በምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከል ችግኝ ዝግጅት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከል ችግኝ ዝግጅት እየተከናወነ ነው

ነቀምቴ/ ጭሮ፥ሚያዝያ 17/2017 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞን በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ የተለያየ ዝሪያ ያለው ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን የዞኖቹ ግብርና ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ።
የምስራቅ ወለጋ ዞን የግብርና ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አስፋው ሀምቢሳ እንደገለጹት፥ በዞኑ በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 544 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ባለፉት ዓመታት በተተከሉ ችግኞች ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፥ በዚህ አመትም የበለጠ ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በፅህፈት ቤቱ የተፋሰስ እና የደን ልማት የስራ ሂደት ሀላፊ አቶ ደሳለኝ በልዓታ፤ በዞኑ በዘንድሮው የክረምት መርሃ ግብር የሚተከሉ የደን፣ የእንስሳት መኖ፣ የፍራፍሬና ሌሎች የችግኝ ዘሮች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ዋሴ በቀለ በበኩላቸው፥ ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ካለፉት አመታት በተሻለ መልኩ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በዞኑ በዘንድሮው የሚተከሉ ከ413 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ችግኝ አይነቶች እየተዘጋጁ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ከ82 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት እንደ ጊሽጣ፤ አቮካዶ፤ ዘይቱን፤ ማንጎና የመሳሰሉ የፍራፍሬ ችግኞች እንደሆኑ ገልጸዋል።
ዘንድሮ ለመትከል የታቀደው የፍራፍሬ ዛፍ አይነቶች ቁጥር ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ከ20 ሚሊዮን በላይ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
በዞኑ በየአመቱ እየተተከሉ ያሉት የፍራፍሬ ችግኞች የአርሶ አደሮችን ገቢ በማሳደግና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ አስተዋጽዎ እያበረከቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡