ከምርምር ማዕከሉ ያገኙት "ቴላ" የተሰኘ የበቆሎ ዝርያ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አርሶ አደሮች ገለጹ

ሀዋሳ፤ ሚያዚያ 16/2017 (ኢዜአ)፡-ከሀዋሳ መለስተኛ የበቆሎ ምርምር ማዕከል ያገኙት "ቴላ" የተሰኘ የበቆሎ ዝርያ ድርቅን መቋቋምና ምርታማ መሆኑ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በሲዳማ ክልል የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በወረዳው የጋሎ ኡርጌሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት ቴላ የተሰኘው የበቆሎ ዝርያ ተባይና ድርቅን የሚቋቋም ሲሆን ዝርያውን መጠቀም ከጀመሩም አራት አመት ሆኗቸዋል።  

በእነዚህ ጊዜያት የተሻለ ምርት በማግኘትና ገቢያቸውን በማሳደግ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውንም አርሶ አደሮቹ ገልፀዋል። 

ከቀበሌው ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ስምኦን መንገሻ እንዳሉት ቀደም ሲል ሲጠቀሙበት ከነበረው የበቆሎ ዘር በሄክታር ከ50 ኩንታል በላይ ምርት አግኝተው አያውቁም። 

ከዚህ በተጨማሪ ዝርያው የዝናብ እጥረት ሲገጥም ድርቅን መቋቋም ስለማይችልና በቀላሉ በትል ስለሚጠቃ ትሉን ለማጥፋት ኬሚካል ይረጩ እንደነበር አስታውሰው ይህም ለወጪ ሲዳርጋቸው መቆየቱን ተናግረዋል።

ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ በወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል ሥር ካለው ሀዋሳ መለስተኛ የበቆሎ ምርምር ማዕከል ያገኙት "ቴላ" የተሰኘ የበቆሎ ዝርያ ድርቅን ስለሚቋቋም ችግራቸው መፈታቱን ነው የገለጹት።

"ከማዕከሉ ያገኘነው የበቆሎ ዝርያ የዝናብ እጥረት ሲገጥም ሳይደርቅ እድገቱን ይቀጥላል፤ በሄክታርም እስከ 100 ኩንታል ምርት እያገኘንበት ነው ሲሉም" ጠቅስዋል።


 

ሌላው ሞዴል አርሶ አደር ካሳ ካያሞ በበኩላቸው እንዳሉት ከማዕከሉ ያገኙት የበቆሎ ዝርያ ከምርታማነቱና ድርቅን ከመቋቋም አቅሙ ባለፈ የተለየ የምግብነት ጣዕም እንዳለው ተናግረዋል።

ዘንድሮም ከምርምር ማዕከሉ ዘር ወስደው በመዝራት በአሁኑ ወቅት ቡቃያውን እየተንከባከቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አምና ካለሙት ማሳ በሄክታር እስከ 100 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ያስታወሱት አርሶ አደር ካሳ፣ አንዱን ኩንታል በ4 ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ይጠቀሙት የነበረው የበቆሎ ዝርያ በሄክታር ከ20 እስከ 40 ኩንታል ቢገኝበትም በቀላሉ በትል ስለሚጠቃ  ለኬሚካል የሚወጣው ወጪና የሚገኘው ገቢ አይመጣጠንም ነበር ብለዋል።


 

በወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል የሀዋሳ መለስተኛ የበቆሎ ምርምር ማዕከል ተመራማሪና የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ይድነቃቸው መርዕድ እንዳሉት "ቴላ" የበቆሎ ዝርያ ባለፉት አራት ዓመታት ምርምር ከተደረገባቸው የበቆሎ ዝርያዎች አንዱ ነው።

ይህ የበቆሎ ዝርያ ቀደሞ አርሶ አደሩ ሲጠቀምበት ከነበረው በቆሎ ጋር ሲነጻጸር ተባይ፣ በሽታንና ድርቅን የመቋቋም አቅሙና ምርታማነቱ ከፍተኛ እንደሆነ በምርምር መረጋገጡን ተናግረዋል።

በአርሶ አደሩ ዘንድ ያለው ተፈላጊነት ከፍተኛ በመሆኑ ይህን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ለማቅረብ ዘር ከሚያባዙ ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ጠቁመዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም