በክልሉ የበጋ ወራት የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከ136 ሺህ ሄከታር በላይ መሬት ላይ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የበጋ ወራት የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከ136 ሺህ ሄከታር በላይ መሬት ላይ ተከናውኗል

ሀዋሳ ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል በበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ አፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከ136 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ መከናወኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ የበጋ ወቅት የተፋሰስ ስራ መዝጊያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የቢሮው ሀላፊ አቶ መምሩ ሞኬ እንዳሉት በክልሉ በበጋ ወቅት የተፋሰስ ልማት ስራ በህዝብ ተሳትፎ ከ136 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ላይ ተከናውኗል።
ለአንድ ወር የተከናወነው የተፋሰስ ልማት የመሬት ለምነትን በመመለስ ምርታመነትን ለመጨመር ማለሙን ተናግረዋል።
በተለይም የመሬት መሸርሸርን ለመከላከል ለጠረጴዛ እርከን ስራ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ የተፋሰስ ልማት በተሰራባቸው አካባቢዎች በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የምግብና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ከ307 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ይተከላሉ ብለዋል።
በደጋማ አካባቢዎች በለሙ ተፋሰሶች ከ85 ሺህ በላይ የአፕል ችግኝ እንደሚተከል ጠቅሰው ከዚህ ጎን ለጎን ባህር ዛፍን በማንሳት በሌላ የመተካት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ቀደም ሲል የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የውሃ ምንጮች እንዲጎለብቱና የአፈር ለምነት እንዲመለስ እንዲሁም የደን ሽፋን እንዲጨምር በማድረግ ለምርትና ምርታማነት ማሳደግ ማገዙን ጠቁመዋል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊና የተፈጥሮ ሀብትና መሬት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፍቅረኢየሱስ አሸናፊ በበኩላቸው በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ክልሉ ካለው ተዳፋታማ የመሬት አቀማመጥ አንጻር የሚስተዋለውን የአፈር መሸርሸር በዘላቂነት ለመከላከል ወሳኝ የሆነውን ጠረጴዛማ እርከን ትኩረት ተሰጥቶ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም 8 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር በላይ መፈጸሙን ገልጸው በእነዚህ ቦታዎች በቀጣይ በስነህይወታዊ ስራዎች የመሸፈን ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
በክልሉ ሀገረ ሰላም ወረዳ ሀለቃ ቀበሌ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ሁኔታ በጎርፍ የሚጠቃ መሆኑን የሚገልጹት አርሶ አደር ፋንታዬ ቡጡነ ጠረጴዛማ እርከን በመስራት ከዚህ ቀደም በዝናብ ወቅት ይደርስባቸው የነበረውን መሸርሸር አስቀርቷል ብለዋል።
የዳራ ኡቲልቾ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጸጋዬ ዳንሳሙ መሬታቸው ተዳፋታማና የዘሩት ሳይቀር በጎርፍ እየተጠረገ ለከፋ ችግር ሲዳረጉ እንደነበረ አስታውሰው በዘንድሮ የተፋሰስ ጠረጴዛማ እርከን በመስራት ችግሩን መከላከል መቻላቸውን ተናግረዋል ።