በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሀገር በቀል ችግኞች ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2017(ኢዜአ)፦ ዘንድሮ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሀገር በቀል ችግኞች ትኩረት ተሰጥቶ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዩኒት ክፍል አስተባባሪና የአረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ መርሃ-ግብር ቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በቂ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

በዚህም ዘንድሮ በሚካሄደው ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት በበጋው ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተሰራባቸው፣ የተራቆቱና ሌሎች ለተከላ ዝግጁ በሆኑ ቦታዎች የችግኝ ተከላ እንደሚከናወን ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም ከፌደራል አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ፈፃሚ አብይ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች ወደ ተለያዩ ክልሎች በመሄድ የመትከያ ቦታዎችንና የችግኝ ዝግጅቱን እየተመለከቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በዘንድሮ ዓመት ለችግኝ ተከላ ከሚለየው መሬት 50 በመቶ ለሚሆነው ካርታ እንደሚዘጋጅለትም ገልጸዋል።

በመርሃ-ግብሩ የፍራፍሬ እና የደን ችግኞችን ለተከላ በማዘጋጀት ቅድመ -ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ ሂደት በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል።


 

ለችግኝ ዝግጅት በርካታ የችግኝ ጣቢያዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ገልፀው፤ በዚህም ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ነው አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር) ያነሱት።

ለመርሃ ግብሩ የተሻለ እና ውጤታማ የሆነ የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ካለፉት አመታት በተለየ ሁኔታ ለሀገር በቀል ችግኞች ትኩረት ተደርጎ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም