብርቅ ታሪካዊ ሀብቶች ይገኙበታል። “መሀል ከተማ ላይ ትልልቅ ዛፎች ያሉት፣ በጣም የሚገራርሙ ታሪካዊ ሀብቶችን የያዘ ስለሆነ ሙሉ ስራ ከተሰራለት በምንም መመዘኛ በየትኛውም የዓለም ክፍል ካሉ ካፒታል ሲቲዎች ሊወዳደር የሚያስችል በቃት አለው” ነበር ያሉት። ለአብነትም በቤተ መንግስቱ ውስጥ የሚገኙ መኪናዎችን የ’ካር ሙዚዬም’ ገንብቶ ለጎብኚዎች ክፍት ቢደረግ ኢትዮጵያ ምን ያህል ተጠቃሚ እንደምትሆን ጠቁመው ነበር። “እነዚህ መኪኖች እኛ ከተማም ይሁን ሌላ ዓለም በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። አይታዩም፤ ብርቅ ናቸው። እነዚህን በጣም ውብ በሆነ መንገድ የመኪና ኤግዚቪሽን ብንሰራ በጣም ብዙ ሰው መጥቶ ያያቸዋል። አንደኛ የንጉሥ መኪና ናቸው። ሁለተኛ አፍሪካ ውስጥ የዛሬ 50 ዓመት 60 ዓመት በዚህ ደረጃ የደረጀ ሀብት እንደነበር የሚያሳይ ነው። … አፍሪካ ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥንታዊ ታሪክ ያላት ከ50 ዓመት በፊት እንደዚህ አይነት ውቅር የደረጀ መንግስቷ የሚንቀሳቀስ ሀገር ናተ የሚለው ቀላል ትርጉም የሚሰጠው አይደለም” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላስደመመቻቸው ‘አምፊካር’ ስለተሰኘችዋ ተሽከርካሪ ሲያብራሩም “በጣም ከገረመኝ ነገር አምፊካር የምትባለውዋ መኪና ናት። በፊልም ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ የምናየው ነገር አይደለም። አምፊካር መሬት ላይ መኪና ነው፤ ውሃ ላይ ጀልባ ነው። እንደ ጀልባም እንደ መኪናም የሚያገለግል የዛሬ 50 እና 60 ዓመት ኢትዮጵያ ነበራት። የዛሬ ትውልድ አያውቀውም። ይህን ታሪክ ማሳየት እንችላለን” ብለዋል። የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ሀብቶችን ለትውልድ ለማስተማርም ለተቀረው ዓለም በማሳየትም የኢትዮጵያን ልክ ማሳየት እንደሚቻል“ይህንን በደንብ ለቱሪስቶች በማሳየት፣ በማስተማር የኢትዮጵያን ልክ ማሳየት ይቸላል። ይህን ለማድረግ እኛ አዳዲስ ታሪክ መፍጠር አይጠበቅብንም፤ ያለውን በወግ እና በልኩ ቦታው ካስቀመጥን በራሱ ከበቂ በላይ የሚያስደንቅና የሚያስደምም ብዙዎችን የሚማርክ ሆኖ እናገኘዋለን። … እዚህ ቤት ውስጥ ተራ የሚባል ዕቃ የለም። እያንዳንዱ ዕቃ ውድ ነው። ዙፋን ብንመለከት የማን ነበር ብለን ጥያቄ የምናነሳው አይደለም። ስም አለበት እንደ ማህተም። … በጣም ብዙ የሚገርሙ ብዙ ሀብቶች እዚህ ውስጥ አሉ። ብዙዎቹ በጣም በውድ የተሰሩ በወርቅ የከበሩ ናቸው። ሰው ቢያቸው ውብ የሆኑ ግን ስቶር ቢቀመጡ ትርጉም የሌላቸው” ሲሉ ነበር ያብራሩት። ቀጥለውም የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ያዘላቸው ታሪኮች፣ ቅርሶችና የስነ ጥበብ ውጤቶች ለኢትዮጵያዊያን ኩራትም እራትም እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል። ከኢትዮጵያ አልፎም የአፍሪካዊያን ታሪክ ማዕከል እንደሆነም እንዲሁ። “የኢትዮጵያን ታሪክ ለማሸጋገር ዕድል ይሰጣል። የትኛው የአፍሪካ ሀገር ነው በዚህ ልክ መጽሀፍ አለኝ ብሎ ማሳየት የሚችለው ብላችሁ መጠየቅ ነው። ጥንታዊ ታሪክ አለን ስንል ይህን የሚያህል መጽሀፍ ቅዱስ አለኝ የሚል የአፍሪካ ሀገር ከየትም ሊያመጣ አይችልም። ብዙ ሊነገር የሚችል ታሪክ በሚሳዝን መንገድ ታጭቆ ተቀምጧል። ሰብሰብ አድርገን ጸዳ፣ ጸዳ አድርገን ቦታው ላይ ብናስቀምጥ ልጆቻችን ታሪካቸውን፣ ማንነታቸውን ለማወቅ ዕድል ያገኛሉ። … እዚህ ቦታ ላይ ሰፊ ሰዓት ሊነገሩ የሚችሉ ታሪኮች፣ ቅርሶችና ፒክቸሮች አሉ። በዓለም ላይ ስመጥር መሪዎች ፎቶዎች ይታያሉ። ማሀተመ ጋንዲ አለ፤ ማርቲን ሉተር ኪነግ አለ። የአፍሪካ ታላላቅ መሪዎች አሉ። እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር ነጻ ሲወጣ መጀመረያ መጥቶ የሚጎበኘው የአፍሪካዋን ነጻ ሀገር ኢትዮጵያ ነው። ሁሉም ሀገር ታሪኩ እዚህ አለ። የኛ ታሪክ ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር መሪው የመጣበት ጊዜ፤ ለምን መጣ ብለን በትክክል ቀምረን ማስቀመጥ ከቻልን እያንዳንዱ ሀገር ነጻ የወጣበትን እና ነጻ እንዲወጣ የረዳችውን ሀገር ታሪክ፣ የራሱንም ታሪክ ያይበታል። ይህ እንግዲህ ከኛም አልፎ የሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ታሪክም እዚህ ውስጥ እንዳለና ለእነርሱ ለማሳየትም በጣም ምቹ ይሆናል። ለእኛ ብቻ ሳይሆን እነሱም ታሪካቸውን መጥተው እንዲያዩ ማድረግ ያስችላል ማለት ነው። በአንድ ክፍል ውስጥ ይህ ሁሉ ታሪክ ታጭቋል። ሕንጻ አድሰን እያንዳንዱን ክብር ባለው ቦታ ብናስቀምጠው ታሪክ ለማወቅ ያግዛል፤ ገንዘብ እንድናገኝበትም ይረዳል፤ ቱሪስት ይስባል” በማለት ነበር ያጠቃለሉት። ብዙ ሀብትና ታሪክ በጉያው የያዘው ብሄራዊ ቤተመንግስት ለዘመናት የተደበቀው ሀብትና ታሪኩ ተገልጦ እንደ ፈረንሳዩ ቨርሳይ፤ እንደ ሩስያው ፒተርሆፍ የሚሆንበት ጊዜ ደረሰ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ባደረጉት ንግግር መሰረት ብሔራዊ ቤተ መንግሥቱ በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ ወደ ዕደሳት ገብቷል። የቨርሳይ ቤተ መንግሥት የዕድሳት ባለሙያዎች እገዛ መኖሩም ሌላ ዕድል ነው። አንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን ይፋዊ የኢትዮ-ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅነትም በጽኑ መሰረት ላይ ያቆመ መሆኑን ያሳዬ ነው። የአፍሪካ ቨርሳይ ያልኩት ብሔራዊ ቤተ መንግሥትም ታድሶ እንደ ፈረንሳዩ ቬርሳይ፣ እንደ ሩስያዋ ፒተርሆፍ የዕልፍ አዕላፍ ቱሪስቶች ሰርክ የሚርመሰመሱበት መዳረሻ ሊሆን እነሆ ቀኑ ደረሰ!!
ዘመን ተሻጋሪው የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ወዳጅነት
Dec 21, 2024 594
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ ግንኙነታቸው ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት እንደተጀመረ የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። የሀገራቱ ግንኙነት እየተጠናከረ ሲመጣ የወዳጅነትና የንግድ ስምምነት ወደ ማድረግ እንደተሸጋገሩና በተለይ ኢትዮጵያ የአድዋ ድልን ከተቀዳጀች በኋላ እኤአ በየካቲት ወር 1897 የኢትዮ-ጂቡቲ የድንበር ስምምነት በመፈራረም የዲፕሎማሲያዊ ትብብራቸውን መሰረት ጥለዋል። እኤአ በ1904 የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የወዳጅነት ቢሮ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ መከፈቱ ለግንኙነታቸው መጠናከር የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። ግንኙነታቸው የበለጠ ተጠናክሮ እኤአ በ1907 ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ ከፍታለች። ከዚያ በኋላ እ.ኤ.አ በ1943 የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የባህል ትብብር ማዕከል፣ በ1947 ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤትን፣ በ1955 የፈረንሳይ አርኪኦሎጂ ሚሽንን ወደ የፈረንሳይ ኢትዮጵያ የጥናት ማዕከል እንዲያድግ ማድረግና የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በሁሉም መስክ እንዲጠናከር ተደርጓል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ጀነራል ጉሌ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ፤ በ1973 ደግሞ ሌላው የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅ ፖምፒዱ ያደረጉት ጉብኝት ግንኙነቱ ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን የሚያመላክት ነበር። ሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን 125ኛ ዓመት ክብረ በዓል በ2014 ዓ.ም በተለያዩ መርኃ ግብሮች አክብረዋል። ከሁነቶቹ መካከል በአዲስ አበባ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ማጠናከርን አላማ በማድረግ የተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ይገኝበታል። በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል። የ125ኛ ዓመት ሁነቱ የግንኙነት ዓመታቱን ከመዘከር ባለፈ ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ዳግም ቃል ኪዳናቸውን ያደሱበት ሆኗል። ግንኙነቱ መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርንም ያካተተ ነው። የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የጉብኝት ልውጦች የሀገራቱ ትብብር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጉብኝት ልውውጦች እና የሁለትዮሽ ውይይቶች ይበልጥ እየጠነከረ መጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም በአውሮፓ ሀገራት የስራ ጉብኝት ሲያደርጉ አንደኛዋ መዳረሻቸው ፈረንሳይ ነበረች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ሁለቱ ሀገራት በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል በዓለም አቀፍ መድረክ አንድ በሚያደርጓቸው አጀንዳዎች፣ በጸረ ሸብርና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውም እንዲሁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፈረንሳይን ከጎበኙ ከአምስት ወራት በኋላ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው። ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ተፈራርመዋል። ከስምምነቶቹ መካከል ፈረንሳይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅርስ እድሳት የሙያና የገንዘብ ድጋፍ የምታደርግበት ማዕቀፍ ይጠቀሳል። ማክሮን በወቅቱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን መጎበኝታቸው የሚታወስ ነው። ኢንቨስትመንት እና መከላከያ ሌሎቹ ስምምነት የተፈረመባቸው መስኮች ናቸው። የሁለቱ መሪዎች የጉብኝት ልውውጦች የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይን ትብብር በማጠናከር ረገድ ወሳኝ ሚና የተጫወተ ነው ማለት ይቻላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከአራት ዓመታት በኋላ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም በፈረንሳይ የስራ ጉብኝት አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል። በርካታ የፈረንሳይ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡና ወደ ፈረንሳይ ስትልክ ፈረንሳይ በበኩሏ የትራንስፖርት ቁሳቁሶችና የህክምና መገልገያ መሳሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ በዋናነት ትልካለች። በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሀገሮች በመካከላቸው ያለው የኢኮኖሚ ትስስር እየጎለበተ መጥቷል። የፈረንሳይ የአውሮፓ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት በሕዳር 2017 ዓ.ም የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ይበልጥ ማጎልበትን አላማ ያደረገ የስራ ጉብኝት በኢትዮጵያ አድርገው ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸው ይታወሳል። ሚኒስትሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ጋርም በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየምንና በፈረንሳይ መንግሥት የተመሠረተውን የሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት መጎብኘታቸውም እንዲሁ። ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1960ዎቹ ከመልካ ቁንጥሬ መካነ ቅርስ ለምርምር ወደ ፈረንሳይ ተወስደው የነበሩ ጥንታዊ የሰው ዘር የተገለገለባቸውን የድንጋይ መሣሪያዎች ለቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ማስረከባቸው ይታወሳል። በወቅቱ በፈረንሳይ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚተገበር ቀጣይነት ያለው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ፕሮጀክት ይፋ የተደረገ ሲሆን ፕሮጀክቱ በ2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናትና የብሔራዊ ሙዚየም እድሳትን አስመልክቶ ስምምነት የደረሱበት ስራ አካል ነው። በሚኒስትሩ ጉብኝት ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ከፈረንሳይ ጋር በዘርፉ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል። ስምምነቱ ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የተለያዩ ነጻ የትምህርት እድሎችን ለመስጠት፣ እንዲሁም በሊሴ ገብረማሪያም ትምህርት ቤት የስኮላር ሺፕ መርሃ ግብሮችን ለማጠናከር የሚያስችል ነው። ባሮት የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት እና ፈረንሳይ የከፍተኛ ደረጃ ስትራቴጂካዊ ምክክር መድረክ ላይም ተሳትፎ አድርገዋል። አቪዬሽን ሌላኛው የአገራቱ የወዳጅነት ማጋመጃ ዘርፍ ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በአቪዬሽን ዘርፍ ያላቸው ትብብርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። ሁለቱ አገራት በ2009 ዓ.ም በሲቪል አቪዬሽን፣ በአየር ትራንስፖርት እና መሰረተ ልማት ዘርፎች ትብብራቸውን ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል። በ2008 ዓ.ም ተመሳሳይ ስምምነት አካሂደው የነበረ ሲሆን የ2009 ዓ.ም ያደረጉት ስምምነት ከወቅቱ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም በማድረግ በድጋሚ ተሻሽሎ እንደተፈረመ በወቅቱ ተገልጿል። ስምምነቱ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፈረንሳይ የሚያደርገውን ሳምንታዊ በረራ የሚያሳድግ እና በቀጣይም ተጨማሪ በረራዎችን ለማድረግ የሚያስችል ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤር ባስ ኤ350-1000 "Ethiopia land of origins" የተሰኘ የመንገደኞች አውሮፕላን ከፈረንሳዩ የኤር ባስ ኩባንያ በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም መረከቡ ይታወቃል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም የኤ350-900 አውሮፕላኖችን ጨምሮ ሌሎች በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆኑ አውሮፕላኖችን ቀድሞ በማስገባት የሚታወቅ ነው። ኢትዮጵያ ኤ350-1000 የኤር ባስ አውሮፕላን የተረከበች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አገር መሆኗ ካለው ታሪካዊ ስኬት ጎን ለጎን ሁለቱ አገራት በአቪዬሽን ዘርፍ ያላቸው ትብብር እያደረገ መምጣቱን የሚያመላክትም ነው። በአገራቱ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከፍ የማድረግ መሻት አለ። ኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እያደረጉ ያሉትን ተሳትፎ በማጠናከር የሁለቱ አገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብር እንዲያድግ ፍላጎት አላት። ሁለቱ አገራት የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የትብብር ጉዳዮች ላይ ያላቸው ትስስር እንዲያድግም ትሻለች። ፈረንሳይም የኢትዮጵያን አገራዊ ምክክር ሂደት እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራን ጨምሮ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች። ኢትዮጵያ እያከናወነች ላለችው ፈጣን የልማት እንቅስዋሴ ፈረንሳይ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም እንዲሁ። የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ይፋዊ የስራ ጉብኝትም ይሄንኑ ከፍታ የሚያሳይ ይሆናል። ጉብኝቱ የአገራቱን ጠንካራ ወዳጅነት ይበልጥ የማጽናት ፍላጎት አካል ነው ተብሎ ሊወሰድም ይችላል።
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ይበልጥ የተጠናከረው የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ወዳጅነት
Dec 21, 2024 476
የኢትዮጵያና ፈረንሳይ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዘመናትን የተሻገረ ቢሆም በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ በብዙ ዘርፎች ግንኙነቱ ይበልጥ ጎልብቷል። በዚህም በሀገራቱ መካከል በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በሰላምና ጸጥታ፣ በአቪዬሽንና በሌሎችም መስኮች የጠበቀ ትስስር መፍጠር ተችሏል። የሀገራቱ ትብብር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመሪዎች የጉብኝት ልውውጦች እና የሁለትዮሽ ውይይቶች ይበልጥ እየጠነከረ መጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም በአውሮፓ ሀገራት የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አንደኛዋ መዳረሻቸው ፈረንሳይ ነበረች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ሁለቱ ሀገራት በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወቃል። ከእነዚህ መካከልም በዓለም አቀፍ መድረክ አንድ በሚያደርጓቸው አጀንዳዎች፣ በጸረ ሽብርና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፈረንሳይን ከጎበኙ ከአምስት ወራት በኋላ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል። ፕሬዚደንት ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ተፈራርመዋል። ከስምምነቶቹ መካከል ፈረንሳይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅርስ እድሳት የሙያና የገንዘብ ድጋፍ የምታደርግበት ማዕቀፍ ይጠቀሳል። ፕሬዚደንት ማክሮን በወቅቱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን መጎበኝታቸው የሚታወስ ነው። ኢንቨስትመንት እና መከላከያ ሌሎቹ ስምምነት የተፈረመባቸው መስኮች ናቸው። የሁለቱ መሪዎች የጉብኝት ልውውጦች የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይን ትብብር በማጠናከር ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከአራት ዓመታት በኋላ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም በፈረንሳይ የስራ ጉብኝት አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸው ይታወሳል። በርካታ የፈረንሳይ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡና ወደ ፈረንሳይ ስትልክ ፈረንሳይ የትራንስፖርት ቁሳቁሶችና የህክምና መገልገያ መሳሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ በዋናነት ትልካለች። በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሀገሮች በመካከላቸው ያለው የኢኮኖሚ ትስስር እየጎለበተ መጥቷል። የፈረንሳይ የአውሮፓ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት በሕዳር 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ይበልጥ ማጎልበትን አላማ ያደረገ ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል። ባሮት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ጋርም በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል። ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት በቆይታቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየምንና በፈረንሳይ መንግሥት የተመሠረተውን የሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ጎብኝተዋል። ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1960ዎቹ ከመልካ ቁንጥሬ መካነ ቅርስ ለምርምር ወደ ፈረንሳይ ተወስደው የነበሩ ጥንታዊ የሰው ዘር የተገለገለባቸውን የድንጋይ መሣሪያዎች ለቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ማስረከባቸውም እንዲሁ። በወቅቱ በፈረንሳይ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚተገበር ቀጣይነት ያለው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል። ፕሮጀክቱ በ2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናትና የብሔራዊ ሙዚየም እድሳትን አስመልክቶ ስምምነት የደረሱበት ስራ አካል ነው። በሚኒስትሩ ጉብኝት ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ከፈረንሳይ ጋር በዘርፉ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል። ስምምነቱ ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የተለያዩ ነጻ የትምህርት እድሎችን ለመስጠት፣ እንዲሁም በሊሴ ገብረማሪያም ትምህርት ቤት የስኮላር ሺፕ መርሃ ግብሮችን ለማጠናከር የሚያስችል ነው። ባሮት የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት እና ፈረንሳይ የከፍተኛ ደረጃ ስትራቴጂካዊ ምክክር መድረክ ላይም ተሳትፎ አድርገዋል። ኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እያደረጉ ያሉትን ተሳትፎ በማጠናከር የሁለቱ ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብር እንዲያድግ ፍላጎት አላት። ሁለቱ ሀገራት የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የትብብር ጉዳዮች ላይ ያላቸው ትስስር እንዲያድግም ትሻለች። ፈረንሳይም የኢትዮጵያን ሀገራዊ ምክክር ሂደት እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራን ጨምሮ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች። ኢትዮጵያ እያከናወነች ላለችው ፈጣን የልማት እንቅስቃሴ ፈረንሳይ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም እንዲሁ። የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በድጋሚ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም ይሄንኑ ከፍታ የሚያሳይ ነው። ጉብኝቱ የሀገራቱን ጠንካራ ወዳጅነት ይበልጥ የማጽናት ፍላጎት አካል ነው ተብሎ ሊወሰድም ይችላል።
አቪዬሽን የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ወዳጅነት ማሳያ
Dec 21, 2024 365
በመቶ ዓመታት የሚቆጠረው የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ እኤአ በ1907 ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ፈረንሳይ ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ እንድትከፍት አስችሏል። ከዚህ በኋላም በብዙ መስኮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው እያደገና እየጎለበተ መጥቶ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በሰላምና ጸጥታ የጠበቀ ትስስር መፍጠር አስችሏቸዋል። ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በአቪዬሽን ዘርፍም ያላቸው ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። ሁለቱ ሀገራት በ2009 ዓ.ም በሲቪል አቪዬሽን፣ በአየር ትራንስፖርት እና መሰረተ ልማት ዘርፎች ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል። በ2008 ዓ.ም ተመሳሳይ ስምምነት አካሂደው የነበረ ሲሆን 2009 ዓ.ም ያደረጉት ስምምነት ከወቅቱ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም በማድረግ በድጋሚ ተሻሽሎ እንደተፈረመ በወቅቱ ተገልጿል። ስምምነቱ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፈረንሳይ የሚያደርገውን ሳምንታዊ በረራ የሚያሳድግ እና በቀጣይም ተጨማሪ በረራዎችን ለማድረግ የሚያስችል ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤር ባስ ኤ350-1000 "Ethiopia land of origins" የተሰኘ የመንገደኞች አውሮፕላን ከፈረንሳዩ የኤር ባስ ኩባንያ በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም መረከቡ ይታወቃል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም የኤ350-900 አውሮፕላኖችን ጨምሮ ሌሎች በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆኑ አውሮፕላኖችን ቀድሞ በማስገባት የሚታወቅ ነው። ኢትዮጵያ ኤ350-1000 የኤር ባስ አውሮፕላን የተረከበች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ ካለው ታሪካዊ ስኬት ጎን ለጎን ሁለቱ ሀገራት በአቪዬሽን ዘርፍ ያላቸው ትብብር እያደረገ መምጣቱን የሚያመላክትም ነው።