ሀዘንና ደስታ የተሰናሰሉበት ትዕይንተ ጥበብ - "ኩርፍወ" - ኢዜአ አማርኛ
ሀዘንና ደስታ የተሰናሰሉበት ትዕይንተ ጥበብ - "ኩርፍወ"

(በእንዳልካቸው ደሳለኝ - ከኢዜአ ወልቂጤ ቅርንጫፍ)
"ኩርፍወ ጨዋታ" በጉራጌ የተለያዩ ድራማዊ ትዕይንቶች የሚገለፁበት ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ትውፊታዊ እሴት ነው። ይህ ትውፊታዊ ክንዋኔ ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት እንደተጀመረም ከአፈ ታሪክ መረዳት ይቻላል። ይህ ጨዋታ አዝናኝና ማራኪ እንዲሁም ብዙ ጊዜያትን ካስቆጠሩ ባህላዊ ጭፈራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው። ሀዘንና ደስታን አንድ ላይ በማሰናሰል የሚተገበር ሲሆን ተጀምሮ እስኪያልቅም የሚያጓጉ ትዕይኖች ይታዩበታል።
"የኩርፍወ ጨዋታ" ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ፣ ሞትና ትንሳኤ ጋር ተያይዞ የሀዘንና ደስታ መግለጫ ነው። ለሁለት ሳምንታት በዙር ይከወናል። የመጀመሪያው በሰሞነ ህማማት ተጀምሮ እስከ ትንሳኤ የሚቆይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከትንሳኤ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሳኤ ይሆናል፡፡ ይሄኛው ዙር ልጃገረዶቹን ብቻ ሳይሆን ወጣቶች እንዲሁም እናትና አባቶችን ጭምር የሚያሳትፍ ነው። ከትንሳኤ በኋላ መጫወትን ይመርጡታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በደስታ ለመጫወት፣ የፍስክ ምግብና መጠጥንም መጠቀም ስለሚያስችል ነው።
የ"ኩርፍወ ጨዋታ" መከወኛ ስፍራ ጨፌ ወይም ወንዝ በሚገኝበት አካባቢ ሲሆን ልጃገረዶች ከየቤታቸው ሲወጡ ተጋጊጠውና አምረው ደምቀው መታየት ስላለባቸው ሁሉም ባህላዊ የክት ልብሳቸውን ለብሰውና ተውበው ይገኛሉ። ኩርፍው አስደናቂ ከሆኑ ገፅታዎቹ መካከል ሁለት መልኮችን አንድ ላይ አሰናስኖ ማንፀባረቁ ነው። የልጃገረዶቹ የእጅ እንቅስቃሴና የእግር አጣጣል በጉራጌዎች ለጀግና የሚከወነውን "ወርኮ" የተሰኘ ሙሾ የሚያንጸባርቅ ሲሆን ዜማው ደግሞ የደስታ ቅላፄ መሆኑ ነው። የኩርፍወ ጨዋታ የራሱ ዜማ እና ግጥም ያለው ሲሆን ከዜማ አውራጇ ቀጥሎ ሁሉም ተጫዋች አዝማቹን ተቀባብለው ያዜማሉ።
አዝማሪ፡- ተቀባዩ
ኩርፍወ ኩርፍወ (2×) ኤዋዬ ኩርፎ
ኩርፍወ
ኩርፎ ኩርፎ ዋዬ ኩርፎ
ኩርፎ ሞቴም
ባማማቴ
ጎር ቲገባ
ዘር ይገባ
እንደገና በተለየ ዜማ
ኩርፍወ -----------------------ዋይ (2×)
ኩርፍወ በሞቴ
ዃም
ባማማቴ
ውርሰንበት
ገባቴ
......... እያሉ ረዘም ባሉ ግጥሞች ያዜማሉ። ዜማና ግጥሞቹ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ በቅብብሎሽ የመጡ ናቸው።
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ልጃገረዶች ለምልሞና ማራኪ ገጽታ ይዞ በበልግ ወራት በስፋት በሚበቅለው "አምባሬ" ከተባለው የተክል ቅጠል ዝርያ በማገልደም ይጫወታሉ ብለዋል። ጨዋታው በዞኑ በይበልጥ በምሁር አክሊል ወረዳ እንደ ሚዘወተርም አመላክተዋል።
ልጃገረዶቹ አምባሬ የሚባለው ተክል ቅጠል ከእነስሩ ነቅለው በመሸንሽን ወገባቸው ላይ አስረው ልክ እንደ ጉራጌ ባህላዊ ለቅሶ እንቅስቃሴ እጆቻቸውን ዘርግተው እግራቸውን ደግሞ ከመሬት ከፍና ዝቅ በማድረግ ነው ሚጫወቱት።ልጃገረዶች ከየቤታቸው ሲወጡ ባህላዊና የክት ልብሳቸውን ከመልበስ በተጨማሪ በአምባር እና በአልቦ ጌጦች ተሽቆጥቁጠው ፀጉራቸውን ሹርባ በመሰራት ከየአቅጣጫው ወደዚሁ ስፍራ ይተማሉ ብለዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ መከራና ሞት በደስታ መቀየሩን በጭፈራው ይጎላል ነው ያሉት። ኩርፍወ ከሌሎች ባህላዊ የጉራጌ ባህላዊ እሴቶች የሚለየው ራሱን የቻለ ዜማ ፣ ግጥም እና የክዋኔ ስርዓት ያለው መሆኑን ነው።
የ"ኩርፍወ ጨዋታ" ማሳረጊያ ላይ ልጃገረዶች አምቾን ወንዶች በማያገኙት ቦታ ላይ ደብቀው ይቀብራሉ። የደበቁትን አምቾ ወንዶች ካላገኙት የልጃገረዶች የወደፊት መፃኢ ዕድል ብሩህ ተስፋ እንዳለው፤ ካገኙት ደግሞ ለወንዶች የተሻለ ጊዜ ይመጣል ተብሎ እንደሚታመን ወይዘሮ መሰረት ይጠቅሳሉ። ይህ እሴት ጥናት እና ምርምር እንዲደርግበት እንዲሁም ለዘመናት የዘለቀው ድራማዊ ስርዓቱ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲሉም ተናግረዋል ።
በዞኑ የኩርፍወ ጨዋታ ከሚዘወተርበት በዋናነት የሚጠቀሰው የምሁር አክሊል ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳህሉ ወልደማርያም በበኩላቸው ኩርፍወ እርስ በርስ የሚያቀራርብ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴት የሚያንፀባርቅ ነው ብለዋል። አብሮነትና አንድነትን ከመስበክ አንጻር ያለው ሚና የላቀ መሆኑን አውስተው ባህሉ በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ ቢቆይም ከነበረበት እንዲያንሰራራ ተደርጓል ነው ያሉት።
ልጃገረዶች በኩርፍወ ጨዋታ ድራማዊ ትዕይንትን በማሳየት በአንድ በኩል ደስታቸውን ሲያንጸባርቁ በሌላ ጉኑ ሲያዝኑ ይስተዋላል። ጨዋታው የሰሙነ ህማማት የሚሆንበት ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁዳውያን የደረሰበት መከራ፣ ስቃይና ሞት ከዚያም የክርስቶስ ትንሳዔን ለማመላከት ነው። ባህላዊ ትውፊቱ ይዘቱን ሳይለቅ በየአካባቢው እንዲተገበርና የቱሪስት መስህብ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራም መሆኑን ነው አቶ ሳህሉ የገለጹት።
አቶ አለምይርጋ ወልዴ ከልጅነታቸው ጀምሮ ልጃገረዶች ኩርፍወን ሲጫወቱ መመልከታቸው እና በአሁኑ ወቅት ከዚህ እሴት ጋር ተያይዞ መፅሀፍ ለማሳተም እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ። እንደእሳቸው ገለጻ ኩርፍወ ሁለት ኩነቶችን የያዘ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል መሰቀሉንና ሞትንም አሸንፎ ከመቃብር መነሳቱን ምክንያት በማድረግ የሚከወን ነው። በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በሰሞነ ህመማት ሀዘንን በኩርፍወ እንጉርጉሮ ይገልፃሉ። ከህማማት መጀመሪያ እስከ ስቅለት ባለው ጊዜ በጉራጌ ለጀግና "ወርኮ" በሚባለው የሙሾ ሥርአት መሰረት ልጃገረዶች ሲያዜሙ ይስተዋላል። ከትንሳኤ እለት እስከ ዳግማዊ ትንሳኤ ደግሞ የኩርፍወ አጨፋፈር፣ ዜማና ግጥሞች ለየት ባለ መልኩ ነው የሚቀርቡት።
የጌታን መነሳት ምክንያት በማድረግ ደስታቸውን የሚገልጹበት ነው። ከትንሳኤ እስከ ዳግማዊ ተንሳኤ የሚያዜሙት ዜማ ከሰሞነ ህማማት ልዩነት አለው። የሚበዛ ትዕይንት የሚበዛውና ጭፈራ ያለው መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ወይዘሮ ጀምበርነሽ አርጋ በምሁር አክሊል ወረዳ ግናብ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። የኩርፍወ ጨዋታ በልጅነታቸው አምረውና ደምቀው ያሳለፉት ውብ ባህላዊ ስርዓት መሆኑን ያነሳሉ። የኢየሱስ ክርስቶስ በእለተ አርብ የደረሰበተን ሞት እና ስቃይ በማስመልከት ሀዘናቸውን የሚገልጹበትና ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱን የሚያሳየው ጫወታ ላይ ከመሳተፍ ባለፈ ከየቤታቸው ምግብ በማዋጣት በጋራ በልተውና ጠጥተው ያሳልፉበት ባህላዊ እሴት እንደ ነበር አስታውሰዋል። ይህ እሴት እንዳይጠፋ ዛሬ ላይ ለወጣት ሴቶች ለማሸጋጋር ልምዳቸውን እያጋሩ መሆኑን ነው የገለጹት።
በወረዳው ግናብ ቀበሌ የምትኖረውና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኩርፍወ ጨዋታ ላይ በንቃት እየተሳተፈች መሆኗን የተናገረችው ደግሞ ወይዘሪት ሰላም ምትኩ ናት። የኩርፍወ ጨዋታ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቶችን አጣምሮ የያዘ ልዩ ትዕይንት እንደሆነ አንስታ ጭፈራው፣ ዜማው እና ድራማዊ ትዕይንቱ ይበልጥ እንደሚስባት ተናግራለች።
ከበሮዋን ይዛ፣ ማስጌጫ ቅጠሉን በወገቧ አገልድማ በዜማና ጭፈራ ወጣት ወንዶች በተገኙበት ከሰሞነ ህማማት እስከ ዳግማዊ ትንሳኤ ትውፊታዊ ስርአት በጠበቀ መልኩ እንደምታሳልፍም አውስታለች። መንግስት ይህን ባህላዊ እሴት ለመታደግ እየሰራ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ወይዘሪት ሰላም አመላክታለች።
ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል ኑረዲን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀት ክፍል ተጠሪና የቋንቋ መምህር ናቸው። ኩርፍወ በትዕይንት የተሞላና ለረጅም ዘመናት በቅብብሎሽ የተሻገሩ ግጥሞች አሉት ይላሉ። ልጃገረዶቹ ደብቀው የሚቀብሩትን አሚቾ (የኮባ ስር የውስጠኛው ክፍል) ለማግኘት የሚደረገው ግብግብ። የተደበቀው እንዳይገኝ ቦታውን ለማሳት የሚደረግ ጥረት። ወንዶች የተቀበረበት ነው ብለው የሚያስቡትን ቦታ ማሰሳቸው የትዕይንቱ አካላ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ወንዶች የተደበቀውን አሚቾ ፈልገው ካገኙት ዘመኑ ለእነሱ ገዳም እንደሚሆን ሲታመን ካላገኙት ደግሞ የሴቶች መልካም ዘመን ነው ተብሎ ይታሰባል።
የኩርፍወ ጨወታ ባለቤቶች ልጃገረዶች እንደመሆናቸው መጠን ወደፊት ስለሚገጥማቸው ትዳርም ጭምር መልካምነት የተቀበረው አሚቾ የማሳየት ብቃት ይኖረዋል ተብሎ ስለሚታመን እጅግ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ነው ጨዋታውን የሚያስኬዱት። ይህ ትዕይንት ዘርፈ ብዙ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ሀላፊነቱን ለመወጣት ይሰራል ሲሉም ነው ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል የገለጹት።