ደመና ማበልጸግ በኢትዮጵያ የአራት ዓመት ጉዞና ስኬት - ኢዜአ አማርኛ
ደመና ማበልጸግ በኢትዮጵያ የአራት ዓመት ጉዞና ስኬት

ደመና ማበልጸግ(Cloud Seeding) ምንድን ነዉ? የደመና ማበልጸግ በደመና ውስጥ ያለውን የዝናብ መጠን ወይም ዓይነት የሚለውጥ(የሚጨምር) የአየር ሁኔታ መቀየሪያ ዘዴ ነው። ይህም ማለት በመሰረታዊነት ዝናብ ሊሆን የሚችልን ነገር ግን አቅም ያጣን ደመና ወደ ዝናብ እንዲቀየር በማፋጠን መዝነብን የመጨመር ተግባር ነው።
የደመና ማበልጸግና ማዝነብ ቴክኖሎጂ በ1940ዎቹ የተጀመረ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ። ደመና ማበልጸግ ቴክኖሎጂን ለመተግበር የተለያዩ መንገዶች ቢኖሩም በዋናነት በአውሮፕላን፣ ባሎን፣ ሮኬት፣ ድሮን እና መሬት ላይ በሚቀመጥ ጀነሬተር በመታገዝ ደመና ላይ ጨው መሰል ብናኝ በመርጨት በዝናብነት ወደ ምድር የማይወርድ ደመናን አቅም ኖሮት እንዲዘንብ ወይም እንዲወርድ ማድረግ ነው። ይህ ሂደት ሰው ሰራሽ ሲሆን የደመና መዝነብን አቅም ከ15-30 በመቶ በማሳደግ ዝናብ እንዲከሰት የማድረግ አቅም አለው።
ይህ ቴክኖሎጂ በተለያዩ ሀገራትና ጊዜያት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በ2013 ዓ.ም ሀገራችን ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጋር ባላት ጠንካራ ግንኙነትና ትብብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ችሏል።
በወቅቱም ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ማዕከል በመጣ አውሮፕላንና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የአየር ላይ ኦፕሬሽን ተደርጓል፤ የማቴሬሪያልና የሙያ ድጋፍ ተገኝቷል።ድርቅ አጋጥሞ በነበረበት በቦረና ጉጂ አካባቢ የዝናብ ማዝነብ ኦፕሬሽን ተከናውኗል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚሰጠው አቅጣጫ ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የተለያዩ ተቋማትን አስተባብሮ ሀገራችን የቴክኖሎጂው ባለቤት የምትሆንበትን መሰረተ ልማትና ሲስተም እንዲያበለጽግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
ሲስተሙን ከመጠቀም አልፎ ከዚህ ቀደም በቻይና ተመርቶ ስንጠቀምበት የነበረው የደመና ማበልጸጊያ(ማዝነቢያ) ግራውንድ ጀነሬተር በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስተባባሪነት በሀገራችን በሙሉ አቅም መሥራት ተችሏል።
በራስ አቅም ልንሰራው በመቻላችን የቴክኖሎጂ ባለቤትነታችንን ከማረጋገጥ ባሻገር የውጭ ምንዛሪን በማዳን ከፍተኛ አገራዊ ጥቅም ሊገኝበት ችሏል።
በ2015 ዓ.ም የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ውሎ በሀገራችን በዝናብ እጥረት የሚያጋጥመውን አደጋ ለመከላከል ለዝናብ ማዝነቢያ የግራውንድ ጄኔሬተር ማምረቻ የሚሆን የፕሮጀክት በጀት መድቧል።
የፕሮጀክት በጀቱንም የማምረት ሥራው ሂደትና ስኬት እየታየ በሁለት ዙር ለመልቀቅ ከኢፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር ውል በተፈራረመው መሰረት በመጀመሪያው ዙር 20 ግራውንድ ጀነሬተር ማምረት ሥራ በስኬት በማጠናቀቅ በኦሮሚያ ክልል በሚፈለግበት ወረዳዎች በሟቋቋም ወደ ኦፕሬሽን እንዲገቡ ተደርገዋል። በሁለተኛው ዙር 25 የግራውንድ ጀነሬተሮቹን የማምረት ሥራው ተጠናቋል፡ ወደ ኦፕሬሽን እንዲገቡም ተደርገዋል።
በአጠቃላይ 45 ጄኔሬተሮች በማምረት የዝናብ እጥረት ለሚያጋጥማቸው ቦታዎች (ደቡብና ምሥራቅ ኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞን፣ በሶማሊ ክልል፣በእንጦጦ ተራራ) ተተክሏል። የአየር ንብረት እና ክላውድ ሲዲንግ መሰረታዊ እውቀት፣የሲስተም ተከላና ኦፕሬሽን በመስክና በታቀደ ስልጠና አቅም ተገንብቷል።
ድሮንን በመጠቀም ሙከራዎች ተደርገዋል። በሚቀጥሉት ጊዜያት በአየር ላይም ኦፕሬሽን ስናደርግ ቴክኖሎጂን በራስ አቅም፣ ባለሙያና ቴክኖሎጂ ለመስራት ጥናትና ትግበራው የሚቀጥል ይሆናል። በአገር ደረጃ የሚመለከታቸውን ተቋማት በማሳተፍ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትና ተጠቃሚነታችንን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ምርምርና ከፍ ያለ ሥራ ይሰራል።
የደመና ማበልጸግ በኢትዮጵያ ፕሮጀክት በዋናነት በኦፕሬሽናልና በተግባራዊ ምርምር ቴክኖሎጂን የመጠቀም፣አስቻይ መሰረተ ልማት የማቋቋም፣ የደመና ማበልጸግ ቴክኖሎጂ ልማትን በሚያሳልጡ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ተልዕኮውን የሚፈጽም ነው።
ይህ ፕሮጀክት ወደ ስራ ሲገባ የተለያዩ ዓላማዎችን አንግቦ ሲሆን የመጀመሪያው በሀገራችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ከባለድርሻ አካል ጋር በመሆን እገዛ ማድረግ፤ በምርምር ፣ ልማት እና ትግበራ ላይ የተመሰረተ ዳመናን ማልማት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ማስቻል ፣በዘርፉ ልህቀት ማዕከል ማቋቋም ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የዳመናን ማልማት ምርምር፣ ልማት እና ትግበራን ለማሳለጥ የሚያግዙ ሀገራዊ የፖሊሲና የመሠረተ-ልማት ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ማቅረብ፤ እንዲሁም በዳመና ልማት ዙሪያ የሚሰማሩ ባለድርሻ አካላት እና የተቋማት ትስስርን ምቹ ምህዳር መፍጠር ነው።