በቀጣዮቹ ቀናት በኢትዮጵያ፣ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች ሞቃታማ የአየር ሁኔታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 14/2017(ኢዜአ):-በቀጣዮቹ ቀናት በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ ኬንያ ከመደበኛው በላይ የሙቀት መጠን የሚመዘገብ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት (ኢክፓክ) አስታውቋል።

የኢክፓክ የአየር ትንበያ መረጃ እንደሚያመለክተው በሱዳን በርካታ አካባቢዎች በኢትዮጵያ በተለይም የአፋር ክልል በቀጣዮቹ ስምንት ቀናት ከፍተኛ የሙቀት መጠን ሊመዘገብ የሚችል መሆኑን ጠቁሟል።

በደቡብ ሱዳንና ኤርትራ እንዲሁም በሰሜን፣ምእራብና ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ደግሞ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ሙቀት የሚኖር ይሆናል።

በጅቡቲ፣ሶማሊያ፣ዩጋንዳ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ በተመሳሳይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ሙቀት ሊመዘገብ ይችላል የሚል የትንበያ መረጃ አስነብቧል።

በአብዛኛው የኤርትራ ክፍል፣በጅቡቲ፣ታንዛኒያ፣ኢትዮጵያ፣ኡጋንዳ፣ ምእራባዊ የኬንያ ክፍል፣ በማእከላዊና ሰሜን የሶማሊያ ግዛቶች ከመደበኛው ባላይ ሙቀት እንደሚኖራቸው ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ ምእራባዊ የሀገሪቱ ክፍሎች፣በሩዋንዳ፣ብሩንዲ፣በሰሜንና ደቡባዊ ታንዛንያ፣በኡጋንዳ ምእራባዊ ክፍል እንዲሁም በኬንያ ጠረፋማ አካባቢዎች መጠነኛ ዝናብ እንደሚኖርም ይጠበቃል።

የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት (ICPAC) የአየር ትንበያና ሌሎች ተያያዥ ወቅታዊ ክስተቶችን በመተንበይና በመተንተን የቅድመ ጥንቃቄ መልእክቶችን በማጋራት ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም