ተቋሙ አሰራሩን ዲጅታላይዝ በማድረግ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ነው

ሀዋሳ፤ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ) ፦የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አሰራሩን ዲጅታላይዝ በማድረግ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገለጸ፡፡

አገልግሎቱ ዩኒቨርሲቲው ላበለጸጋቸው አዳዲስ ሶፍትዌሮች እውቅና የመስጠትና በቀጣይ ስራዎችን በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፥ ተቋሙ አሰራሩን ዲጅታላይዝ በማድረግ ለደንበኞቹ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግም ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አዳዲስ መተግበሪያዎችን በማበልጸግ ወደ ስራ ማግባቱን ተናግረዋል።

ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅንጅት የበለጸጉት አዳዲስ መተግበሪያዎችም አገልግሎቱን ለማዘመን ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የበለጸጉት መተግበሪያዎችም የትምህርት ማስረጃን የማጣራት፣ወደ ሌላ ተቋም የመላክና ሌሎች አገልግሎቶችን በፍጥነት ለደንበኞች ለማቅረብ ያስችላሉ ብለዋል፡፡

በቀጣይም ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የፈተና አስተዳደርና የምዝገባ ስርዓቱን ማዘመን የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን ለማበልጸግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ከ34 ሚሊየን በላይ ዜጎችን መረጃ መያዙን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህን መረጃዎች በተፈለጉበት ፍጥነት ለደንበኞች ለማድረስ አዲስ የበለጸጉት መተግበሪያዎች ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑ አስረድተዋል።

በተለይም መረጃዎችን በዘመናዊ መልኩ በመሰነድ ለተለያየ አገልግሎት እንዲውሉ እንደሚያግዙ ተናግረዋል፡፡

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን የሚያስችሉ ሶፍትዌር በማበልጸግ ማስረከቡን ጠቁመዋል፡፡

መተግበሪያው የአገልገሎቱን አሰራር በማዘመን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታና የተደራጀ መረጃን ለመያዝ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም የኒቨርሲቲው ከመደበኛ ማስተማር ስራው በተጓዳኝ የማህበረሰብን ችግሮች የሚፈቱ የምርምር ስራዎችን ከሚያፈልቅበት ስራዎች አንዱ መሆኑን አንስተዋል ብለዋል፡፡

የበለጸገው መተግበሪያ በከፍተኛ ወጪ የቀነሰና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የቀረፈ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ጉመራ ናቸው፡፡

ዪኒቨርሲቲው ያበለጸገው መተግበሪያም ለህዝብ የሚጠቅሙ አዳዲስ አሰራሮችን ለመዘርጋት የሚያደርግው ጥረት አካል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም