የኢትዮ-ቻይና የባህል እና የቋንቋ ልውውጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና የቻይና የባህል እና የቋንቋ ልውውጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) ገለጹ።

የቻይና ቋንቋ ቀን በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የቻይና ቋንቋ ቀን በተቋሙ መከበር የሀገራቱን ባህሎች ለመተዋወቅ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ የሚበረታታ ተግባር ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ እና የቻይና የባህል እና የቋንቋ ልውውጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ቋንቋ ሰዎችን፣ ባህልንና ጥበብን የሚያገናኝ ድልድይ መሆኑንም ጨምረው አመላክተዋል።

እንደ ኮንፊሺየስ የሙያ ትምህርት ተቋም ያሉ የቻይና ቋንቋ ማዕከላት መቋቋማቸው በሁለቱ ሀገራት በባህል፣ ሳይንስና ስነ ጥበብ መካከል ያለውን የጋራ ግንዛቤ ማሳደግ የሚያስችል ተጨማሪ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በአሁኑ ጊዜ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በሌሎች ዘርፎች ካለው ጠቀሜታ የተነሳ የቻይና ቋንቋን የመማር ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በየዓመቱ ተመራቂዎች የቻይና ቋንቋን እንደ ተጨማሪ ትምህርት በተቋሙ እንዲማሩ እንደሚደረግም አመላከተዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የባህል አማካሪ ዣንግ ያዌ በበኩላቸው የቻይና ቋንቋ ቀን መከበሩ በቻይና ቋንቋ የተካተተውን ታሪክና ባህል ብቻ ሳይሆን መግባባትና አብሮ መኖርን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን የረጅም ጊዜ የሁለትዮሽ ትብብር ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል።

የቋንቋ ልውውጥ በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል ባህሎች እንዲራመዱ እና ጥልቀት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ቻይና ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም