በጋምቤላ ክልል የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች የክረምት ቅድመ ጥንቃቄና የዝግጅት ስራዎች ተጀምረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች የክረምት ቅድመ ጥንቃቄና የዝግጅት ስራዎች ተጀምረዋል

ጋምቤላ ፤ ሚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች የክረምት ቅድመ ጥንቃቄና የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የክረምት ወራት የአደጋ ምላሽ እቅድ ማዘጋጀቱን ገልጿል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጃክ ጆሴፍ ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ ዝቅተኛና ትላልቅ ወንዞች አቋርጠው የሚያልፉበት በመሆኑ በክረምት ወራት የጎርፍ ተጋላጭነቱ ከፍተኛ ነው።
በተለይም ባሮን ጨምሮ ክልሉን አቋርጠው የሚያልፉ አራት ትላልቅ ወንዞች ከደጋና በአካባቢ በሚጥለው ዝናብ ሞልተው በመፍሰስ በወንዞች አካባቢ የሚኖሩ በርካታ ዜጎችን እንደሚያፈናቅል ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ይህን ታሳቢ በማድረግ ከክልሉ እስከ ወረዳ የጎርፍ መከላከል ግብረ ሃይል አደረጃጀቶችን በመፍጠር በተጋላጭ አካባቢዎች የቅደመ ጥንቃቄና የዝግጅት ስራዎች ከወዲሁ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በገጠር ወረዳዎች አካባቢ ውሃ ሰብሮ በሚገባባቸው ቦታዎች በአፈር የመገደብ እንዲሁም ጋምቤላን ጨምሮ በከተሞች በቆሻሻ የተሞሉ የውሃ ማፋሰሻ ቦዮችን የማጽዳት ስራ የእተከወነ ነው ብለዋል።
የጎርፍ አደጋ የሚከሰትበት ጊዜ ከመቃረቡ ጋር ተያይዞ የጤና፣ የውሃ፣ የትምህርትና ሌሎች የልማት ዘርፍ መስሪያ ቤቶች የተካተቱበት የጋራ አደጋ ምላሽ እቅድ መዘጋጀቱንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
የጋምቤላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ጀምስ ፖል በበኩላቸው የጋምቤላ ከተማ በክረምት ወራት በአካባቢው በሚጥላው ዝናብና የባሮ ወንዝ በሚሞላበት ወቅት ለጎርፍ አደጋ ይጋለጣል ብለዋል።
ማዘጋጃ ቤቱ ይህን ታሳቢ በማድረግ የክረምቱ ወራት ከመግባቱ በፊት የውሃ ማፋሰሻ ቦዮች ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የማጽዳትና ተጨማሪ የውሃ ማፋሰሻ ቦዮችን የመገንባት ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ጋምቤላ ከተማንና ኢታንግ ልዩ ወረዳን ጨምሮ በኑዌርና በአኝዋሃ ዞኖች የሚገኙ ወረዳዎች የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች እንደሆኑ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።