ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ 4ኛው ክልላዊ የስራ ፈጠራ ውድድር መርሃ ግብርን አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ 4ኛው ክልላዊ የስራ ፈጠራ ውድድር መርሃ ግብርን አስጀመሩ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2017(ኢዜአ)፦ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ 4ኛው ክልላዊ የስራ ፈጠራ ውድድር መርሃ ግብርን አስጀምረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ውድድሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት በክልሉ በቴክኒክ ሙያ ኮሌጆች መምህራን እና ተማሪዎች የሚዘጋጁ የፈጠራ ስራዎች የማህበረሰቡን የእለት ተእለት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያቃልሉ ሊሆኑ ይገባል።
በውድድሩ 12 የቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች 34 መምህራን፣ 59 ተማሪዎች እና 2 የግል ድርጅቶች መቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በተወዳዳሪዎቹ ተዘጋጅተው ከቀረቡ የፈጠራ ውጤቶች መካከል የእርሻ ምርት መሰብሰቢያ ማሽኖች፣ የዶሮ መፈልፈያ፣ የእንስሳት መኖ ማዘጋጃና ለቤት ግንባታ የሚውሉ ግብዓቶች እንደሚገኙበትም ተጠቁሟል።
ለውድድሩ የሚቀርቡ የፈጠራ ስራዎች የማህበረሰቡን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ መሆን እንደሚገባቸው ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
በውድድሩ ላይ ለእይታ የቀረቡ ምርቶች የክልሉን ህዝብ የእለት ተእለት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያቃልሉና የወጣቶችን የስራ ፈጠራ ባህል የሚያበረታቱ እንዲሆኑም አስገንዝበዋል።
በፈጠራ ላይ የሚሰማሩ ሰዎች የሚሰሯቸውን ሥራዎች ለመደገፍ የክልሉ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
የሶማሌ ክልል የክህሎትና ሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ጌይድ፤ 4ኛ ዙር ዓመታዊ የቴክኒክ ኮሌጆች ያቀረቡት ምርቶች ለግብርና፣ ለእንስሳት እርባታና ለስራ ፈጠራ የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱና አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች የቀረበበት ነው ብለዋል።
ለሶስት ቀናት የሚቆየው ይህ ውድድር "ጤናና አምራች ዜጋ ለሁለንተናዊ እድገት መሰረት ነው" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ የሚቆይ ሲሆን በውድድሩ ለሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች እውቅና እና ሽልማት እንደሚበረክት ገልጸዋል።
በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ፣ የክልሉ የክህሎትና ስራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ጌይድ፤ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ አደንና ሌሎች አመራሮች መገኘታቸው ተጠቅሷል።