የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም የሚችልና ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ የተፋሰስ ልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው - ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም የሚችልና ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ የተፋሰስ ልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው - ግብርና ሚኒስቴር

አዳማ፤ ሚያዚያ 3/2017(ኢዜአ)፦ የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም የሚችልና ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ የተፋሰስ ልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
በዘንድሮው የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ እቀባ የተፋሰስ ልማት ስራ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ መከናወኑ ተገልጿል።
የዘንድሮውን የበጋ ተፋሰስ ልማት ክንውንና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ዝግጅት ላይ ያተኮረ የሁሉም ክልሎች የግብርና ቢሮ አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢያሱ ኤሊያስ(ፕ/ር) በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት የተፋስስ ልማትን በሳይንሳዊ መንገድ በመምራት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚያጋጥም ድርቅና ጎርፍን የመቋቋም ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
በተጨማሪም የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ሳይንሳዊ አሰራርን የተከተለ የተፋሰስ ልማት ስራ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የተፋሰስ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ ስራ በዘመቻ ብቻ ሳይሆን ሳይንሳዊ ይዘትና አሰራርን በተከተለ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የባለሙያዎችና የአመራሮች ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የዛሬው መድረክ በተፋሰስ ልማቱና በችግኝ ዝግጅቱ ሂደት ላይ ያገጠሙ ክፍተቶች ተገምግመው ችግሮችን በመለየት ቀጣይ የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው ብለዋል።
ከተፋሰስ ልማት ስራ ጎን ለጎን ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፕሮግራም የመትከያ ጉድጓድ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
የተፋሰስ ልማቱ ከዘመቻ ባለፈ የህዝቡ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የተደረገና ውጤታማ እየሆነ የመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን በበኩላቸው በዘንድሮው የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ21 ሺህ 379 በላይ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው ከ598 ሺህ በላይ ሄክታር ከንክኪ ነፃ የተደረገበት ነውም ብለዋል።
በተፋሰስ ልማት ስራው በርካታ ህዝብ መሳተፉን የገለፁት አቶ ፋኖሴ አዲስ ከሚሰራው የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ በተጓዳኝ አምና የተሰሩትን ዕርከኖች የማደስና የመጠገን ስራ መከናወኑንም አመላክተዋል።
ህዝቡ በአማካይ ለሁለት ወራት የተፋሰስ ልማት ስራውን በነቂስ ወጥቶ ሲያከናውን መቆየቱንም ገልጸዋል።