የሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያ በድሮን ቴክኖሎጂ የገነባችውን አቅም አደነቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያ በድሮን ቴክኖሎጂ የገነባችውን አቅም አደነቀ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ የሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያ በድሮን ቴክኖሎጂ የገነባችውን አቅም አድንቋል።
በሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ በሪድ የተመራ የልዑካን ቡድን የስካይ ዊን ኤሮናቲክስ ኢንደስትሪንና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን መጎብኘቱን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡
የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በመርሐ-ግብሩ መሳተፋቸውንም ጠቁሟል፡፡
በጉብኝቱ የተሳተፉት የሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል የአቅም ግንባታ ዘርፍ ተወካይ ኮለኔል ሜጀር ሳልህ ኢዲን ሪዞኒ የስካይ ዊን ኤሮናቲክስ ኢንደስትሪን በመጎበኘታቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ የደረሰችበት ደረጃ የሚደነቅ መሆኑንም ጨምረው መናገራቸው በመረጃው ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በድሮን ቴክኖሎጂ የምታከናውናቸው ተግባራትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ብሔራዊ ደኅንነትንና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ በተለያየ መልክ የሚገለጹ ፋይዳዎች እንዳሉትም ኮለኔል ሜጀር ሳልህ ኢዲን ሪዞኒ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያና የሞሮኮ የመረጃና የደኅንነት ተቋማት በተለያዩ መስኮች በትብብር ሢሰሩ መቆየታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ ጠቁሟል፡፡