የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ)፡-70ኛው አፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም(GHACOF 70) ግንቦት 11 እና 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ፎረሙ የሚካሄደው “የአየር ንብረት አገልግሎት፤ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አቅምን በጋራ ማጠናከር ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል(ICPAC) ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ፎረሙን እንዳዘጋጀ ተገልጿል።
እ.አ.አ ከማርች እስከ ሜይ 2025 ያለው የአየር ንብረት ትንበያ አፈጻጸም ውይይት እንደሚደረግበት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በፎረሙ እ.አ.አ ከጁን እስከ ሴፕቴምበር 2025 ያለው ቀጣናዊ የአየር ትንበያ ይፋ እንደሚደረግ አመልክቷል።
የአየር ንብረት ትንበያ እና አስተዳደር ስትራቴጂዎች ፋይዳ የተመለከተ ውይይትም ይደረጋል።
በፎረሙ ላይ የኢጋድ አባል ሀገራት፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት አጋሮችንና የዘርፉ ተዋንያንን ይሳተፋሉ።
ከዋናው ፎረም አስቀድሞ የአየር ንብረት ትንበያ እና ተጓዳኝ አውደ ጥናቶች እንደሚካሄዱ ኢጋድ አስታውቋል።
69ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በጥር ወር 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ የሚታወስ ነው።