ኢዜአ የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት ለአገራዊ ግቦች ስኬት ሚናውን ይወጣል - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት ለአገራዊ ግቦች ስኬት ሚናውን ይወጣል

አዲስ አበባ፤መጋቢት 24/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች አቅም በመገንባት ለአገራዊ ግቦች ስኬት ሚናውን እንደሚወጣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ነጋሲ አምባዬ ገለፁ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከዜና ዘገባ ባሻገር የተቋማትን የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች አቅም ለማጎልበት የተለያዩ የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎችን በመስጠት ይታወቃል፡፡
ተቋሙ ከዚህ ቀደም በርከት ላሉ የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች በዜና አዘጋገብ፣ በቪዲዮ ቀረፃና ኤዲቲንግ፣በፎቶ አነሳስ እና መሰል ሙያዎች አቅማቸውን የሚያጎለብት ስልጠና በመስጠት የበኩሉን ሚና ተወጥቷል፡፡
የዚሁ አካል የሆነውና ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።
ስልጠናው ሶስት ርእሰ ጉዳዮችን በመያዝ በምስልና ድምፅ ቀረፃ፣በምስልና ድምፅ ቅንብር ፣ በድምፅና ምስል ክምችት (አርካይቭ) አያያዝ እንዲሁም በመፅሄት ዝግጅት ላይ ተሰጥቷል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ መልእከት ያስተላለፉት የኢዜአ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ነጋሲ አምባዬ፤ ተቋሙ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን በስልጠና ለማብቃት የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል፡፡
ባለሙያዎቹ በስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ለተቋማቸው ለውጥ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በቀጣይም ኢዜአ የመረጃ ተደራሽነትን ውጤታማ ለማድረግ የሚሰጠውን ስልጠና አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኢትዮጵያን ወደ ምታስበው የብልፅግና ማማ ለማሸጋገር በሚደረገው ጉዞ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው በቆይታቸው ጥሩ የሙያ ክህሎትና እውቀት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የመጡት ሰልጣኝ ሮቤል አህመድ ስልጠናው ለሚሰሩት ሥራ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥርላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የመጣችው የሻረግ ደበበ በበኩሏ በስልጠናው ያገኘሁትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር የመረጃ ተደራሽነት ውጤታማ ለማድረግ በተሻለ ሁኔታ እሰራለሁ ስትል ገልጻለች።
ስልጠናው እንደ ተቋም የኮሙኒኬሽን ስራችንን በአግባቡ ለመስራት ትልቅ አቅም የሚሰጥ ነው ሲል ከኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለስልጣን የመጣው አቶ ቸርነት አባተ ተናግሯል።
ከአማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመጣችው እቴነሽ ማሞ ከስልጠናው ያገኘሁትን እውቀት እና ክህሎት በመጠቀም የተሻለ ስራ ለመስራት ተዘጋጅቻለሁ ብላለች።
ሰልጣኞቹ ኢዜአ ለተለያዩ ተቋማት የሚሰጠው ስልጠና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉ ሲሆን መሰል ስልጠናዎች ተቋማት እውቀትን ማዕከል ያደረገ አሰራርን በመከተል የተሻለ ስራ እንዲሰሩ ያግዛቸዋል ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል።