ኮሌጆች ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት ተወዳዳሪነትን ማሳደግ አለባቸው

አሶሳ፤ሚያዝያ 18/2017(ኢዜአ):-በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ችግር ፈቺ እና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንዳለባቸው የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው ከአሶሳ ዩኒቨርስቲ እና ከአሶሳ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር "ክልላዊ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ እና ጥናትና ምርምር ውድድር" በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱሰላም ሸንገል በወቅቱ እንደገለፁት፥ ኮሌጆች ችግር ፈቺ እና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሰው ሀይል ለማፍራት የተያዘውን ግብ ለማሳካት ተወዳዳሪዎች ባገኙት ዕድል መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ውድድሩ የቴክኖሎጂ ትውውቅን በማጎልበት ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶች እንዲወጡ ያግዛል ያሉት አቶ አብዱሰላም ተወዳዳሪዎች ያካበቱትን ዕውቀት የሚያዳብሩበት ነው ብለዋል።

የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች የሚሰጡት ተግባር ተኮር ስልጠና ውጤት የሚታይበት እንዲሁም ክፍተቶችን ለመለየት የሚያስችል ውድድር መሆኑን አንስተዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ የክህሎት እና ተቋማት ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አህመድ ሙሳ በበኩላቸው የዚህ ውድድር አሸናፊዎች በቀጥታ በሀገር አቀፍ ውድድር ይሳተፋሉ ብለዋል።

የቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ እና የቴክኖሎጂ ትስስር ለመፍጠር አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

ውድድሩ "ብሩህ አዕምሮዎች፤ በቴክኒክ የበቁ ዜጎች" በሚል መሪ ሃሳብ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ይካሄዳል።

በአውቶ መካኒክ፣ ኤሌክትሪክ ስራ፣ ኮንስትራክሽን፣ በእንጨት ስራ እና በአጠቃላይ በስምንት ሙያዎች ውድድሩ ይደረጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም