በመጪዎቹ አሥር ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛዎቹ የበልግ ተጠቃሚ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀጣይነት ይኖራቸዋል -የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 14/2017(ኢዜአ)፡-በመጪዎቹ አሥር ቀናት  ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛዎቹ የበልግ ተጠቃሚ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ቀጣይነት እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት  አስታወቀ።      

ኢኒስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በደቡብ፣ደቡብ ምዕራብ፣ምዕራብ፣በምስራቅ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይኖራቸዋል።    

በዚህም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎችን የሚሸፍን ቀላል መጠን ያለው ዝናብ የሚያገኙ ሲሆን በውሃ አካላትና በከባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ኢኒስቲትዩቱ በትንበያው ይፋ አድርጓል። 

ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎችን ጨምሮ  የደቡብ ምዕራብ እና የምዕራብ  እንዲሁም የሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ቦታዎችን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም ኢኒስቲትዩቱ ገልጿል።      

አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በደቡብ፣ደቡብ ምስራቅ፣ እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚጠቁሙም አስታውቋል።   

በኤፕሪል የሶስተኛው አሥር ቀናት ከሚኖረው ከፍተኛ የጸሀይ ኃይል ጋር በተያያዘ በተለይም በጋምቤላ፣በአፋር፣በሶማሌ ፣ቤንሻንጉል -ጉሙዝና   በምዕራብ አማራ አካባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ35 እንዲሁም በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ ከ40 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሚሆን የኢኒስቲትዩቱ ትንበያ መረጃ ያመለክታል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም