በክልሉ ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል

ሶዶ፤ሚያዚያ14/2017(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ገለጸ።
በቢሮው አዘጋጅነት ክልል አቀፍ የቴክኖሎጂ፣የክህሎት እና ተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር ከነገ ጀምሮ ለአራት ቀናት በሶዶ እና አርባ ምንጭ ከተሞች እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ በዛብህ ገበየሁ ክልል አቀፍ ውድድሩን በማስመልከት በሶዶ ከተማ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ በዛብህ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ በክልሉ ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በተለይ በመካከለኛ ደረጃ ብቁ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ይህም የኢ-ፍትሃዊነት ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎችን ለማሳለጥ ያግዛል ብለዋል።
በሶዶ እና አርባ ምንጭ ከተሞች የሚካሄደው የቴክኖሎጂ፣የክህሎት እና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር ዓላማ ሠልጣኞች ያገኙትን ዕውቀት ወደ ኢንተርፕራይዝ ለማሽጋገር ታስቦ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቴክኖሎጂም የማህበረሰቡን ችግር ከመፍታት ባለፈ ተቋማት ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳትና በማባዛት ሀብት እንዲያመነጩ ታስቦ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድርም ጥናታዊ ሥራዎች በመደርደሪያ የሚቀመጡ ሳይሆን ቴክኖሎጂ፣ ምርት እና አገልግሎት ሆነው እንዲወጡ ነው ብለዋል።
ለአራት ቀናት በሚቆየው ክልል አቀፍ ውድድር በክህሎት ዘርፍ በ20 ሙያዎች፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ደግሞ በ14 ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም በስድስት የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ውድድር ይካሄዳል ብለዋል።
በውድድሩም የተለያዩ አሠልጣኝ መምህራን፣ ሠልጣኞችና ኢንተርፕራይዞች እንደሚሳተፉም ነው አቶ በዛብህ ያስታወቁት።
በክልል ደረጃ የተዘጋጀውን ውድድር የሚያሸንፉት ተወዳዳሪዎችም በቀጣይ ክልሉን በመወከል በፌዴራል ደረጃ በሚካሄድ ውደድርም እንደሚሳተፉ ታውቋል።