በክልሉ የቴክኖሎጂ ዘርፉን ለስራ እድል ፈጠራ በማዋል የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ ጥረት እየተደረገ ነው

ሀዋሳ ፤ሚያዚያ 17/2017(ኢዜአ):- በሲዳማ ክልል የቴክኖሎጂ ዘርፉን ለስራ እድል ፈጠራ በማዋል የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

በሲዳማ ክልል የቴክኖሎጂ፣ ክህሎትና የጥናትና ምርምር አውደ ርዕይ በሀዋሳ ሚሊኒየም አደባባይ ተከፍቷል።

የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ፤ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ዘርፉን  በማጠናከር ልማትን ለማፋጠን ግብ ተቀምጦ እየተተገበረ ነው ብለዋል።


 

በእስካሁኑ ሂደትም በክልሉ በመፍጠርና በማሻሻል እንዲሁም መቅዳትና ማሸጋገር የቻሉ በርካታ ተወዳዳሪ ዜጎች መፈጠራቸውን ጠቁመዋል።

ውጤቱንም ይበልጥ ለማሳደግ  በዘርፉ ተሰማርተው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውም አቶ በየነ ተናግረዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ተወካይና የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ  በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት ለቴክኒክና ሙያ ዘርፎች በሰጠው ትኩረት ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይህንንም ለማጠናከር ሙያንና ክህሎት ለማሳደግና  ልምድ ለመለዋወጥ የሚያግዙ ውድድሮችና አውደ ራዕዮች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል ስራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሀገረጽዮን አበበ በበኩላቸው በክልሉ በፈጠራና ቴክኖሎጂ ዘርፉ ያለውን ዕምቅ አቅም ለስራ ፈጠራና የዜጎች ህይወት የሚለውጥ እንዲሆን ታቅዶ በመሰራቱ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።

በተለይም ወደ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች ለመቀላቀል የነበረው አመለካከት በመቀየሩ በርካቶች በዚህ ሂደት እያለፉ ህይወታቸውን እየቀየሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ ከራሳቸው አልፈው ሀገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ መወከል የቻሉ ሰልጣኞች መፈጠራቸውን አንስተው ''ይህን አጠናክረን መቀጠል ይገባናል'' ብለዋል።

ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ውድድር በክልሉ ከሚገኙ ከመንግስት፣ከግል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የተውጣጡ አሰልጣኞችና ሰልጣኞች እንዲሁም በኢንተርፕራይዞች የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች መቅረባቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም