ስኬታማ የፈጠራ ውጤት ባለቤቶችን ለመደገፍና ለማብቃት ትኩረት ተሰጥቷል

ዱራሜ፤ሚያዝያ 18/2017(ኢዜአ) :-ስኬታማ የፈጠራ ውጤቶች ባለቤቶችን ለመደገፍና ለማብቃት ትኩረት መስጠቱን የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስትቲዩት አስታወቀ፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዱራሜ ከተማ "ብሩህ አዕምሮዎች በክህሎት የበለፀጉ እጆች" በሚል መሪ ሀሳብ ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ጥናትና ምርምር ውድድር ሲምፖዝየምና ኤግዚቢሽን ተጠናቋል፡፡

በማጠናቀቂያው ላይ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት የጥናት፣ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ሙልጌታ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ውጤታማ የፈጠራ ባለቤቶችን የመደገፍና የማብቃት ስራ ትኩረት አግኝቷል፡፡

በተቋማቱና በፈጠራ ባለቤቶች የሚሰሩ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለውድድር የማቅረብና ተሞክሮና ልምድ እንዲወሰዱ እንዲሁም የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውም ይደረጋል ብለዋል።

በቴክኒክና ሙያ የሚሰጠው የስልጠናና የውድድር ስርዓቱ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ደረጃን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ይደረጋልም ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ደቼ በበኩላቸው፥በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በዜጎች ህይወት ላይ ለውጥ የሚያመጡና ችግር ፈቺ ቴክሎጂዎች ማፍለቅ ላይ እንዲያተኩሩ መደረጉን ተናግረዋል።

በተቋማቱ እየተሰሩ የሚገኙ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች የግብርናውን ዘርፍ ጨምሮ ሌሎች መርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች የምርምር ስራዎችን እያወጡ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ወደ ማህበረሰቡ በማውረድ በኩል የሚታየውን ውስንነት ለመቅረፍ በቀጣይ በስፋት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

ከወራቤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የክህሎት ተወዳዳሪና የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ሰምረዲን ተማም፥ በክህሎት ዘርፍ በሰራው የፈጠራ ስራ ተሸላሚ መሆን መቻሉን ገልጿል።

መንግሥት በዚህን ወቅት የፈጠራ ስራን ለማበረታታትና ለማገዝ እያደረገ ያለው ጥረት እና የውድድሩ መዘጋጀት የክህሎትና የቴክኖሎጂን ዘርፍ ውጤታማነት በማረጋገጥና ተተኪዎች ለማፍራት ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ተናግሯል።

በውድድሩም የወራቤ ክላስተር፣የወልቂጤና የቡታጅራ ክላስተሮች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ በመውጣት የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል እንዲሁም የዞንና የልዩ ወረዳዎች ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም